ሾልኮ የወጣው የፓኪስታን የቢንላደን ዘገባ | ዓለም | DW | 11.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሾልኮ የወጣው የፓኪስታን የቢንላደን ዘገባ

ቢንላደን እንዳይያዙ በመጠበቅ ከለላ አድርገዋል ሲል በስም የጠቀሰው ባለሥልጣን ባይኖርም ከአሁኑም ሆነ ከቀድሞ ባለሥልጣናት ድጋፍ ያደረገላቸው እንደማይጠፋ ጠቅሷል ። ምዕራባውያን ተንታኞች ግን የፓኪስታን የደህንነት ባለስልጣናት ቢንላደን የኖሩበት የነበረውን ቤት ለይተው ማወቅ ያለመቻላቸው ምክንያት ቸልተኝነት ነው የሚለውን አይቀበሉም ።

የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ፓኪስታን ውስጥ ከዛሬ 2 ዓመት በፊት እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ እንዴት ይኖሩ እንደነበረ እንዲያጣራ ፓኪስታን ያቋቋመችው ኮሚሽን ዘገባ ሾልኮ መውጣት የፓኪስታንን መንግሥትና የሃገሪቱን የደህንነት መስሪያ ቤቶች በእጅጉ አሳፍሯል ። መቀመጫው በቀተር የሚገኘው አልጀዚራ ይፋ ያደረገው የፓኪስታን ዳኞች አጣሪ ኮሚሽን ዘገባ ቢን ላደን ከ9 ዓመት በላይ ሳይደረስበት ፓኪስታን መኖር የቻለው ፣ በፓኪስታን ባለሥልጣናት የብቃት ጉድለትና ና ቸልተኝነት መሆኑን አጋልጧል ። ኦሳም ቢንላደን ፓኪስታን ውስጥ ሳይደረስባቸው እንዴት 9 ዓመት ሊኖሩ እንደቻለ እንዲመረመር አጣሪ ኮሚሽን የተቋቋመው በቀድሞው የአሲፍ አሊ ዛርዳሪ መንግሥት ነበር ።

Pakistan Javed Iqbal Leiter der Abbottabad Kommission

ጃቬድ ኢክባል

5 አባላት ያሉት በቀድሞው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጃቫድ ኢክባል የሚመራው ይኽው አቦታባድ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ኮሚሽን ከ 200 በላይ ሰዎች አነጋግሯል ። ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው መካከልም ከፍተኛ የሲቪል ና ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም በተገደሉበት ግቢ ውስጥ አብረዋቸው ይኖሩ የነበሩ 3 ባለቤቶቻቸው ይገኙበታል ። በ336 ገፅ የተጠናቀረው የኮሚሽኑ ምርመራ ውጤት አልጀዚራ ይፋ እስካደረገው ድረስ በሚስጥር ነበር የተያዘው ። ዘገባውን ማን አሹልኮ እንዳወጣው ግልፅ አይደለም ። ስለዘገባው የፓኪስታን ጦር ኃይል አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል ። ዘገባው ቢንላደን እንዳይያዙ በመጠበቅ ከለላ አድርገዋል ሲል በስም የጠቀሰው ባለሥልጣን ባይኖርም ከአሁኑም ሆነ ከቀድሞ ባለሥልጣናት ድጋፍ ያደረገላቸው እንደማይጠፋ ጠቅሷል ። እነዚሁ ባለሥልጣናትም ለቸልተኝነታቸው በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል ብሏል ። አንዳንድ ምዕራባውያን ተንታኞች ግን የፓኪስታን የደህንነት ባለስልጣናት ቢንላደን የኖሩበት የነበረውን ቤት ለይተው ማወቅ ያለመቻላቸው ምክንያት ቸልተኝነት ነው የሚለውን ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም ። ከዚያ ይልቅ ከለላ ያደርጉላቸው ነበር ብለው ነው የሚያስቡት ። ይህን ከሚሉት አንዱ መቀመጫውን ጀርመን ያደረገው በአሸባሪነትና በፀጥታ መርህ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያካሂደው ተቋም ሃላፊ ሮልፍ ቶፕሆፈን ናቸው ።

Bin Ladens Versteck in Abbottabad , Pakistan

ቢንላደን የተገደሉበት የአቦትአባዱ ቤት

« መዘንጋት የሌለበት ነገር በምህፃሩ ISI በሚባለው የፓኪስታን የስለላ ድርጅትና በአልቃይዳ መካከል ከመስከረም 1 ፣ 1994 ቱ የኒውዮርኩ የአሸባሪዎች ጥቃት በፊትም ቢሆን የመገናኛ መስመር ነበር ። »

በቶፕሆፈን አስተያየት አጣሪው ኮሚሽን ብቃት ጎድሏቸዋል በማለት ፣የአልቃይዳውን መሥራች ቢንላደንን ሃገራቸው የደበቁትን የፓኪስታን ደህንነት ባለሥልጣናት እንደዋዛ አልፏቸዋል ። ቶፕሆፈን እንደሚሉት የስለላው መስሪያ ቤት አቅም ያነሳዋል የሚባል አይደለም ።

« ISI ስለ ቢንላደን ካላወቀ ከዓለም የመጨረሻው ደካማ የደህንነት ድርጅት በሆነ ነበር ። ሆኖም ሰዉ እንደሚያስበው አሁን በርግጠኝነት ያን ያህል ደካማ መስሪያ ቤት አይደለም ። በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን በሙሉ ያውቃል ። በጎሳዎቹ አካባቢዎች በሰሜን ምዕራብ የውጊያ ግንባሮች በሃገር ውስጥም ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያውቅ በጣም እርግጠኛ ነኝ ።»

በቶፕሆፈን እምነት አሜሪካኖች በአቦትአባዱ የቢንላደን መሸሸጊያና መኖሪያ ላይ ፓኪስታኖችን ሳይማክሩ ጥቃት ያደረሱት በርግጠኝነት የስለላው መስሪያ ቤት ከአልቃይዳ ጋር አለው ተብሎ በሚጠረጠረው ግንኙነትና በመስሪያ ቤቱም ላይ እምነት በማጣታቸው ነው ።

በርሳቸው አባባል አሜሪካኖች ለፓኪስታኖች ዘመቻው እንደሚካሄድ ቢያሳውቁ ኖሮ መረጃውን ለቢንላደን አሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ጥርጣሬ ነበራቸው ። ዘገባው ባሳሰበው መሠረት የፓኪስታን ጦር ኃይልም ሆነ የስለላ ድርጅት ባለሥልጣናት ህዝቡንም ሆነ አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍን መንግሥት ይቅርታ መጠየቃቸውን ይጠራጠራሉ ። ዘገባው የፓኪስታን ባለሥልጣናትን በተጠያቂነት ቢከስም ጠቅላይ ሚኒስትር ሸሪፍ አሁን ጀነራሎቹን ለፍርድ የማቅረብ አቅሙ አላቸው ተብሎ አይታመንም ። የፀረ አሸባሪነት ጉዳዮች ተንታኝ ግሃፋር ሁሴን እንደሚሉት በወታደራዊ ባለሥልጣናት ውስጥ የጠፋው ወጥ አሰራርም ሌላው ችግር ነው ። « በሃገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ሥልጣን አቆናጣጭ ኃይሎች አሉ ። ሁሉም የራሳቸውን አጀንዳ ለሚያራምዱት ለተለያዩ አንጃዎቻቸው ሥልጣን ሲቀራመቱ ነው የሚታየው ። »

ሻሚል ሻምስና ገብርየል ዶሚንግዌዝ

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic