ሽብርተኝነት የጀርመን ትልቁ ሥጋት ነው፦አንጌላ ሜርክል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 31.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ሽብርተኝነት የጀርመን ትልቁ ሥጋት ነው፦አንጌላ ሜርክል

እስላማዊ ሽብርተኝነት የጀርመን ትልቁ ሥጋት እንደሆነ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተናገሩ። በአዲስ ዓመት ዋዜማ የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሽብር የማይበግራቸው ጠንካሮች እንደሆኑ ተናግረዋል።

እስላማዊ ሽብርተኝነት የጀርመን ትልቁ ሥጋት እንደሆነ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተናገሩ።  መራሒተ-መንግሥቷ ዛሬ ባደረጉት የአዲስ አመት ዋዜማ ንግግራቸው የአገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ የሚያጠናክሩ አዋጆች ገቢራዊ ለማድረግ ቃል-ገብተዋል። ተገን ጠያቂው አኒስ አምሪ በበርሊን ከተማ የገና ገበያ መካከል በጭነት ተሽከርካሪ በፈጸመው ጥቃት አስራ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። አንጌላ ሜርክል መሰል የሽብር ጥቃቶች ደኅንነት ፍለጋ መጥተው ድጋፍ እና ርዳታ በተደረገላቸው መፈጸሙ «ጎምዛዛ እና እጅግ አስቀያሚ» ነው ሲሉ ተደምጠዋል። መራሒተ-መንግሥቷ መሰል ድርጊቶች ጀርመን ለመርዳት ባላት ፈቃደኝነት እና በእውነተኛ ከለላ ፈላጊዎች ላይ የሚሳለቁ ናቸው ብለዋል።

 «ሕይወታችንን እየመራን ብሎም ተግባራችንን እያስቀጠልን አሸባሪዎችን፦በጥላቻ የተዋጡ ነፈሰ-ገዳዮች  እንላቸዋለን። ኾኖም እንዴት እንደምንኖር እና እንዴትስ መኖር እንደምንሻ እነሱ አይወስኑልንም። ግልጽ፣ ሰብአዊነት የሚሰማው እና ነጻ ሰዎች ነን። ሶሪያ ውስጥ በቦንብ ፍርስርሷ የወጣችው አሌፖ ምስል ከፊታችን እንደተደቀነ ባሳለፍነው ዓመት ሀገራችን  ከልብ የእኛን ጥላ ከለላ የሚሹትን በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ እና ከማኅበረሰቡ ጋርም እንዲዋሃዱ መርዳቷ ምን ያህል ጠቃሚ እና አስፈላጊ እንደነበር  በድጋሚ ለመናገር ይፈቀድልን።» 

ሜርክል «በርካቶች 2016ን ከዓለም ቁልቁል የመገልበጥ ሥሜት ጋር አቆራኝተውታል አሊያም ለረጅም ጊዜ ስኬቶች ተደርገው የተቆጠሩ ኩነቶች ጥያቄ ውስጥ የወደቁበት ነው» በማለት የአውሮጳ ኅብረትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ጀርመናውያን ከፅንፈኝነት እንዲርቁ ጥሪ ያቀረቡት አንጌላ ሜርክል የአውሮጳ ኅብረት የገጠሙትን በርካታ ጋሬጣዎች ለመጋፈጥ ጀርመን የመሪነት ሚና መጫወት ይኖርባታልም ብለዋል። መራሒተ-መንግሥቷ ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት መወሰኗን ከጥልቅ ቀዶ-ጥገና ጋር አወዳድረው ኅብረቱ ዘገምተኛ እና በጣም ፈታኝ ቢሆንም እንኳ አባል አገራት ከብሔራዊ ጥቅሞቻቸው በተሻገሩ የጋራ ፍላጎቶች ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