ሻርሊ ኤብዶ እና የኒጀር ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 19.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሻርሊ ኤብዶ እና የኒጀር ተቃውሞ

በምጸታዊ ካርቱኖቹ የሚታወቀው የፈረንሳዩ ሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ ከተፈጸመበት ጥቃት ማግስት ለህትመት የበቃው እትም በዓለም ዙሪያ ቁጣን ቀስቅሷል። በድጋሚ በነብዩ መሐመድ ላይ የሚሳለቅ ምስል ይዞ ብቅ ያለው የፈረንሳይ ጋዜጣ በእስያ፤መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪቃ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሃገር ኒጀር ደግሞ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን የፈረንሳዩ ኤ.ኤፍ.ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ኒጀር በነብዩ መሐመድ በተሳለቀው የሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ ተቃውሞ 10 ሰዎች መሞታቸውን 45 አብያተ ክርስቲያናት፤ሆቴሎችና መጠጥ ቤቶች መቃጠላቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ.አፍ.ፒ. ዘግቧል።በኒጀር የኒያሜ ግዛት አምስት ሰዎች ሲሞቱ 128 መቁሰላቸውንና የክርስትና እምነት ተከታዮች ትምህርት ቤት እና ህጻናት ማሳደጊያ መቃጠላቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ የሃገሪቱን ፖሊስ ቃል አቀባይ ጠቅሶ ዘግቧል።በግዛቲቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ 90 ሰዎች መታሰራቸው ተሰምቷል።የጀርመን ዜና አገልግሎት የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 92 መድረሱን ዘግቧል።


የእለተ አርብ ጸሎትን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ቅዳሜ እና እሁድ የዘለቀ ሲሆን የኒጀር ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱ ተሰምቷል።
አምስት ሰዎች በሞቱበት እና ከ45 በላይ በቆሰሉባት የኒጀር ሁለተኛ ከተማ ዚንደር አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቤለ የሰጡ ነዋሪዎች የቻርሊ አብዶ ጋዜጣ ምስሎችን ኮንነዋል።

«ነብዩ መሐመድ ሲነኩ ራሴን አሳልፌ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። ይህ መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በጋራ የምንጸልይበት ቀን ነው። ለዚህም ነው ለነብዩ መሐመድ ያለንን ድጋፍ ለማሳየት ይህን ጊዜ የመረጥንው። በፍጹም ደስተኞች አለመሆናችንን ማሳየት እንሻለን። ወደ ቤታችን የምንመለሰውም ከነንዴታችን ነው።»«ፖለቲከኞቻችን ሙስሊሞችም አዋቂዎችም አይደሉም። 'እኔ ሻርሊ ነኝ' እያልክ 99 በመቶ ህዝብ ሙስሊም የሆነበትን ሃገር ማስተዳደር አትችልም። ማሃመዱ ኢሱፉ ከስልጣን ሊወርዱ ይገባል። ይህንን ብቻ ነው ማለት የምንችለው።»

«የቱንም ያህል ለቅኝ ገዢዎች እና ለኢምፔሪያሊዝም ብታጎበድድ እንዴትም ስልጣን ላይ ብትወጣ ነብዩን የሚያስከፋ ነገር ማድረግ የለብህም።በቅዱስ ቁርዓን ለሚያምኑ ሰዎች ውርደት ነው። ነብዩን የተዳፈረ ማንኛውም ሰው ሊሰቀል ይገባል። ይህ እስላማዊ ህግ ነው። ሌላ አማራጭ የለም።»

በጽንፈኞች ከደረሰበት ጥቃት በኋላ 7 ሚሊዮን ኮፒ መሸጡ የተዘገበው የሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ በሱዳን፤ሶማሊያ፤አልጄሪያ፤በፓኪስታን እና የሩሲያዋ ቺቺኒያ ግዛት ከፍ ያለተቃውሞ ገጥሞታል።
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic