ሶሪያ፤ ሠላም የራቃት ምድር | ዓለም | DW | 02.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሶሪያ፤ ሠላም የራቃት ምድር

አርሚያዎች-ኤብላዎችን፤ ባቢሎኖች አርሚያዎችን፤ አሞርቲዎች ባቢሎኖችን፤ ግብፆች ሚታኒዎችን፤ አሰሪያዎች ግብፆችን፤ ሮሞች-ግሪኮችን አረቦች ሮሞችን፤ ቱርኮች አረቦችን፤ አዉሮጶች ቱርኮችን ሲያስገብሩባት አሌፖ-ጀግና ወልዳ ጀግና ቀብራለች።እየተገነባች ወድማለች።እየፈረሰች ተገንብታለች።አምስት ሺሕ ዓመት።ዛሬም ያዉናት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:05
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:05 ደቂቃ

ሶሪያ፤ ሠላም የራቃት ምድር

ርዕሠ-መንበሩን ለንደን ብሪታንያ ያደረገዉ የሶሪያ ጉዳይ ታዛቢ ድርጅት የበላይ ራሚ አብድረሕማን «የሶሪያዉን ጦርነት ለማሸነፍ ይሁን ሠላም ለማዉረድ ቁልፏ አሌፖ ናት።» አሉ ባለፈዉ ሳምንት።የፖለቲካ ተንታኝ ፋብሪስ ባላንቼም አጠናከሩት።«በሽር አል አሰድ የሶሪያ ፕሬዝደንት መሆን ከፈለጉ አሌፖን መቆጣጠር አለባቸዉ።» ብለዉ።ያቺን ለም፤ሐብታም ሥልታዊ አካባቢን ለመቆጣጠር ኤብላዎች፤ባቢሎኖች፤አሞርቲዎች፤አሲርያዎች፤ ግሪኮች፤ሮሞች፤ሞንጎሎች፤አረቦች፤ቱርኮች፤ አዉሮጶች እየገነቡ እንዳፈረሷት፤ እያፈረሱ እንደገነቧት 5000 ዘመናት አስቆጥራለች።ዛሬም አረቦች፤ኩርዶች፤ ቱርኮች፤ፋርሶች፤አዉሮጶች፤አሜሪካኖች፤ ሩሲያዎች ይገድሉ፤ይጋደሉ-ያጋድሉባታል።አሌፖ ወይም ኻላብ-እንደ ጥንት ጌቶቿ።የአሌፖን ጥፋት አስታከን የሶሪያዉን ጦርነት ላፍታ እንቃኛለን።

ዶክተር መሐመድ ዋሲም መዓዝ ዉሎ አዳራቸዉ አንድም አዲስ ከተወለዱ አለያም ቦምብ፤ ጥይት፤ፍርስራሽ ካቆሰላቸዉ ሕፃናት ጋር ከሆነ ከረመ።አንዱን አክመዉ ተንፈስ ሲሉ ሌላዉ ይተካል።የተንዠረገገዉ ጢማቸዉ፤ አዳፋ ልብሳቸዉ፤ የተጨራመተ ጫማቸዉ ፈላስፋ ወይም ደራሲ እንጂ ሐኪምነታቸዉን ይቃረናል።

ተወልደዉ ያደጉት አሌፖ ነዉ-ኻላብ።ትምረዉ-የሠለጠኑት-አሌፖ።አግብተዉ ወልደዉ የከበዱት-አሌፖ።የሚሠሩት አሌፖ።ጦርነት፤ እልቂት፤ ፍጅቱ ሲከፋ ቤተሰቦቻቸዉን ወደ ቱርክ አሻገሩ።እሳቸዉ ግን የዚያችን ዉብ ከተማ ጥፋት ምንም የማያዉቁ ሕፃናቷን እልቂት እያዩ እንዴት ጥለዋት ይዉጡ።

«ዶክተር መዓዝ እዚሕ ጀሐንብ ዉስጥ ካሉ ጥቂት ሐኪሞች አንዱ-እና ምርጡ የሕፃናት ሐኪም ነበር።» ይላሉ የመዓዝ አለቃ ሐቲም (ሙሉ ስማቸዉ መጠቀሱን አልፈለጉም)

ባለፈዉ ሳምንት ሮብም ዶክተር መዓዝ ከሐቲም ጋር ሲሰሩ ዉለዉ ማምሻ ተለያዩ።ወዲያዉ ግን አስቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገዉ በሽተኛ በመምጣቱ ተጠሩና አል-ቁዱስ ሆስፒታል ገቡ።መሽቷል።ጢማሙ ዶክተር አልጋላይ የተንጋለለችዉን ሕፃን ሕይወት ለማዳን አቀርቅረዉ ልጅቱን እያገለባጡ ይመረምራሉ።

ከላይ፤ ከጠራዉ በላይ፤ ከዚያም በላይ ከሩቅ መዓቱ ወረደ።ሐኪሙም፤ ረዳቶቻቸዉም፤ ታካሚዋም-መዓሠላማ።አዲዮስ።ለቀሪ ዎች ሌላ ዋይታ-ሲቃ።አሌፖ።«እምላለሁ ፈጣሪ ይጥለዋል።እናስወግደዋለን።እናስወግደዋለን።ይሕ ቤታችን ነዉ።እዘኑልን።ኢራን ሐገራችንን ልትቀማን ትፈልጋለች።አንሰጣቸዉም።እስከ መጨረሻዉ ደም ጠብታ ድረስ ከዚሕ አንሔድም።»

ጥንት፤ አርሚያዎች-ኤብላዎችን፤ ባቢሎኖች አርሚያዎችን፤ አሞርቲዎች ባቢሎኖችን፤ ግብፆች ሚታኒዎችን፤ አሰሪያዎች ግብፆችን፤ ሮሞች-ግሪኮችን አረቦች ሮሞችን፤ ቱርኮች አረቦችን፤ አዉሮጶች ቱርኮችን ሲያስገብሩባት አሌፖ-ጀግና ወልዳ ጀግና ቀብራለች።እየተገነባች ወድማለች።እየፈረሰች ተገንብታለች።አምስት ሺሕ ዓመት።ዛሬም ያዉናት።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የዛሬዎቹን ሶሪያና ሊባኖስን ከኦስማን ቱርኮች የማረኩት ፈረንሳዮች አገዛዛቸዉ እንዲቀጥል ሶሪያን በየግዛቱ መሽንሸንን እንደ ጥሩ ብልሐት ነበር ያዩት።አካባቢዉን የሚቆጣጠረዉ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሔንሪ ዦሴፍ ጉራዉድ የሶሪያን ነፃነትና አንድነት የሚያቀነቅኑ የሐገሬዉ ተወላጆችን ፍላጎት ለመቅጨት አሌፖን መገንጠል ቀዳሚዉ ዓላማቸዉ አደረጉት።

ጄኔራሉ ዕቅዳቸዉን ከግብ ያደርሳሉ ያሏቸዉ ሐይላት በቅጡ መደራጀታቸዉን ካረጋገጡ በኋላ የአሌፖን መስተዳድር አፍርሰዉ በ1925 (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) አዲስ ምርጫ ጠሩ። ፈረንሳዮች፤ አሌፖን ከሌላዉ የሶሪያ ግዛት ይገነጥሉልናል ብለዉ ፍራንክ ሲያንቆረቁሩላቸዉ ከነበሩት አብዛኞቹ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ አቋማቸዉን ለዉጠዉ የአንድነት ሐይሎችን መረጡ።

በምርጫዉ ዉጤት በጣሙን በመታለላቸዉ የበገኑት ፈረንሳዮች በርካታ የአሌፖ ነዋሪዎችን አጋዙ፤ አሠሩ፤ ከሥራ አባረሩም።አሌፖ ግን-ሶሪያ፤ ሶሪያም አሌፖ እንደሆነች ቀጠለች።በ2012 እንደ የፕሬዝደንት በሽር አል አሰድን መንግሥት የሚዋጉት ሐይላት የአሌፖ ግዛትን በተለይ ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።ወዲያዉ ግን አብዛኛዉን የከተማይቱን አካባቢ የመንግሥት ጦር መልሶ ተቆጣጠረዉ።

አንዱ ሌላዉን እያባረረ ወይም እየገደለ ከተማይቱን በተቆጣጠረ ቁጥር ያለ ጥፋቱ የሚሠደድ፤ የሚገደል፤ የሚቆስለዉ አሌፖዊ ቁጥር ከልክ እያለፈ ነዉ።የሶሪያዉ ጦርነት ሲጀመር አሌፖ 2,5 ሚሊዮን ነዋሪዎች ነበሯት።አሁን አንድ ሚሊዮን ነዉ የቀራት። ባለፈዉ ሳምንት ተረኞቹ እነ ዶኮተር መዓዝ ሆኑ።ከዶክተሩ ጋር አንድ የጥርስ ሐኪም፤ ሰወስት ነርሶች እና ሐያ-ሁለት ሕመምተኞች ወይም አስታማሚዎች ተገድለዋል።

በእስካሁኑ ጦርነት ጥንታዊ አብያተ-መንግሥታት፤ በኡመያዶች ዘመን የተገነባዉን ዝነኛ መስጊድን ጨምሮ በርካታ መሳጂዶች፤ አብያተ-ክርስቲያናት፤ ምኩራቦች፤ ትምሕርት ቤቶች ወድመዋል።ባለፈዉ ሮብ ተረኛዉ አል-ቁዱስ ሆስፒታል ሆነ።«አሁንም አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች የሕክምና ተቋማት አሉ።የማወለጃ ማዕከል ይሕ ነበር።ሕፃናት ልዩ የሕፃናት ሐኪም የሚያገኙትና የሚታከሙበት ሥፍራ ይሕ ነበር።አሁን ግን የፍርስራሽ ክምር ሆኗል።ሌላ አማራጭ መፈለግ አለባቸዉ።ምን ያሕል አማራጭ እንዳለ ግን አላዉቅም።»

ይላሉ ሆስፒታሉን የሚያስተዳድረዉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ድርጅት ሐላፊ።አሌፖ በርግጥም የፖለቲካ አዋቂዉ እንዳሉት የሶሪያ ጦርነትም፤ የሠላምም ቁልፍ ሳትሆን አልቀረችም።ሶሪያ ዉስጥ የሚፋለሙ ወገኖች በሙሉ አሌፖ ዉስጥ አሉ።የመንግሥት ጦር፤ አል-ኑስራን የመሳሰሉ ፅንፈኛ ቡድናት፤ ኩርዶች፤ በምዕራባዉያንና በአረቦች የሚደገፉት ደፈጣ ተዋጊዎች ከተማይቱን ተቀራምተዋታል።

ሸባሪ ከሚባሉት ቡድናት ዉጪ ያሉት የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላት በዩናይትድ ስቴትስና በሩሲያ መልካም ፈቃድ ባለፈዉ የካቲት ያደረጉት ተኩስ አቁም ለዘላቂ ሠላም የመጀመሪያዉ ተስፋ ተደርጎ ነበር።ተስፋዉ ግን ከተስፋ አላለፈም።ባለፈዉ ሳምንት አሌፖ፤ ላታኪያና ደማስቆ አካባቢ ያገረሸዉ ጦርነት በቅጡ ያልፀናዉ ተኩስ አቁም ጨርሶ እንዳይፈርስ አስግቷል።

የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች የሚያደርጉት ድርድርም ደንበር፤ ገተር፤ እያለ ነዉ።ዋና አደራዳሪ ስቴፋን ደ ሚስቱራ ተደራዳሪዎችን የሚያስማማዉ የሶሪያ ሕዝብ-ስቃይ-ሰቆቃ ሳይሆን የሐያላኑ ቁጣ፤ ግልምጫና ጫና መሆኑን ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።

«ሥለዚሕ የዩኤስ-ሩሲያ ከፍተኛ አመራሮች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልጉ አመለክታለሁ።ምክንያቱም የፕሬዝደንት ኦባማ እና የፕሬዝደንት ፑቲን የከዚሕ ቀደም ልዩ እርምጃ ጥሩ ጅምር ማሳያቱ አይዘነጋም።እንዳጀማመሩ ሁሉ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቅ አለበት።»የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ አምስተኛ ዓመቱን በደፈነዉ ጦርነት ከ450 ሺሕ በላይ ሰዉ አልቋል።270 ሺዉ ሠላማዊ ሰዉ ነዉ።ከአራት ሚሊዮን በላይ ተሰድዷል።ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጥ ተፈናቅሏል።በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብትና ንብረት ወድሟል።እስካሁን ግን አሸናፊም ተሸናፊም የለም።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ እንዳሉት ደግሞ ከዚሕ በኋላም ቢሆን በጦርነቱ አሸናፊ እና ተሸናፊ መለየቱ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ጥፋቱን ለማስቆምም ከድርድር የተሻለ መፍትሔ የለም።

«ሶሪያ ዉስጥ ያለዉ አሳዛኝ ሰብአዊ እልቂት በጣም ያሳስበናል።እልቂቱን በየዕለቱ እየተከታተልኩት ነዉ።በየቀኑ አነባለሁ።እዚያ ምን እየሆነ እንደሆነ ጥፋት-ስቃዩ ካጋጠማቸዉ ወይም ካዩ ሰዎች እንሰማለን።ከኔቶ ሸሪካችን ቱርክ ጋር ይህን ሁኔታ ሥለምንለዉጥበት መንገድ በየጊዜዉ እየተወያየን ነዉ።እንደምታዉቁት ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ ተኩስ አቁሙ ሥለሚቀጥልበት መንገድ ፕሬዝደንት ፑቲንን አነጋግሬያቸዉ ነበር።የፖለቲካዊዉ ድርድር መቋርጥ እንደሌለበትም ተነጋግረናል።»

ሁለቱ ሐያላን በመግባባታቸዉ ደማስቆና ላቲካን በመሳሰሉ አካባቢዎች ያገረሸዉን ጦርነት የመንግሥት ጦር ማቆሙን አስታዉቋል።ጦርነቱ የሚቆመዉ ግን በጣም ቢረዝም ለ72 ሰዓታት ነዉ።አሌፖ ከተማ ግዛት የሚደረገዉን ዉጊያ ግን እንደቀጠለ ነዉ።

ትናንት ዤኔቭ-ስዊትዘርላንድ የገቡት የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ዛሬ የሳዑዲ አረቢያዉን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አድል አል ጀባርንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ስቴፋን ደ ሚስቱራን አነጋግረዋል።

ኬሪ ከንግግሩ በኋላ እንዳስታወቁት ባለፈዉ የካቲት የታወጀዉ ተኩስ አቁም እንዲፀና የተለያዩ ሐሳቦችን እያሰባሰቡ ነዉ። ዛሬ ማታ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ከሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በሥልክ ከተነጋገሩ በኋላ የሚስማሙበትን ሐሳብ ያስታዉቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኬሪ ጥረት፤ ፕሬዝደንት ኦባማ ከአስር ቀን በፊት እንዳሉት የሶሪያዉን ጦርነት በድርድር ለማስቆም መቁረጣቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ የሚል አስተያየት አስከትሏል።ይሁንና ኦባማ ዉጪ ጉዳይ ሚስትራቸዉን ወደ አዉሮጳ በላኩበት ማግሥት ዛሬ 250 ተጨማሪ ወታደሮቻቸዉን ወደ ሶሪያ አዝምተዋልም።

«የእግረኛዉን ጦር ዉጊያ ለሚሩ አይደለም።ISLን የሚዋጉ የሐገሬዉን ሐይላት ለማሠልጠንና ለመርዳት ግን በጣም ወሳኝ ናቸዉ።»ወታደርና ዲፕሎማት።ዉጊያና ድርድር።ጦርነትና ሠላም።የአሜሪካኖች መርሕ።የሶሪያዎች እልቂት።ማብቂያ ይኖረዉ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች