ሶሪያ፤ የስድስት ዓመት ጥፋት | ዓለም | DW | 13.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሶሪያ፤ የስድስት ዓመት ጥፋት

ታሬክ አል ጠይብ መሐመድ ቡአዚዚ ለቱኒዚያ ከነበረ፤ሙዓዉያ ሲያስኔ በርግጥ የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅ አቀጣጣይ ነበር።ሕዝባዊ አመፁ  ግን እንደ ቱኒዚያ ሕዝባዊነቱን ይዞ አልቀጠለም።ባፍታ ወደ ነፍጥ ግጭት-ወደለየለት ጦርነት ተለወጠ እንጂ።ያ ወጣትም ተዋጊ ሆነ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:59

ሶሪያ፤ የስድስት ዓመት ጥፋት

 

«አባትሕ ያዉቁ ነበር?» ጠየቀዉ ጋዜጠኛዉ የደርዓዉን ወጣት።«አዎ» አጭር መልስ።«ምን አሉሕ» 
                      
«ለምን ፃፍክ አለኝ? አደረግ ነዉ አልኩት።ከዚያ ተደበቅ አለኝ።ፈርቶ ነበር።» ሙዓዉያ ሲያስኔ።ከጓደኞቹ ጋር ያደረገዉን ሲያደርግ የአስራ አራት ዓመት ወጣት ነበር።የአባቱ ፍራቻም ተገቢ ነበር።የዚያ ወጣት እና የጓደኞቹ ድርጊት፤ የአባትዬዉ ፍርሐትም ሶሪያን የሚያጠፋ፤ ሶሪያዎችን የሚያጫርስ፤ አረቦችን የሚያናጭ፤ ኃያላንን የሚያጋጭ መዘዝ ያስከትላል ብሎ ያሰበ፤የጠረጠረ፤የገመተም አልነበረም።ግን ሆነ።ከነገ-ወዲያ ሮብ ስድስተኛ ዓመቱ።
                  
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶሪያ ላይ እስካሁን የተሳከለት አንድ ሥራ አግኝቷል።ዓመት ያሰላል።አስከሬን ስደተኛ ይቆጥራል።ሮብ-ስድስተኛ ዓመቱ።ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዉ አልቋል።አስራ-ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ አንድም ተሰድዷል አለያም ተፈናቅሏል።ከስደተኞቹ  ከ2,8 ሚሊዮን የሚበልጡት፤

ከሟቾቹ አራት ሺሕ ያሕሉ  ሕጻናት ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎች ነበሩ።አብዛኞቹ ሕፃናት ወይም ታዳጊዎች የተገደሉት ትምሕርት ቤት ወይም ትምሕርት ቤት አጠገብ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ከግማሽ የሚበልጠዉ ሶሪያዊ ልጁን ትምሕርት ቤት አይልክም።እሱም በ2011  የ14 ዓመት ወጣት ነበር።የደርዓ ከተማ ነዋሪ።የሰባተኛ ክፍል ተማሪ።ሙዓዉያ ሲያስኔ።
                                   
«ግብፅ እና ቱኒዚያ የሆነዉን እናይ ነበር።ከዚያ ትምሕርት ቤታችን ዉስጥ ተሰበሰብን፤ ቀለም ፈለግን እና ትምሕርት ቤቱ ግርግዳ ላይ ፃፍን።»
የካቲት ማብቂያ ነበር 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ግራፍቲ  ይሉታል ፅሁፉን። መልዕክቱ ግን አደገኛ ነበር።«አሁን የርስዎ ተራ ነዉ ዶክተር አሰድ» ይላል ሙአዉያ የፃፈዉ።ሌሎች

እየተቀባበሉ በመላዉ ዓረብ ሐገር የተዛመተዉን መፈክር ፃፉ። «ሕዝቡ  ሥርዓቱን ማስወገድ ይፈልጋል።» እያሉ።
 መፈክሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማ-የተፃፈዉ ቱኒዝ-ነበር።መልዕክቱ በትክክል ተሳክቷልም።ግብፅ ተደገመ።ጄኔራል አልሲሲ እስኪደፈልቁት ድረስ የቱኒዞችን መስሎ ነበር።ሊቢያ አሰለሰ።የዉጪ ሐይላት ጣልቃ ገብተዉበት በዕልቂት ፍጅት አሳረገ።
የየመን ሕዝባዊ አመፅም እንደቱኒዚያ ጀምሮ-እንደ ግብፅ አዝግሞ እንደ ሊቢያ ሆነ።የሶሪያ ለብቻዉ ነዉ።የሙዓዉያ አባት ገና ያኔ ፈርተዋል።የፈሩት ለልጃቸዉ ደሕንነት ነበር።ልጃቸዉ ለጊዜዉ ተሰወረ።ሰወስት የቅርብ ጓደኞቹን ጨምሮ አስራ-አምስት የትምሕርት ቤት ባልንጀሮቹ ግን ታሰሩ።ተገረፉ።አንዱ በዱላ ብዛት ሞተ።የደማስቆ ሕዝብ ደርዓ ላይ የደረሰዉን ሲሰማ የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለመቃወም የግልብጥ ብሎ አደባባይ ወጣ።
                                  
ሶሪያዊዉ ደራሲ ሎኡይ አል-ሁሴይን የዚያን ቀን ነበር «ሶሪያም ሕዝባዊ አመፅ የሚደረግባቸዉን የአካባቢዉን ሐገራት ተቀየጠች» ብለዉ የፃፉት።ታሬክ አል ጠይብ መሐመድ ቡአዚዚ ለቱኒዚያ ከነበረ፤ሙዓዉያ ሲያስኔ በርግጥ የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅ አቀጣጣይ ነበር።ሕዝባዊ አመፁ  ግን እንደ ቱኒዚያ ሕዝባዊነቱን ይዞ አልቀጠለም።ባፍታ ወደ ነፍጥ ግጭት-ወደለየለት ጦርነት ተለወጠ እንጂ።ያ ወጣትም ተዋጊ ሆነ
አረቦችን በሐይማኖት ሐራጥቃ ሱኒ-ሺዓ ብሎ፤ ፋርሶችን ከአረቦች ከፍሎ፤ ቱርኮችን ከኩርዶች፤ ኩርዶችን ከአረቦች ነጣጥሎ፤ ሐያላንን ምዕራብ-ምሥራቅ አሳድሞ የሚያዋጋዉ ጦርነት የተፋላሚዎችን ዓላማ እና ምክንያት በግልፅ ለማወቅ እንኳ አዳጋች ደረጃ ላይ ደርሷል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በሶሪያዉ ጦርነት ከሰላሳ የሚበልጡ አማፂ ቡድናት፤

ከሃያ በላይ መንግሥታት ጎራ ለይተዉ ይዋጋሉ።በጦርነቱ በቀጥታ ከሚካፈሉት በተጨማሪ ከ20 የሚበልጡ መንግሥታትና ድርጅቶች ተፋላሚ ኃይላትን ይደግፋሉ።የአንድ ሐገር ጦርነት ይሕን ያሕል ቡድናት ወይም መንግሥት ሲያስልፍ የሶሪያዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።ጦርነቱ ያሰደደና ያፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ትይቶ አይታወቅም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለጦርነት ሠላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ከቀድሞዉ ዋና ፀሐፊዉ ኮፊ አናን እስከ እዉቅ ዲፕሎማቱ ላሕዳር ብራሒሚ በአደራዳሪነት ሰይሞ ነበር።ሁለቱም ተልዕኳቸዉን «በበቃኝ» አቆሙ።ሐምሌ 2014 የልዩ መልዕክተኝነቱን ሥልጣን የያዙት ስታፋን ደ ሚስቱራ የሶሪያ ተፋላሚ ኃይላት ተወካዮችን ለማደራደር ያደረጉት ጥረትም ጊዜ እና ገንዘብ ከማባከን ባለፍ እስካሁን ለዉጤት አልበቃም።
ከቪየና-ጄኔቭ፤ ከአንካራ-በርሊን ሲሽከረከር ዓመታት ያስቆጠረዉ ድርድርና ቅድመ ድርድር ከአስር ቀን በፊት ጄኔቭ ላይ የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮችን ፊት ለፊት ሲያገጣጥም የስድስት ዓመቱ ዲፕሎማሲ የተስፋ ጭላንጭል የፈነጠቀ መስሎ ነበር።ዋና አደራዳሪዉ፤ የዓለም አቀፉ ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ደ ሚስቱራ የሰጡት መግለጫም ጭላንጭሉን የሚያደምቅ ነበር።
                           
«ይሕ ፎቶ ዝም ብሎ ዉብ ፎቶ ብቻ አይደለም።ከፍተኛ ተምሳሌታዊ ጭምር እንጂ።ይሕ ልዩ አጋጣሚ ነዉ።ከሶሪያዉ ጦርነት ጋር የተነካኩ በሙሉ አንድ አዳሽ ዉስጥ መቀመጥ መቻላቸዉን መላዉ የሶሪያ ሕዝብ እንዲገነዘብ ያደረገ አጋጣሚ ነዉ።ተወካዮቹ አንድ አዳራሽ ተቀምጠዉ መፍትሔ ለማምጣት እንዴት መቀጠል እንዳለባቸዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሰጠዉን ሐሳብ ያደመጡበት አጋጣሚ ነዉ።ግልፅ አጀንዳ አለን ብዬ አምናለሁ።ከሶሪያ መንግስት ጋር በሚደረገዉ ድርድር ተቃዋሚዎችን የሚወክል አንድ መልዕክተኛ ለመሰየም የሚረዳ መሰረት ተጥሏል።»
ጅምሩ በስድስትተኛ  ዓመቱም  ቢሆን በርግጥ ጥሩ ነዉ ። በስድኛ ዓመቱ   ዘንድሮም መንግሥትን የሚወጉ ተፋላሚዎች አንድ ለመሆን ገና መግባቢያ መሠረት ላይ እንኳ አለመድረሳቸዉ እንጂ ግራዉ።ግራዉ እዉነትም ከመገናኛ ዘዴዎች ያፍታ ዘገባ በኋላ አለመቀጠሉ በርግጥ «እንቆቅልሽ» እንጂ ምን ይባላል።
ከአስር ቀን በፊት

ጄኔቭ ዉስጥ ከተደረገዉ ስብሰባ በፊት አስታና-ካዛክስታን ዉስጥ ሌላ ግን ተመሳሳይ ድርድር ነበር።የሶሪያ መንግስትን  የሚደግፉት ሩሲያና ኢራን፤ የሶሪያ መንግስት ተቃዋሚዎችን ከምትደግፈዉ ቱርክ ጋር ሆነዉ ባዘጋጁት የመጀመሪያ ዙር ድርድር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ስታፋን ደ ሚስቱራ ተገኝተዉ ነበር።
በሁለተኛዉ ዙር ድርድር ላይ ግን ደ ሚስቱራ አልተካፈሉም።ደ ሚስቱራ በድርድሩ ላለመገኘታቸዉ በይፋ የተሰጠዉ ምክንያት የጄኔቫዉን ድርድር ለማዘጋጀት ጊዜ ሥለሚያጥራቸዉ የሚል ዲፕሎማሲያዊ ሰበብ ነበር።ከሰበቡ ጀርባ ያለዉ እዉነት ግን የአስታናዉን ድርድር ምዕራባዉያን መንግሥታት አለመደገፋቸዉን ጠቋሚ ነዉ። 
የሶሪያ ተፋላሚ ኃይላት እስከ መጋቢት 20 ድረስ ፤ ቢያንስ በተወሰነ አካባቢ ዉጊያ እንዲያቆሙ ያስማማዉ ግን የጄኔቩ ሳይሆን የአስታናዉ ድርድር ነበር።የጄኔቩ የመጨረሻ ድርድር የተፋላሚ ኃይላት ተወካዮችን ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ አዳራሽ አስቀምጦ ፎቶ ግራፍ ባስነሳ ሳልስት አብቅቷል።
ተፋላሚ ኃይላት በአስታናዉ ድርድር ያደረጉትን የተኩስ አቁም ዉል  ሙሉ በሙሉ እንዲያከብሩ ለማግባባት የሚደረገዉ ጥረት እንደሚቀጥል የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈዉ ቅዳሜ አስታዉቀዋል።የዩናይትድ ስቴትስን ድጋፍ ጠይቀዋልም።
«ከጥንቃቄ ጋር አወንታዊ ተስፋዬን መግለፅ እወዳለሁ።የጋራ ጥረታችንን በማጠናከርና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ ኃይላትን በማሳተፍ የሶሪያዉን የተኩስ አቁም ዉል ዉጤታማ እንዲሆን ማጠናከር እንችላለን።በዚያ ላይ በመመስረትም ወደ ሙሉ ፖለቲካዊ መፍትሄ እናመራለን።»


ፑቲን ሞስኮ ዉስጥ እንግዳቸዉን፤ የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻንን ከጎናቸዉ አስቀምጠዉ ሥለ ሶሪያ ተኩስ አቁም ሲናገሩ የሶሪያ መንግሥት ጦርና አማፂን ባርዛ፤ አል ቁባኒ እና ቲሽራ የተባሉትን አካባቢዎች ለመያዝና ላለመስያዝ በታንክ፤ በመድፍ-አዳፍኔ ይቀጣቀጡ ነበር።የሶሪያ መንግስት ተቃዋሚዎችም ለነገ-በተቀጠረዉ 3ኛ ዙር ድርድር ላይ ለመካፈል ወደ አስታና እንደማይሔዱ አስታወቁ።
የፑቲን ጥንቃቄ ያልተለዉ ተስፋ ከሞስኮ በተሰማ ማግስት ደማስቆ በቦምብ ፍንዳታ ተሸበረች።በደም አበላ ጨቀየች።ከአርባ በላይ ነዋሪዎችን ቀበረች።ስድስተኛ ዓመቷ ሮብ ትዘክራለች። 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic