ሺሻ፦የማይጎዳ መዝናኛ ወይስ አደገኛ እፅ? | ወጣቶች | DW | 13.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ሺሻ፦የማይጎዳ መዝናኛ ወይስ አደገኛ እፅ?

በዛሬው #77ከመቶው በተሰኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ሺሻ ማጨስን ከሰኔ ወር ጀምሮ ስለምታግደው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ጋና እና የአደንዛዥ እፅ ሱሰኞችን በመልሶ ማቋቋም ስራ ስለተሰማራው የኬንያ ማዕከል እንቃኛለን።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:23

ሺሻ ማጨስ

ሰሜን ጋና ውስጥ በምትገኘው ታማሌ ከተማ አንድ ከሰዓት በኋላ፣ ወጣት ወንዶች የማንጎ ዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበዋል።  ዛፉ ግን ለማጨስ የተሰበሰቡትን ወጣቶቹን  ከፀሀይዋ ብቻ አይደለም የከለላቸው ፤  ከአላፊ አግዳሚው ዓይን ጭምር እንጂ ይላል የዶይቸ ቬለው ማክስዌል ሱክ። የ26 ዓመቱ ሁሴን እንደነሚናገረው ወጣቶቹ የተሰበሰቡት ሲጋራ እና ሺሻ ለማጨስ እንጂ ብዙዎች እንደሚገምቱት ማሪዋና ለማጨስ አይደለም። « እኔ ሁለተኛ አዛዥ ነኝ። ይሔ ጀነራሉ ነው። እኔ ደግሞ ሁለተኛው የሺሻ አዛዥ»ወጣቶቹ ስራዬ ብለው ለማጨስ በየጊዜው ይሰባሰባሉ። ከሚያጨሱት ሺሻ  የሚወጣውን እንፋሎት በፍቅር ወደ ሰማይ ይተነፍሳሉ። ሁሴን ሺሻ ማጨስ ለምን ደስ እንደሚለው ይናገራል።« ስታጨስ የሚወጣው እንፋሎት ከሲጋራ ጪስ የበለጠ ነው ገባህ? አብዛኛውን ጊዜ የሚወጣው እንፋሎት ነው እንድናጨስ የሚማርከን ። የሚወጣውን ጭስ ስታይ ቀጥለህ አጭስ አጭስ ይልሀል።»

የታማሌ ነዋሪ ድምፁን አጥፍቶ ሺሻ ማጨስን የተቀበለው ይመስላል። በየቦታው ሺሻ የሚጨስባቸው ቦታቸው ተከፍተዋል።መጠጥ ቤቶች ውስጥ በርካቶች ሲጋራ ብቻ ቢያጨሱም አልፎ አልፎ ማሪዋና ቀላቅለው የሚያጨሱም አልጠፉም። የጋና የጤና ማዕከሎች የሺሻ አጫሹ ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ። ሺሻ የሚያጨሰውም ቁጥር መደበኛ ሲጋራ ከሚያጨሰው በ5,3 በመቶ ጨምሯል ይላሉ። ለዚህም ነው ባለስልጣናት ከመጪው ሰኔ ወር አንስቶ ሺሻ ማጨስን ለማገድ የወሰኑት። ሁሴን ግን ሺሻ ማጨስ ህገ ወጥ ሆኖ መታየት የለበትም ባይ ነው።« ሺሻ ምንም ማለት አይደለም። አያመረቅንም፣ አያፈዝም ወይም ሌላ ነገር አያደርግም። መዓዛውን ብቻ ነው የምታሸተው።»

ይሁንና በአካባቢው በሚገኘው ሆስፒታል የሚሰሩት ዶክተር አብደላ ያሀያ ሺሻ ማጨስ አደገኛ እንደሆነ ነው የሚያስተምሩት።« አመናችሁም አላመናችሁም ለጤና ጥሩ አይደለም። ለዐዕምሮአችሁ፤ ለልባችሁ፣ ለጉበት እና ለኩላሊታችሁ»የአለም የጤና ድርጅት አንድ የውኃ ሺሻ ማጨስ 100 ሲጋራዎች ከማጨስ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልፃል። እንደ ኢስማኤል ላሉ ሺሻ አፍቃሪዎች ግን የሚወዱትን ሺሻ ለማጨስ ማንኛውንም ህግ አያግዳቸውም።« ልክ ማሪዋና እንደማጨስ ነው። በህግ የተፈቀደ አይደለም። ነገር ግን ተደብቀውም ቢሆን ያጨሳሉ። ለምን? አንዳንዴ አይገባኝም ለምን አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የተለዩ ይደረጋሉ። መጨረሻ ሟቹ እኔ ራሴ ነኝ አይደል። እና ታድያ?»

ነገር ግን ሁሉም የግለሰቡ የግል ምርጫ ነው ብለው አይደመድሙም። አንዳንዶች ማሪዋና ወይም ሌሎች እፆችን የሺሻ ማጨሻው ውስጥ ይጨምራሉ። ከእፅ መውሰዱ ጋር ተያይዞም የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተጠናክረዋል። እንደ ና አብዱላሂ ያሉ ሰዎች ጉዳዩ ይበልጥ ያሳስባቸዋል።

« በየሰፈሩ እፅ የሚወሰድባቸው ጭፈራ ቤቶች እና ቦታዎች አሉ። የዚህ መጨረሻ ደግሞ አስገድዶ መድፈር፤ ስርቆት፣ የኃይል ጥቃት የመሳሰሉት ናቸው ለወጣቱ እና ላልተወለደው ልጅ መጥፎ የሆኑ ተግባራት።»ሺሻ መታገድን የሚያወድሰው አብዱላሂ ብቻ አይደለም። የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ማርክ ፓብሎም ቢሆን ማጨስ ጨርሶ መከልከል አለበት ይላል።« መከልከሉ በጣም ጥሩ ነው። ሺሻ ወጣቱን በተለይ ሴቶቻችንን አበላሽቷል።»

ጋና ሺሻን ለማገድ ቆርጣ ብትነሳም ተግባራዊነቱ አጠያያቂ ነው። ገበያው እጅጉን ተስፋፍቷል። የአንድ ሺሻ መሸጫ ሱቅ ባለቤት የሆኑት ሞሀመድ ዙቤሩ እንደሚሉት ሰው ሺሻ ለመግዛት ያለማቋረጥ ነው  ወደ ሱቃቸው የሚመጣው።« የሚያግዱት ከሆነ ንግዴን ይጎዳል።»

የጋናን አዲስ የሺሻ ህግ የሚያወድሱ እንዳሉ ሁሉ፤ መከልከሉ ይበልጥ ማህበረሰቡን ወደሌላ አይነት ችግር እንዳይከተው የሚሰጉም አሉ።

 

የእፅ ሱሰኞችን መልሶ ማቋቋም በኬንያ

የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ አደንዛዥ እፅን መዋጋት ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። ምንም እንኳን ሀገሪቱ ችግሩን ለመቆጣጠር ብትሞክርም አደንዛዥ እፆች አሁንም በቀላሉ ወደሀገሪቱ ይገባሉ። ኬንያ ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው አደንዛዥ እጽ ከ 500 000 በላይ ህዝብን ህይወት አበላሽቷል። ከነዚህም አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው።  ኡኩንዳ በተባለው ከተማ ውስጥ ግን አንድ የተስፋ ጭላንጭል ይታያል። የአደንዛዥ እፅ ሱሰኞች የመድሐኒት እና ስነ ልቦናዊ ርዳት የሚያገኙበት ተቋም ተመስርቷል። የዶይቸ ቬለዋ ዲያና ዋንዮኒ ተቋሙን ጎብኝታ እንደዘገበችው ኬንያ ውስጥ የተለያዩ አደንዛዥ እፆች በድብቅ ለገበያ ይቀርባሉ። በብዛት የሚሸጡትም ኮካኤን፣ ሄሮይን እና ሀሽሽ ናቸው። በካዋላ አውራጃ የሚገኘው  እና ቲንስ ዎች ሴንተር የተባለው የአደንዛዥ እፅ ሱሰኞች መርጃ ማዕከል ውስጥ አሌክሳ አንያንጎ ድጋፍ ታገኛለች።  ወጣቷ የሄሮይን ሱሰኛ ናት።« ሞምባሳ ነበር የምኖረው። ወደ ኡኩንዳ ስመጣ ሴተኛ አዳሪ ከሆኑ አዳዲስ ጓደኞች ተዋወቁ። ህይወቴን ከባድ ያደረገብኝ አንድ ፍቅረኛም እዚህ ተዋውቄያለሁ። ያኔ ነው ጓደኞቼ ከሄሮይን ጋር ያስተዋወቁኝ። ራሴን ለቀቅ እንዳረግ ይረዳኝ ነበር። ያን ነበር ክለቦች ውስጥ እንዳልሰራ የታገድኩት። ከዚያ በኋላ  በሴተኛ አዳሪነት መስራት ጀመርኩ።  የቾቢንጎ ጫካ እንሄድ እና አብረውን ወሲብ የሚፈፅሙ ወንዶች እንጠብቃለን። 100 የኬንያ ሺሊንግ ይከፍሉናል። አንዳንዴም 70። አማራጭ ስላልነበረን እንቀበላለን።»

አሌክሳ ሁለት «የቲንስ ዎች ሴንተር» ሰራተኞች ወደ ጫካው ሄደው ከሱሷ እንድትላቀቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉላት እና መቆያ ቦታ እንደሚሰጧት እስከሚነግሯት ድረስ እጣ ፈንተዋን ተቀብላ እየኖረች ነበር።« ለእኔና ለጓደኞቼ ያለ መከላከያ ወሲብ መፈፀም ስላለው አደጋ አብራሩልን።  ለጤና ምርመራም ወስደውኛል። ለመመገብ እና ገላን ለመታጠብ ወደዚህ መምጣት እንደምችልም ነግረውኛል። ለሌላ የጤና ምርመራም ወስደውኛል። በእውነት በጣም ነው የተባበሩኝ።»

ማዕከሉ የጤና ድጋፍ ብቻ አይደለም የሚያደርገው። ሱሰኞቹ ከጣቢያው ሲወጡ ገንዘብ ሊያገኙ የሚችሉበት የተለያዩ ሙያዎች እንዲማሩ ይደረጋል። ለቤት ሥራ የሚውል የሸክላ ሥራ እና የመሳሰሉትን ይማራሉ። ጆን ሙሬቲ ለአምስት አመታት የሄሮይን ሱሰኛ ነበር። ያለፈበትን መንገድ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል።« እፅ መውሰድ የጀመርኩት በአንድ ሀገር ጎብኚ አማካይነት ነው። ሆቴል ውስጥ አስተናጋጅ ሆኜ እሰራ ነበር። አንድ ቀን ሀገር ጎብኚው መጥቶ ሄሮይን ላገኝለት እችል እንደው ጠየቀኝ።  የሰጠኝ ገንዘብ ጠቀም ያለ ነበር። አንድ ግራም በሁለት ሺ ገዝቼ ለእሱ በ10 000 ልሸጥለት እችል ነበር። በየቀኑ ነበር የሚወስደው። ታድያ አንድ ቀን ለምን ለዚህ ሰውዬ የምሸጥለትን ነገር እራሴም አልሞክረውም አልኩ። ቀስ በቀስ ራሴም ሱሰኛ ሆንኩ። ስለዚህ ማዕከል ያወኩት እፁን የምናገኝበት ቦታ ትምህርት እና የምንወጋበት ንፁህ መርፌ ሲሰጡ ነው።  ከ«ቲንስ ዎች ሴንተር» የማረከኝ አንዱ ነገር እንዴት ከሱሰኞች ጋራ ያወሩ እንደነበር ነው። የሚጫኑ ሳይሆኑ በጣም ተባባሪ ነበሩ። ወደ እነሱ ቢሮ የሄድኩ ዕለት ህይወቴን መቀየር የጀመርኩበት እለት ነበር። »

ጆን ዛሬ በማዕከሉ ውስጥ መሰሎቹን ብቻ ሳይሆን በሚኖርበት አካባቢ ያለውን እፅ የማይወስደውን ማህበረሰብንም ያስተምራል። « በእፅ ሱሰኞች ላይ ማህበረሰቡ ያለውን አቋም መቀየር ችለዋል። ቀደም ሲል ማህበረሰቡ ሱሰኞችን መርዳት አይፈልግም ነበር። ቲንስ ዎች ግን ማህበረሰቡ እንዲረዳው አድርጓል። ሰዎች የእፅ ሱሰኛ የሚሆኑት ሆን ብለው ሳይሆን በመጥፎ ጓደኛ፣ ምን እንደሆነ ለማወቅ በመጓጓት ወይም ጭራሽ ምክንያቱን እንኳን ሳያውቁት ነው።»

ኮስሞስ ማያና ቲንስ ዎች ሴንተርን ከ 17 ዓመት በፊት ነው የመሰረቱት።« ይህ የመከላከያ መርሃ ግብር ነው። ትምህርት ቤቶች፣ መስጊዶች እና ቤተ ክርስትያናት እየሄድን ወጣቱን ስለ አደንዛዥ እፅ እናስተምራለን። ሱሰኞቹም ራሳቸውን በማይጎዱበት መልኩ እንዴት እፁን መጠቀም እንደሚችሉም እናስተምራለን። ኡኩንዳ ውስጥ ከ 3000 በላይ  የሄሮይን ሱሰኞች ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል። የቲንስ ዎች ማዕከል ሰዎች ሱሰኛ ስለመሆናቸው ምርመራ የሚያገኙበት ክሊኒክ እና ተመላልሰው ክትትል የሚያገኙበት ማዕከል አሉት።« በካዋሌ አውራጃ 3550 የሚጠጉ የሄሮይን ሱሰኞች ይገኛሉ። ራሳቸውን መርፌ የሚወጉ እና የማይወጉ ማለት ነው። ከነዚህ መካከል 1699ኙ ራሳቸውን ሄሮይን ይወጋሉ። ራሳቸውን በማይጎዳ መልኩ እንዲወጉ ንፁህ መርፌ እናቀርብላቸዋለን። እርግጥ ነው በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ግን ይህንን የምናደርገው ራሳቸውን ከHIV እንዲከላከሉ እና መርፌውን እንዳይጋሩ ስንል እንደሆነ አሁን ማህበረሰቡ ተረድቶናል። »

 

ማክስዌል ሱክ/ዲያና ዋንዮኒ/ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች