ሶማልያ ሱናሚ ያደረሰው ጥፋት | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.01.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሶማልያ ሱናሚ ያደረሰው ጥፋት

በሕንድ ውቅያኖስ ከአሥራ ሁለት ቀናት በፊት የተከሰተው የጎርፍ ማዕበል አደጋ በደቡብ እሥያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪቃ የባህር ጠረፍም የሰው ሕይወት አጥፍቶዋል፤ ብዙ ጉዳትም አድርሶዋል።

ሱናሚ በሶማልያ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከአየር ላይ ሲታይ

ሱናሚ በሶማልያ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከአየር ላይ ሲታይ

ግዙፉ ጥፋት ከታየበት ደቡብ እሥያ አካባቢ አራት ሺህ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘዋ ሶማልያ በተፈጥሮው መቅሠፍት አብዝታ ተጎድታለች። የቀድሞው የሶማልያ ፕሬዚደንት ዚያድ ባሬ ከሥልጣን ከተወገዱ ካለፉት አሥራ አራት ዓመት ወዲህ ማዕከላይ መንግሥት የሌላት ይህችው ሀገር አስቸኳዩ ርዳታ ያስፈልጋታል።

በሶማልያ የባህር ጠረፍ በሱናሚ የሞተው ሰው አሀዝ በግልፅ ማወቁ አዳጋች ነው። የታህሳስ ሀያ ስድስቱ ገዳይ የጎሮፍ ማዕበል የሶማልያ ባህር ዳርቻ በደረሰበት ጊዜ ብዙ ሶማልያውያን አሣ አሥጋሪዎች መርከቦቻቸውን ይዘው ወደ ውቅያኖሱ ወጥተው ነበርና። በተመ ድ እና በርዳታ ድርጅቶች ግምት መሠረት፡ የሞቱት ሶማልያውያን ቁጥር በሁለት መቶና ሦስት መቶ መካከል ንብረታቸውን ያጡትና ካለ መጠለያ የቀሩት ደግሞ በአሥራ ሰባት እና ሀምሳ አራት ሺህ መካከል ይደርሳል። የተ መ ድ የዓለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ላውራ ሜሎ ከናይሮቢ ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለፁት።
« ሱናሚ በሶማልያ ባህር ጠረፍ ያደረሰው ጉዳት ገና በግልፅ አልታወቀም። በዚያ ርዳታ የሚሰጡና የደረሰውን ጥፋት የሚገመግሙ ቡድኖችን አሠማርተናል። አሁን ባለን መረጃ መሠረት፡ የጎርፉ ማዕበል አደጋ ከሠላሣ ሺህ የሚበልጥ ሰውን የነካ ሲሆን፡ ያፈሩትን ሁሉ፡ መኖሪያ ቤታቸውን፡ እና ለአሣ ማሥገሪያው ሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ - ብሎም ኑሮዋቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን የኅልውናቸው መሠረት ሁሉ አጥተዋል።»
በሱናሚ ብዙ ጉዳት የደረሰበት በሰሜን ሶማልያ የሚገኘውና ነፃ መንግውት መሥርቻለሁ የሚለው ፑንትላንድ ናት። አንዳንድ በጎርፉ አደጋ ትልቁ ጥፋት የገጠመው የሀይፉን ከፊል ደሴት ነዋሪዎች ከከተማይቱ በላይ ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ በመሄድ ሕይወታቸውን ሊያተርፉ ችለዋል። አሣን ወደ ጎረቤት ዱባይ በኤክስፖርት የሚልኩት ብዙዎቹ አሣ አሥጋሪዎች ግን አሣ ለማጥመድ ወደ ውቅያኖሱ እንደወጡ በዚያው ሳይመለሱ ቀርተዋል። ከዚህ ሌላም የጎርፉ ማዕበል ያን ያህል ያልነበረውን የብዙዎቹን አካባቢዎች መሠረተ ልማት ከሞላ ጎደል በማውደሙ የርዳታ አቅርቦት የያዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች አጀብ ርዳታውን ለተጎጂው በማድረሱ ሥራቸው ላይ ችግር እንደገጠማቸው ላውራ ሜሎ ገልፀዋል። በተለይ ጊዜው ለአሣ ማሥገሩ ተግባር አመቺ በሆነበት በዚሁ ወቅት የጎርፉ ማዕበል አደጋ ሶማልያ ባህር ጠረፍን መምታቱ ብዙዎቹን፡ ብሎም፡ ካለፉት አራት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰተው ድርቅና በሰበቡም በተፈጠረው የምግብ እጥረት የተነሣ እረኝነቱን ትተው በአሣ ማሥገሩ ተግባር የተሠማሩትን የሀገሪቱን ዜጎች ጭምር አብዝቶ ጎድቶዋል።
የተመድ የዓለም የምግብ ድርጅት ከዛሬ ጀምሮ ከሞምባሳ ኬንያ በሚነሡ በመርከቦች ለሰሜናዊ ሶማልያ የምግብ ርዳታ፡ ብርድ ልብስና መድሀኒት ርዳታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። የሶማልያ ሕዝብ ለርዳታ አቅርቦቱ በአዲሱ መንግሥት ላይ ሊተማመን አይችልም፤ ምክንያቱም አዲስ የተመሠረተውና አሁንም በኬንያ የሚገኘው አዲሱ የሶማልያ መንግሥት በሀገሩ አንድ ስንዝር መሬት ባለመቆጠጠሩ፡ አሁንም ሥልጣኑ ያለው በተለያዩት የጦር ባላባቶች እጅ ነውና። ቢህም የተነሣ ምንም እንኳን የሱናሚ ጥፋት በእሥያ እጅግ ግዙፍ ቢሆንም፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ አፍሪቃንም መርሳት እንደሌለበት የተ መ ድ የዓለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ላውራ ሜሎ የሚከተለውን ጥሪ አሰምተዋል። « በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ በሶማልያ ላሉት የሱናሚ ተጎጂዎች ማቅረብ እንችል ዘንድ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚልዮን ዩኤስ ዶላር አስቸኳይ ርዳታ እንዲቀርብልን እንማፀናለን።»