ሶማልያ እና የኢስታንቡል ጉባዔ | አፍሪቃ | DW | 02.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሶማልያ እና የኢስታንቡል ጉባዔ

በቱርክ የኢስታንቡል ከተማ በሶማልያ ጉዳይ ላይ የመከረው ዓቢይ ጉባዔ ትናንት ተጠናቀቀ። የሀምሳ አራት ሀገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉበት የሁለት ቀናቱ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ትኩረቱን ያሳረፈው በወደፊቱ የሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነበር።

ከሁለት አሠርተ ዓመት የርስበርስ ጦርነትና የተመሰቃቀለ ሁኔታ በኋላ ሶማልያ አሁን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ርዳታ ለማግኘት ተስፋ አድርጋለች። ሀገሪቱን ለማረጋጋት የመጀመሪያው ሂደት ፍሬ እያሳየ መሆኑን የገለጹት የሶማልያ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሀመድ ሀገራቸው በመልሶ ግንባታ ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ አሚሶም የሚረዳው የሶማልያ የሽግግር መንግሥት በአሸባብ አንጻር ባደረገው ዘመቻ በወቅቱ ያስገኘው ውጤት እንዳይከሽፍ ከተፈለገ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሶማልያ ሰፊ የመልሶ ግንባታ መርሃ ግብር እንዲያነቃቃ ጠቅላይ ሚንስር አብዲወሊ መሀመድ የሀምሳ አራት ሀገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት፡ የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች፡ የተመድ ጠበብት እና ሶማልያውያን ባለተቋማት በተሳተፉበት ጉባዔ ላይ ጠይቀዋል። በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያሰሙት የሶማልያ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብዲዌሊ መሀመድ ከስብሰባው የሚጠብቁትን ውጤት እንዲህ ነበር የገለጹት።


« ሶማልያን እስከዛሬ በዓለም እንደ መንግሥት መቆም ያቃታት ሀገር በመባል በግንባር ቀደምትነት ከምትታወቅበት ሁኔታ ተላቃ አዲስ አቅጣጫና አዲስ ጅምር እንድታነቃቃ፡ እንዲሁም፡ ቀድሞ ወደነበርንበት ኩሩ መንግሥትነት እንድትመለስ መምራት ያስፈልጋል። ጉባዔው የሚሳካው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሶማልያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አንድ አቋም ሲይዝ ነው። »
በሶማልያ ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት ስለሚቻልበት ጉዳይ ለመወያየት በተሰበሰቡበት ጉባዔ ንግግር ያሰሙት የተመድ ዋና ፅሐፊ ፓን ኪ ሙንም ለጋሽ ሀገሮች ይህንኑ የመልሶ ግንባታ ጥረት እንዲደግፉ ተማፅነዋል።
« ለጋሽ ሀገሮች ለዚሁ ወሳኝ ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ አሳስባለሁ። የሽብርተኝነት፡ የባህር ላይ ውንብድና ፡ የድርቅና ረሀብ ችግር የተደቀነባት ሶማልያ ትብብር ያስፈልጋታል። ሶማልያ ሀገርዋን መልሳ ለመገንባት በጀመረችው ጥረትዋ ላይ ሊረዳ የሚችል የግል ዘርፍ አላት። የሶማልያ ወጣቶችም ዕድሉ ከተሰጣቸው ሀገሪቱን ሊቀይሩ ይችላሉ። ግን አጋር ሀገሮች የሚጥበቅባቸውን ርዳታ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። »


