ሶማልያና አከራካሪው የሽግግር መንግሥት መንበር ጥያቄ | የጋዜጦች አምድ | DW | 24.09.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሶማልያና አከራካሪው የሽግግር መንግሥት መንበር ጥያቄ

ፕሬዚደንት አብዱላሂ ዩሱፍ የሚመሩት የሶማልያ የሽግግር መንግሥት መንበር የት ይሁን በሚለው ጥያቄ የተነሣ ከፕሬዚደንቱና ከደጋፊዎቻቸው ጋር መወዛገብ የያዙት የተለያዩት

በሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ የሚገኙት ጦር አበጋዞችና ተባባሪዎቻቸው አንዳንድ የሽግግሩ መንግሥት ካቢኔ አባላት፡ እንዲሁም፡ አንዳንድ የሽግግሩ ምክር ቤት እንደራሴዎች ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስገኘት የተጀመረውን ጥረት ለማሰናከል ተነሥተዋል ሲሉ የሶማልያ ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ጌዲ ከጥቂት ቀናት በፊት ወቀሳ አሰሙ። ጌዲ ይህንን መግለጫ ያወጡት የጦር አበጋዞቹ በኢትዮጵያ ይረዳል ባሉት የአብዱላሂ ዩሱፍ ጦር ኃይልን የሚቋቋም ሚሊሺያ ጦራቸውን ከመዲናይቱ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ስለሚሰማራበት ጉዳይ ከተወያዩ በኋላ ነበር።

በሶማልያ እየከፋ የሄደው የፖለቲካ ውዝግብ ሀገሪቱን እንደገና ወደ ጦርነቱ ሁኔታ እንዳይመልሳት እና አሳሳቢውን ሰብዓዊ ችግር እንዳይፈጥር ማሥጋቱን ጠበብት ገለፁ። በፕሬዚደንት አብዱላ ዩሱፍ የሚመራው በግዞት የሚገኘው ወደሀገሪቱ በሚመለስበት ጊዜ የመንግሥቱ አስተዳደር መንበር የት ይሁን በሚለው ጥያቄ ሰበብ ከብዙ ወራት በፊት የተፈጠረው ልዩነት በአባላቱ መካከል መተማመን እንዳይኖር አድርጎዋል። ይኸው በመንግሥቱ አባላት መካከል የታየው የልዩነት ሁኔታም ካለፉት ቅርብ ጊዚያት ወዲህ ይበልጡን እየተካረረ በመሄዱ፡ የጦር አበጋዞች ውዝግባቸውን ለማስወገድ ሲሉ በኃይሉ ርምጃ እንዳይጠቀሙ ነው የሀገሪቱን ነዋሪዎች ያሳሰበው። ባንድ በኩል የፕሬዚደንት ዩሱፍ የሚደግፉ፡ በሌላ ወገን ደግሞ የሚቃወሙ ሚሊሺያዎች እንቅስቃሴ የተጠናከረበት፡ ከውጭ ወደ ሶማልያ በንግድ ወደ ሶማልያ ግዙፍ የቶር መሣሪያ መግባት የያዘበት፡ በሞቃዲሾ የታወቁ ሶማልያ ዜጎች የተገደሉበት፡ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት በመዲናይቱ የተካሄደው ፕሮዤ የከሸፈበት፡ በመጨረሻም አክራሪ ሙሥሊሞች በሀገሪቱ የታየውን የሥልጣን ክፍተት ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የጀመሩት ጥረት ባንድነት አሥጊ ሁኔታ መፍጠሩን ያካባቢውን ፖለቲካ የሚከታተሉ አስተንታኞች አስረድተዋል። ሶማልያውያኑ ፖለቲከኞች ብዙ ዓመት ለሆነው ውዝግባቸው ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት ዝግጁ ያልሆኑበት ድርጊት ሀገራቸውን ደም አፋሳሹ ውጊያ ውስጥ እንዳይጥላት የሠጉት የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደራዛክ ሀጅ ሁሴን በመግለፅ፡ ሶማልያ ውስጥ በቅርቡ አስደንጋጩ ሰብዓዊ ችግር ቢከሰት ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ እንዳይገርመው አስገንዝበዋል።
ሶማልያ ምስቅልቅሉ ሁኔታ ውስጥ ከምትወድቅበት ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑት፡ የፖለቲካ አስተንታኞች እንደሚሉት፡ በሞቃዲሾ የሚገኙትና ውዝግቡን የቀጠሉት የጦር ባላባቶችና በሀገሪቱ ፖለቲካ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የሚፈልጉት ሙሥሊሞች ናቸው። የፕሬዚደንት ዩሱፍ የሽግግር መንግሥት ካለፉት በርካታ ሣምንታት ወዲህ በመላ ሶማልያ ተዋጊዎችን ማሠልጠን የጀመረ ሲሆን፡ ርምጃቸው በተቀናቃኞቻቸው አንዳንድ በሞቃዲሾ አካባቢ ይገኛሉ በሚባሉት የካቢኔ አባላት፡ በሽግግሩ ምክር ቤቱ እንደራሴዎች፡ በጦር አበጋዞቹ ሠፈሮች ጥቃት ለመሰንዘር መሆቸውን የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ታይቶዋል። እርግጥ፡ ያካባቢው ኃያል መንግሥት ከምትባለው ኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ፕሬዚደንት ዩሱፍ ተቀናቃኞቻቸውን ለማግባባትና ትብብራቸውን ለማግኘት የኃይሉን ተግባር ሳይሆን ውይይቱን እንደሚያስቀድሙ አዘውትረው ይናገራሉ። ሒሰኞቻቸ እንደሚሉት ግን፡ የሰባ ዓመቱ ዩሱፍ አሁን አዲስ ኃይል ለማቋቋም የጀመሩት ጥረታቸው ቀድሞም ይጠቀሙበት የነበረውን የኃይልእ አሠራራቸውን የሚያጎላ ነው። የክፍለ ሀገር ጦር ባላባት የነበሩት ዩሱፍ በተለያዩት የሶማልያ የሞቃዲሾ የጦር አበጋዞች መካከል ኅብረት ለመፍጠር ቀደም ባሉ ዓመታት ለተደረጉት ዲፕሎማቲካዊ ጥረቶች ፍፁም ክብደት ሰጥተው የማያውቁ ግለሰብ መሆናቸውን ነው ሒሰኞች የገለፁት። ሶማልያውያን ቀንደኛ ጠላት አድርገው የሚመለከተዋት ኢትዮጵያ ለአብዱላሂ ዩሱፍ ጦር ኃይል የጦር ርዳታ ሰጥታለች የተባለበትን ዘገባ በተደጋጋሚ ብታስተባብልም፡ ያይን ምስክሮች ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ በብዙ የሶማልያ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ጦር መኮንኖች የፕሬዚደንት ዩሱፍ ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ ማየታቸውን አመልክተዋል። ዩሱፍ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ሥልጣናቸውን በኃይል ለማሳረፍ ይሞክራሉ የሚሉት ተቃዋሚዎቻቸው የጦር አበጋዞችና ሙሥሊሞቹ አሁን ሚሊሺያዎቻቸውን እንደገና በማደራጀት በአብዱላሂ ዩሱፍ ጦር ኃይል አንፃር የሚዋጋ አንድ የጋራ ጠንካራ ኅብረት ፈጥረዋል። ሶማልያዊው የፖለቲካ አስተንታኝ አብዲ ኢዝማኤል ሳማትራ እንዳስረዱት፡ አሁን በዩሱፍ አንፃር የተፈጠረው የጋራ ኅብረት የግል ጥቅምን ለማስከበር ነው።
አብዱላሂ ዩሱፍና አሊ ጌዲ የሽግግሩን መንግሥት በሞቃዲሾ እንዲያደርጉ ተቀናቃኞቻቸው በተደጋጋሚ ፍላጎታቸውን ቢያሰሙም፡ ዩሱፍ መዲናይቱ አደጋኛ ቦታ ናት በሚል የመንግሥታቸውን መንበር በክፍለ ሀገርዋ የጆውሀር ከተማ ማድረጉን ነው የመረጡት።
በዚሁ ልዩነት የተነሣ በሶማልያ ሊነሣ የሚችል የጦርነት ርምጃ ተቀባይነት እንደማይኖረው የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቀደም ሲል አስታውቋል፤ ይሁንና፡ ለሶማልያ ዘላቂ ሰላም በሚወርድበት ዘዴ ላይ ስምምነት ባለመደረሱና አንድም ኃያል መንግሥት ለዚሁ የምክር ቤት መልዕክት ድጋፍ ባለመስጠቱ፡ መልዕክቱ ክብደት ሳያገኝ ታልፎዋል። ይህንንም የታዘቡት ሶማልያዊው የፖለቲካ አስተንታኝ ሳማትራ፡ ምንም እንኳን ቀደም ባሉ ጊዚያት ለሶማልያ ውዝግብ መፍትሔ ለመሻት በርካታ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ቢደረጉምና ቢከሽፉም፡ አሁን ሶማልያውያኑ ተቀናቃኝ ወገኖች ለጦርነት ዝግጅት የያዙበትን ሁኔታ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ በቸልታ መመልከት የቀጠለበትን ድርጊት ግራ አጋቢ ሆኖ አግኝተውታል። በዚህም የተነሣ አንዳንድ ዓበይት መንግሥታት ከሶማልያ የሚሰጡትን ርዳታ፡ ሶማልያውያኑ ለውዝግባቸው መፍትሔ እስኪያስገኙ ድረስ፡ ለማቋረጥ በማሰላሰል ላይ ይገኛሉ። ይሁንና፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ሲያድ ባሬ ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲህ ካለማዕከላይ መንግሥት በምትገኘዋ ሶማልያ ውስጥ አዲስ ውጊያ የሚነሣበት ሁኔታ ሥቃይ ባልተለየው የሀገሪቱ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ችግር እንደሚፈጥርበት የርዳታ ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል። የሶማልያ የምግብ አቅርቦት ዋስትናን እንዲመረምር የአውሮጳ ኅብረትና ዩኤስ አሜሪካ በጋራ ያቋቋሙት አንድ ቡድን እንዳመለከተው፡ በዚችው ሀገር በጣለው ንእዑስ ዝናብ የተነሣ ዘንድሮ የሚሰበበሰበው መኸር እጅግ ንዑስ ነው፤ ይህም ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ የሶማልያ ዜጋ በአስቸኳዩ የምግብ ርዳታ ላይ ጥገኛ እንዲሆን ያደርገዋል።

ተዛማጅ ዘገባዎች