ሶሪያና የኮፊ አናን ሽምግልና፣ | ዓለም | DW | 28.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሶሪያና የኮፊ አናን ሽምግልና፣

የሶሪያው ርእሰ-ብሔር በሺር አል አሰድ፤ ሽምግልናውን ሊቀበሉ ይሆን? የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልእክተኛ ኮፊ አናን ትናንት ቤይጂንግ ላይ እንዳስታወቁት፤ የአርስ በርስ ውጊያ ለሚያምሳት ሶሪያ ይበጃል ተብሎ የታሰበውን፤ ዓለም አቀፉን ባለ 6

ነጥብ የሰላም አቅድ አሳድ ተቀብለዋል ። የተከፋፈለው የሶሪያ የተቃውሞው ወገን፤ ኢስታንቡል ፤ቱርክ ውስጥ በመሰብሰብ፤ ያቋቋመው ፣ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘው የተቃውሞው ወገን ብቸኛ ወኪል ይሆን ዘንድ ለመቀበል መምከሩ ነው የተገለጠው። ውጊያው አሁንም ሶሪያ ውስጥ እንደቀጠለ በመሆኑ ፤ የኮፊ አናን ሽምግልና የሚሠምር መሆኑን የተቃውሞው ወገን በጥርጣሬ ዓይን ነው የተመለከተው። የዶቸ ቨለ ባልደረባ Jürgen Stryjak ያቀረበውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ትናንት ከቀትር በፊት ፤ በደማስቆ መዳረሻ፤ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱ በተነገረ በጥቂት ሰዓቶች ልዩነት፤ የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሺር አል አሰድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ኮፊ አናን ያቀረቡትን የሰላም አቅድ ተቀበሉት የሚል አስገረሚነቱ የተነገረለት ዜና ከቤይጂንግ ይሰማል። ከቻይናውያን ጋር በጥብቅ የተወያዩት አናን ፤ አሰድ የሰላሙን አቅድ እንዲቀበሉ አብቅተዋል።

«የቻይና መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። ከፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት አባላት ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ገልጾልናል። 6 ነጥቦችን ያካተተው የሰላም አቅድ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። ከደማስቆ አወናታዊ ምላሽ ማግኘቴን አሳውቄአለሁ። ከዚህ ቀደም ሲል ሩሲያ እንዳደረገችው ሁሉ፤ ቻይናም አሁን፤ የኮፊ አናናን አቅድ መደገፉን መርጣለች። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሩሲያና ቻይና፣ አሰድን በመደገፍ፤ የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎች እንዳይተላለፉ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸው ሲያግዱ መቆያታቸው እሙን ነው። አናን ቀጠል በማዳረግ--

« 6 ነጥቦችን የያዘው የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት የሰላም አቅድ፣ የሶሪያው ውዝግብ በቀጥታ የሚመለከታቸው ወገኖች በአጣዳፊ ሁኔታ መወያያቱ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው የሚያሳስበው። ህዝብ ከሚኖርባቸው አካባባዎች፣ ከባድ የጦር መሣሪያዎች እንዲሰበሰቡ፤ የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ፤ እንዲሁም፣ የአርዳታ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች፣ ያለሳንክ እንዲዘዋወሩ ይጠይቃል። እነዚህን የመሳሰሉትን በሰላሙ እቅድ የተካከተቱትን ሃሳቦች ነው እንግዲህ ፣ የሶሪያ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ፣ የተቀበለው። »

ኢስታንቡል ፣ ቱርክ ውስጥ ፣ በ«ግሪን ፓርክ ሆቴል» ፣ ሰሞኑን ስብሰባ ያካሄደው የሶሪያ የተቃውሞ ወገን፣ የኮፊ አናናን የሰላማ አቅድ እንደማይቀበለው ነው የገለጠው። የደማስቆ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ተቃዋሚና የተቃውሞው ብሔራዊ ምክር ቤት ባልደረባ ፣ ናጂ ታያራ--

«የአናን አቅድ የተጓደለ ነው። በደማስቆ የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ አይጠይቅም። ይህ ነው ዋናው ችግራችን፤ በባለ 6 ነጥቡ የሰላም አቅድ ላይ ያየንበት ችግር። እንደሚመስለኝ ፤ በቅርቡ የኃይል እርምጃ ይገታል ብዬ አላስብም። »

ሌላው የታያራ ባልደረባ፤ሐዋዝ ቴሎ የተቃውሞውን ወገን አቋም ይበልጥ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል።

«ፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ፣ አንዱን ዓመት ሙሉ ከውሸት በስተቀር ሌላ የተናገረው ጉዳይ የለም። በዚህ ዓመት ምን ያህል ጊዜ ቃል ገባ? ግን አንዱንም ተግባራዊ አላደረገም። አገዛዙ ፤ ጊዜ ለማትረፍና የህዝቡን አብዮት ለመቀልበስ ነው ዋና ትኩረቱ።

የተከፋፈለው የሶሪያ የተቃውሞ ኃይል ተወካዮች ፣ ፕሬዚዳንት አሰድ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ለመከራከር አይደለም ኢስታንቡል ድረስ በመጓዝ የተሰባሰቡት። የጋራ ግንባርን ለማጠናከር እንዲሁም የምዕራቡን ዓለም ጥያቄ ማሟላት ነው፤ ዋና ዓላማቸው። መጋቢት 23 ቀን 2004 ደግሞ ፣ ከምዕራቡ ዓለምና ከዓረብ መንግሥታት የሚውጣጡ፣ የሶሪያ ወዳጆች የሚባሉ አገሮች ተወካዮች ፣ ኢስታንቡል ውስጥ ይሰበሰባሉ። እስከዚያ፤ የተቃውሞው ወገን፤ በአንድ አቋም ተጠናክሮ ለመገኘት ነው የሚሻው። የሶሪያ ወዳጆች፤ የተቃውሞው ወገን ተግባር ምን እንደሚሆን፤ እንዲሁም ለምን ዓይነት ሶሪያ እንደሚቆም ማወቅ ይፈልጋሉ።ከኢስታንቡል፤ የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ፣ ባሳም ያራ፣

«የተቀውሞው ወገን አንጃዎች፤ የሶሪያን ብሔራዊ ም/ቤት ማደረጃታቸውን በማረጋገጥ አንድ ሰነድ ይፈርሙ ዘንድ ሁሉንም ማግባባት ነው የምንፈልገው። ይህም፣ ከአሰድ ውድቀት በኋላ ፤ የአዲሲቱን ሶሪያ ገጽ የሚያሳይ ይሆናል። አዲሲቱ ሶሪያ፤ ዴሞክራሲን የተላበሰች፣የመደብለ ፓርቲን ሥርዓት የተቀበለች፣ ለሶሪያውያን በመላ የእኩልነትን መብት የምታጎናጽፍ መሆን ይኖርባታል።

ሶሪያ ለወዝግቧ በጊዜ መፍትኄ ካልፈለገች፤ አገሪቱን እየለቀቁ የሚወጡት ስደተኞችም መባራከታቸው አይቀሬ ነው።በአሁኑ ጊዜ አገር ለቀው የወጡት ሶሪያውያን ስደተኞች ቁጥር 40,000 ደርሷል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 28.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14TVL
 • ቀን 28.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14TVL