በሀገሪቱ የሚታየው የረሀብ፡ የስራ አጥነትና የተፈጥሮ አካባቢ ብክለት ችግሮች ሳይወገዱ በፊት የሶማልያን ውዝግብ ማብቃት ይቻላል ተብሎ ማሰብ ዘበት መሆኑን የጉባዔው ተሳታፊዎች ገልጸዋል። የሶማልያ ፕሬዚደንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ፡ የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር ሬቼፕ ጠይብ ኤርዶኻን፡ እና የብሪታንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዊልያም ሄግ ጭምር ተሳታፊ የሆኑበት የኢስታንቡል ዓቢይ ጉባዔ ይህንኑ የሶማልያ የመልሶ ግንባታ ጥረትን እአአ እስከ 2015 ዓም ድረስ የማሳካት ዓላማን ይዞ ነበር የተነሳው። የጉባዔው ተሳታፊዎች ትኩረት ሰጥተው ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የመሠረተ ልማቱ፡ የኃይል አቅርቦት ፕሮዤዎች፡ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ዋነኞቹ ነበሩ። በዚችው የአፍሪቃ ቀንድ ሀገር ውስጥ ልማትን ማራመድ እንዲቻልም የፀጥታው መረጋጋት ወሳኙ ቅድመ ግዴታ መሆኑን ሶማልያዊው ባለተቋም አብዲርታህማን አብዲካኒ አስታውቀዋል።
« የፖለቲካው ሁኔታ ጥሩ ካልሆነና የፀጥታ መረጋጋት ከተጓደለ ማንም ንግድ ለመጀመር አይፈልግም። ሰብዓዊ ርዳታ ማቅረብ እንኳን አይቻልም። »


የኢስታንቡል ዓቢይ ጉባዔ የተካሄደው የሽግግሩ መንግሥት ፀጥታ ኃይላትና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ወታደሮች በመንግሥቱ አንፃር በሚዋጋው አክራሪው አሸባብ አንፃር ጠንካራ ዘመቻ በቀጠሉበት ወቅት ነው። የሙሥሊሞች ቡድን አሁንም ብዙውን የሶማልያ አካባቢ እንደተቆጣጠረ ይገኛል፤ ይሁንና፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሀመድ እንዳስረዱት፡ አሸባብን ለመደምሰስ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት እያስገኘ ነው።
« መዲናይቱን ሞቃዲሾ እና በደቡባዊ እና በማዕከላይ ሶማልያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአሸባብ ሥር የነበሩ ሰፊ አካባቢዎችን ተቆጣጥረናል። አሚሶም፡ የኬንያ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች አሸባብን ጠንክረው በመዋጋት ላይ ናቸው። እና የአሸባብ ሚሊሺያዎች ኅልውና ብዙ ጊዜ ሊቀጥል አይችልም፤ ምክንያቱም፡ የተጠቀሙበት ደንታ የለሽ ሥልት የሕዝብ ድጋፍ አሳጥቷቸዋል። »
የውጭ ጦር ኃይላት የሶማልያን የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት ሊያስወግዱ አይችሉም ያሉት የተመድ ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙን ይህችው ሀገር የራስዋ ጠንካራ ጦር ሠራዊት እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ በሶማልያ ፀጥቃውን በተመለከተ የተመዘገበውን ውጤት በዘላቂነት ለመጠበቅ ይቻል ዘንድ ሶማልያውያን ፀጥታ ኃይላት ማሰልጠንና የጦር መሣሪያ ማስታጠቅ የሚያስችል ገንዘብ ሊዘጋጅላት ይገባል በሚል የቀረበው ሀሳብ በኢስታንቡሉ ጉባዔ በሰፊው ተመክሮበታል። ከዚህ በተጨማሪም ጉባዔው ደግሞ የሽግግሩ መንግሥት ተልዕኮ የፊታችን ነሀሴ ካበቃ በኋላ ስለሚከተለው የሀገሪቱ የፖለቲካ ዕጣ ተወያይቶዋል። ኢብራሂም ማሃዳል የተባሉት ሶማልያዊ የጉባዔው ተሳታፊ እንዳስታወቁት፡ አዲስ መንግሥት ማቋቋም የሚቻልበትን የሰላም ዕቅድ ባፋጣኝ ማውጣት የግድ ነው።


« ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ያዲሱን መንግሥት ምሥረታ የሚያስችለውን የጉዞ ዕቅድ እአአ ከነሀሴ ሀያ በፊት ማብቃት ይሆናል። እንግዲህ እስከዛ ሁለት ወር አላቸው። እንደራሴዎቹን መምረጥ ትልቅ ችግር ይፈጥርባቸዋል ብየ አስባለሁ። »
በዕቅዱ መሠረት፡ አዲስ ሕገ መንግሥት ይረቀቃል ፡ አዲስ ምክር ቤት መንግሥት ይቋቋማል። ይሁንና፡ በቀሩት ሁለት ወራት ውስጥ የተለያዩት የሶማልያ ጎሳ መሪዎች ድጋፍ የሚኖረው የመንግሥት ምሥረታውን ዕቅድ ማውጣቱ አዳጋች እንደሚሆን የፖለቲካ ተንታኞችና ጠበብት ቢያስታውቁም፡ የሶማልያ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሀመድ በአዲሱ ምክር ቤት የሚወከሉት እንደራሴዎችን ቁጥር እና የሴቶች ውክልናን በተመለከተ ፈጣን መሻሻል እየተገኘ መሆንኑን ነው ያመለከቱት።
በቱርክ ጉባዔው የተካሄደ በነበረበት ጊዜ በደቡብ ሶማልያ ይዞት ከቆየው ጠንካራ ሠፈር ለቆ መውጣቱን ያስታወቀው አሸባብ ግን፡ ልክ ካሁን ቀደም በሶማልያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በመከሩት ጉባዔዎች እንደሆነው፡ በኢስታንቡልም ስብሰባ ላይ አልተጋበዘም። ይህ በሽግግሩ መንግሥት አንጻር የሚዋጋው ቡድን ሀገሪቱን ከሚመለከቱ ጉባዔዎች እስከተገለለ ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ተብሎ እንደማይታሰብ ሶማልያዊው ጋዜጠኛ እና ተንቀሳቃሽ ሥዕል አዘጋጅ ጀማል ኦስማን ለአልጀዚራ አስረድቶዋል።
« ምዕራባውያን መንግሥታት ከአሸባብ ጋ በፍፁም እንደማይወያዩ ይናገራሉ፤ የሙሥሊም ሀገሮች ግን በይፋ ባይሆንም በግል በሚሰጡት አስተያየት ላይ ከአሸባብ ጋ መደራደር አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ከአሸባብ ጋ እስካልተደራደሩ ድረስ እንዴት ነው ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው። እና አሸባብ ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ መጋበዝ አለበት ብዬ አስባለሁ። በሶማልያ ኃይልና ተፅዕኖ ያለው ቡድን ለመሆኑ ዕውቅና ተሰጥቶት የሰላሙ ሂደት አካል መሆን አለበት። ይህ እውን እስካልሆነ ድረስ ግን ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበት ሁኔታ አይታየኝም። »
በሀገሯ ለሁለተኛዋ ጊዜ ሶማልያን የተመለከተ ዓቢይ ጉባዔ ያስተናገደችው ቱርክ በተለይ ሶማልያን ለመርዳት ያነሳሳት ምክንያት ከምትከተለው የአፍሪቃ ፖሊሲዋ ጋ የተያያዘ መሆኑን የዶይቸ ቬለ የቱርክ ክፍል ባልደረባ አይኻን ሺምሼክ እደሚለው፡ አስረድቷል።

« ሶማልያን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በአፍሪቃ አኳያ የምትከተለው ፖሊሲዋ ይመስለኛል። ቱርክ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ ነበር አዲስ የአፍሪቃ ፖሊሲ ያወጣችው። በተለይ እአአ ከ 2005ዓም በኋላ አፍሪቃ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። ከዚሁ አዲስ የአፍሪቃ፡ የሶማልያ ፖሊሲ በስተጀርባ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ እና ሀይማኖታዊ ምክንያቶችዋነኛ ሚና መያዛቸው ይታመናል። »

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 02.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/156db
 • ቀን 02.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/156db