ሶማልያ እና የተመ የሰብዓዊ መብት ጠበብት ጥሪ | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 02.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

ሶማልያ እና የተመ የሰብዓዊ መብት ጠበብት ጥሪ

በሶማልያ የሚገኙት ተቀናቃኝ ወገኖች በሲቭሉ ሕዝብ ላይ የቀጠሉትን የኋይል ርምጃ አሁኑኑ እንዲያበቁ ታዋቂ የተ መ ድ የሰብዓዊ መብት ጠበብት ጥሪ አቀረቡ። ትምህርት ቤቶች፡ ሀኪም ቤቶች እና የመኖሪያ ሰፈሮች የተፋላሚዎቹ ቡድኖች ጥቃት ዒላማ የሆኑበት ድርጊት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተመድ ጠበብት ትናንት በዠኔቭ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

በሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ የሚካሄደው ውጊያ የብዙ ሲቭል ሕዝብ ሕይወት ማጥፋቱና ተጠናክሮና ዒላማ ሳይለይ በቀጠለው ውጊያ የሚሞተው ሕዝብም ቁጥር በሚቀጥሉት ቀናት ሊጨምር እንደሚችል አሥራ ሁለት የተመድ የሰብዓዊ መብት ጠበብት ሥጋታቸውን በዘገባቸው ገልፀዋል። በተመድ የሶማልያ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተመልካች ተጠሪ ጋኒም አልናዣር፡ የመባረር ዕጣ የሚያጋጥማቸው ሰዎች ጉዳይ ተመልካች ተጠሪ፡ ዋልተር ኬሊንን የመሳሰሉ ታዋቂ ጠበብት የተጠቃለሉበት መንበሩን ዠኔቭ ያደረገው ቡድን ዘገባ እንዳመለከተው፡ ሲቭሉ ሕዝብ ውጊያውን እየሸሸ እንዳይወጣ እና የምግብና ሌላ የርዳታ ቁሳቁስም እንዳይጓጓዝ አከላላክለዋል። ባለፈው ሣምንት ብቻ በኢትዮጵያ ጦር ኃይላት በሚረዱት የሽግግሩ መንግሥት ወታደሮችና በሸማቂዎች መካከል በተነሱ በርካታ ግጭቶች እስከ አራት መቶ ሰዎች ተገድለው ከሰባት መቶ የሚበልጡ መቁሰላቸውን፡ በሞቃዲሾ ካለፈው የካቲት ወዲህ የቀጠለው ውጊያ ወደ አራት መት ሺህ የሚጠጋ ሰው ብሎም ከከተማይቱ ነዋሪ አንድ ሦስተኛውን ከቤት ንብረቱ ማፈናቀሉን ዘገባው አስታውሶዋል። ከዚህም በመነሳት ተፋላሚዎቹ ወገኖች ባስቸኳይ የተኩስ አቁም ደምብ እንዲደርሱ በጥብቅ አሳስበዋል። እንደሚታወሰው፡ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሶማልያ መዲና የቀጠለውን ውጊያ ከትናንት በስቲያ አውግዞዋል፤ በመቀጠልም የሶማልያ የሽግግር መንግሥት በሀገሪቱ ካሉ የተለያዩ ቡድኖች በተለይ በሀገሪቱ ፖለቲካ ለወትሮው ትልቅ ተፅዕኖ ከሚያሳርፉር የጎሳ አንጃ ጋር ውይይቱን እንዲያጠናክር አሳስበዋል። የሽግግሩ መንግሥት ሶማልያውያንን በጠቅላላ የሚወክል አንድ ብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ጉባዔን ባስቸኳይ እንዲጠራና በሀገሪቱ ለተነሱ ልዩነቶች ሁሉ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚኖርበት ምክር ቤቱ በተጨማሪ ጠይቆዋል።