ሶርያ፤ የፀጥታዉ ምክር ቤትና ሩሲያ | ዓለም | DW | 21.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሶርያ፤ የፀጥታዉ ምክር ቤትና ሩሲያ

ሩሲያ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ሶርያ ላይ በሚያደርገዉ ግፊት እንደምትተባበር ፍንጭ ሰጠች። የሐገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የፀጥታዉ ምክር ቤት የሶርያን ሁኔታ ከግምት ያስገባ መግለጫ ዛሬ ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ 15 አባላት የመንግስታቱ ድርጅትና የአረቡ ሊግ ሶርያን ከእርስ በርስ ጦርነት እንዲያድኑ ለሰላማዊ መፍትሄ የሾማቸዉ ልዑክ ኮፊ አናንን ተልዕኮ እንደሚደግፉ በመግለፅ ሶርያ አናን የሚያቀርቡትን ሰላማዊ የመፍትሄ ሃሳብ እንድትቀበል ጠይቀዋል። የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት የሶርያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ለመግታት የሚወስደዉን የኃይል ርምጃ ቢቃወምም አባላቱ በአንድነት ቆመዉ የጋራ መግለጫ ለማዉጣት ጊዜ ፈጅቶበታል። ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸዉን ዉሳኔዉን ለመፃረር ለወትሮዉ የሚጠቀሙት ሩሲያና ቻይና የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ ባደረጉት ዉይይት የመስማማት አዝማሚያ አሳይተዋል።

Außenministertreffen in Berlin Westerwelle Lawrow Sikorski

የጀርመን፤ ሩሲያና የፖላንድ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

ዘገባዎች እንዳመለከቱትም 15ቱም የምክር ቤት አባላት የተመድና የአረብ ሊግ የሶርያን ግጭትና የኃይል ርምጃ አስቁሞ ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ የሰየማቸዉ ልዑክ የቀድሞዉ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናንን ተልዕኮ ለመደገፍ ተስማምተዋል። በጋራ ባወጡት መግለጫም የሶርያ መንግስት ከኃይል ርምጃዉ ታቅቦ አናን የሚያቀርቡትን ሰላማዊ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲቀበል ጠይቀዋል። በርሊን ላይ ትናንት ከጀርመንና ከፖላንድ አቻዎቻቸዉ ጋ ጉዳዩን አንስተዉ የተወያዩት የሩሲያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የሶርያን ወቅታዊ ሁኔታ በማንፀባርቅ የአናንን ተልዕኮ የሚደግፍ ዉሳኔ ከምክር ቤቱ ከወጣ አገራቸዉ የአቋም ለዉጥ እንደምታደርግ ጠቁመዉ ነበር።

«ሂደቱን በደስታ እንቀበለዋለን። የእኛ ተጓዳኝነት ሁኔታዉን የሚረዳ ከሆነ አቋማችንን ቀይረናል። በፈጣሪ ስም! ዋናዉ ነገር ለጉዳዩ መርዳቱ ነዉ።»

ሩሲያ ሶርያን በሚመለከት የያዘችዉን አቋም መለወጧን ብታሳዉቅም ወታደራዊ ጣልቃገብነት የሚለዉን ፈፅማ እንደማትደግፍ አሁንም ይፋ አድርጋለች። የድጋፏ ትኩረት ሰብዓዊ ርዳታ ለተጎጂዉ የሶርያ ህዝብ የሚገባበት ስልት እንዲቀየስ የሚል ሲሆን ከምንም በላይ ከፀጥታዉ ምክር ቤት የሚወጣዉ ዉሳኔ የኮፊ አናንን ሃሳብ በግልፅ ማካተት እንደሚኖርበት ላቭሮቭ አፅንኦት ሰጥተዋል፤

«ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች መኖር አለባቸዉ። የመጀመሪያዉ የኮፊ አናን አስተያየት ግልፅ መሆን አለበት። ሁለተኛ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ ቀነገደብ ያለዉ መሆን የለበትም። ዉሳኔዉ ሂደትን የሚያስገነዝብ መሆንም አለበት። ሁሉንም የሶርያ ኃይላት፤ መንግስትንና የተቃዋሚ ኃይሎችን በሙሉ የሚያካትት እንዲሆንም መሠረቱ የኮፊ አናን የመፍትሄ ሃሳብ መሆን አለበት።»

ዛሬ ሩሲያን እና ቻይናን አካቶ የወጣዉ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ ሶርያ የኮፊ አናንን የመፍትሄ ሃሳብ በመቀበል ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ ቀጣይ ርምጃ ሊኖር እንደሚችል አጠንቅቋል። የሚወሰደዉን ርምጃ ምንነት ግን መግለጫዉ ግልፅ አላደረገም። አናን ለሶርያ መንግስት የሚያቀርቧቸዉ ስድስቱ የማግባቢያ ነጥቦችም ዛሬ ኒዉዮርክ ላይ እንደሚዘጋጁ ዲፕሎማቶች አመልክተዋል። ሩሲያ ባቀረበችዉ ጥያቄ መሠረትም በምዕራባዉን ሐገሮች የተዘጋጀዉ ረቂቅ የጊዜ ገደቡ ተነስቶ በአርትኦት እንደሚስተካከል ተጠቁሟል። እንዲያም ሆኖ ዲፕሎማቶች ኃያላኑ መንግስታት በጋራ የተስማሙበት የመፍትሄ ሃሳብ ስልጣን ላለመልቀቅ ለሚሟሟቱት የሶርያ ፕሬዝደንት ባሽር አልአሰድ ቀላል ጫና እንደማይሆን ገምተዋል። ሶርያ ዉስጥ ፀረ መንግስት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ ወደስምንት ሺህ ህዝብ አልቋል። የመንግስት ኃይሎች የሚሰነዝሩትን የኃይል ርምጃ አጠናክረዉ ዛሬም ሆምስ ከተማን በጦር መሳሪያ መደብደብ መቀጠላቸዉን የመብት ተሟጋቾች አመልክተዋል።

ክርስቲና ናግል

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic