ሶማልያ እና የተጠናከረው ፀረ አሸባብ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 11.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሶማልያ እና የተጠናከረው ፀረ አሸባብ ዘመቻ

የሶማልያ መንግሥት ጦር እና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች፣ አሚሶም በደቡባዊ እና ደቡብ ማዕከላይ የሀገሪቱ ከፊል በሚገኙት የአሸባብ ተዋጊዎች አንፃር ካለፉት ሰባት ቀናት ወዲህ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

በዚሁ የጋራ ዘመቻቸውም በሶማልያ መንግሥት እና በውጭ ኃይላት አንፃር የሚዋጋውን አክራሪውን አሸባብ ከበርካታ ሥልታዊ ከተሞች ማስወጣቱ ተሳክቶላቸዋል። ፀረ አሸባብ ጥቃት በተጠናከረበት በዚሁ ጊዜ፣ ሶማሊያውያን በዘመቻው አንፃር እንዲነሱ፣ በተለይ ደግሞ ዘመቻውን በመምራት ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ ላይ ቅዱሱን ጦርነት እንዲያካሂዱ የአሸባብ መሪ አህመድ ጎደኔ ጥሪ አስተላለፈዋል።

የሶማልያ ጦር እና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አሰከባሪ ጓድ፣ አሚሶም ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በደቡባዊ ሶማልያ ባካሄዱት ውጊያ ሰፊ አካባቢዎችን መቆጠጠር መቻላቸው ተሰምቶዋል። መቃድሾ የሚገኘው የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ መሀመድ ኦማር ሁሴን የመንግሥቱን መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አሸባብ መቃዲሾ የሚገኘውን ፕሬዚደንታዊ ቤተመንግሥስት ባለፈው ወር ካጠቃ በኋላ ሰሞኑን ተጠናክሮ በቀጠለው ዘመቻ ትልቅ ሽንፈት የደረሰበት ሲሆን፣ ከ30 በላይ ተዋጊዎቹንም አጥቶዋል።

« አሸባብ በብዙ የሶማልያ አካባቢዎች ተቆጣጥሯዋቸው የነበሩ ቦታዎችን ማጣት ከጀመረ ሰንብቶዋል። የኢትዮጲያ ወታደሮች ከሶማልያ ኃይላት ጋ ባንድነት በሰነዘሩት በዚሁ ጥቃት የባኮል ግዛት ዋና ከተማ ሁዱርን፣ ዋጂድ እና በጎዴ ግዛት ያለችውን ሥልታዊቷን ቡርዱቦን ተቆጣጥረዋል። »

በውጊያው አንድ ሲቭልም መገደሉ ታውቋል። በመጠነ ሰፊው ዘመቻ አሸባብ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ መሪው አህመድ ጎዳኔ ሶማሊያውያን በቀጠለው ዘመቻ፣ በተለይ ደግሞ ዘመቻውን ለመምራት በመዘጋጀት ላይ በሆነችው እና ከ2006 እስከ 2009 ዓም ድረስ በአሸባብ አንፃር ውጊያ ባካሄደችው ኢትዮጵያ አንፃር እንዲነሳ የአሸባብ መሪ ጥሪ አስተላለፈዋል። ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ እና ሲየራ ልዮን የተውጣጡ ወታደሮች የሚገኙበትን እና በወቅቱ የጦሩ ቁጥር 22,000 የደረሰውን አሚሶም ከጥቂት ወራት በፊት በተቀላቀለችው ኢትዮጵያ አንፃር ጎዳኔ ካሁን በፊት እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም ጥሪ ማሰማታቸው አልቀረም፣ ግን፣ ጋዜጠኛ መሀመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለው፣ ጎዳኔ ሶማልያውያኑን ለቅዱሱ ጦርነት ለማነሳሳት ያሰሙት ጥሪያቸው በአሁኑ ጊዜ ሰሚ ጆሮ አያገኝም። ምክንያቱም፣ አህመድ ጎዳኔ በኢትዮጵያ እና በሶማልያ መካከል እአአ በ1977 እና በ1978 ዓም የተካሄደው ጦርነት በዚያን ወቅት በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ፈጥሮት የነበረውን የጠላትነት ስሜት በመቀስቀስ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚያደርጉት ሙከራ መሆኑን እና ጊዜው መቀየሩን የሶማልያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ አሳምሮ ያውቀዋልና፣ መሀመድ ኦማር ሁሴን

« በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኛው የሶማልያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማልያ እንዲገባና ራሱን አሸባብ ብሎ የሚጠራውን ቡድን እንዲደመስስለት፤ እንዲሁም፣ አሸባብ የያዛቸውን ከተሞች እንዲቆጣጠር ይፈልጋል። ሚስተር ጎደኔ ለራሳቸው ጥቅም የሚሰሩ ሰው መሆናቸውን ስለሚያውቅም አስተላለፉት የተባለውን ጥሪ አይከተልም። ጎደኔ በሶማልያ ድጋፍ የላቸውም። »

የአሸባብ መሪ አህመድ ጎደኔ በአሁኑ ጊዜ የት እንዳሉ በግልጽ ባይታወቅም፣ ይዞ ለሚያስረክባት 20 ሚልዮን ዶላር ጉርሻ እንደምትሰጥ ቃል የገባችወ ዩኤስ አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰው አልባ አይሮፕላንዋ በረዌ የሚባል ቦታ አካባቢ ጣለችው በተባለ ጥቃት ሳይቆስሉ እንዳልቀሩ ጋዜጠኛ መሀመድ ኦማር ሁሴን አመልክቶዋል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic