ሶማሊያ እና ፀጥታዋ | አፍሪቃ | DW | 16.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሶማሊያ እና ፀጥታዋ

የሶማልያ መንግሥት አሸባብ የደቀነውን የሽብርተኝነት ስጋት በሚቻለው ሁሉ ለመታገል ጥረቱን ቀጥሎዋል። ይሁንና፣ ይኸው ትግሉ ቀላል እንዳልሆነ ገልጾዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:33
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:33 ደቂቃ

ፀረ ሽብርተኝነት ትግል

አሁንም የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ በሆነችው ሶማልያ የቀድሞው የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስትር በመዲናይቱ ሞቃዲሾ በመኪና ውስጥ የተጠመደ ቦምብ በፈነዳበት ጥቃት ተገድለዋል። ከሞቃዲሾ ወደ ጅቡቲ ሲበር በረራውን ባስቸኳይ አቋርጦ ወደ መዲናይቱ እንዲመለስ በተገደደ አንድ የመንገደኞች ማመላለሻ አይሮፕላንም ላይ ከ11 ቀን በፊት የቦምብ ጥቃት መጣሉ የሚታወስ ነው። ለሁለቱም ጥቃትበመንግሥቱ አንፃር የሚንቀሳቀሰው ያማፂ ቡድን አሸባብ ኃላፊነቱን ወስዶዋል። ሶማልያ በሽብርተኝነት አንፃር ስለጀመረችው ትግል የሀገሪቱ ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ ለዶይቸ ቬለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በጀርመን የሚውኒክ ከተማ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የሶስት ቀናት የፀጥታ ጉባዔ ከመከረባቸው ዓቢይ ጉዳዮች መካከል ራሱን «እስላማዊ መንግሥት(«አይ ኤስ») ወይም በዐረብኛ «ዳያሽ» ብሎ የሚጠራው ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ የደቀነው የሽብርተኝነት ስጋት ዋነኛው ነበር። በጉባዔው ከተሳተፉት መካከል ይኸው ችግር ካልተለያቸው አፍሪቃዊት ሀገራት አንዷ የሆነችው የሶማሊያ መንግሥት ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ አብዲራህማን ሼክ ኢሴ «እስላማዊው መንግሥት» የደቀነው ስጋት ለሀገራቸውም አሳሳቢ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል። ይሁንና፣ «እስላማዊው መንግሥት» ከአል ቃይዳ ጋር ቅርበት አለው ከሚባለው የሶማሊያ ዓማፂ ቡድን አሸባብ ጋር በመተባበር በሀገራቸው ስር ለመስደድ እያደረገው ያለው ሙከራ እንዳልተሳካ ኢሴ በመግለጽ፣ መንግሥታቸው ይህን ለማከላከል ጥረቱን ማጠናከሩን አመልክተዋል።

« የምንኖረው ሁሉ ነገር፣ ችግሮችም ጭምር በተያያዙበት ዓለም ውስጥ ነው። አሸባብ ብቻውን የቆመ ቡድን አይደለም፣ ከሌሎች አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አለው። እንደሚታወቀው፣ ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ቀደም ባሉ ጊዚያት ይፋ አድርጎዋል። እርግጥ፣ አንዳንድ የአሸባብ አንጃዎች ከ«አይ ኤስ» ጋር ግንኙነት መፍጠር ይፈልጋሉ፣ በዚህም የተነሳ በቡድኑ ውስጥ ልዩነት መፈጠሩ ሚስጥር አይደለም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን የኛ ዓላማ በሽብርተኝነት አንፃር የጀመርነውን ጦርነት ማሸነፍ ነው፣ ጦርነቱን ለማሸነፍም እነሱን መደምሰስ ይኖርብናል። »

ይሁንና፣ የሶማልያ መንግሥት ይህንኑ ዓላማውን እስካሁን ከግብ ማድረስ አልሆነለትም፣ አሸባብ በተለይ በሶማልያ ወጣቶች ዘንድ ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረቱ የመንግሥቱን ርምጃ እያሰናከለው መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ከሶማልያ ሕዝብ መካከል 70% 15 እና በ35 ዕድሜ መካከል የሚገኝ ሲሆን፣ አሸባብ በዚሁ ቡድን ውስጥ የሚታየውን ግዙፍ የስራ አጥነት ችግር በመንግሥቱ አንፃር ለሚያካሂደው ዓመፅ ማራመጃ፣ ብሎም ወጣቱን ለመመልመያ ይጠቀምበታል። የሶማልያ መንግሥት ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ አብዲራህማን ሼክ ኢሴ ችግሩ ቀላል አለመሆኑን አልካዱም፣ ያም ቢሆን ግን፣ መንግሥታቸው የዚህኑ ያማፂ ቡድን እቅድ ለማክሸፍ በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

« እርግጥ ነው በወቅቱ አሸባብን በጦር ለመውጋት ብቻ ሳይሆን የወጣቱን ልብ እና አስተሳሰብ ለመማረክም ነው እየታገልን ያለነው። በዘረፋ ትርጉሙ «ወጣት» የሚሰኝ ስያሜ የያዘው አሸባብ ዋና ዒላማ ያደረገው ወጣቱን ነው። በመሆኑም፣ እኛ ይህ እንዳይሳካ ለወጣቱ ብሩሕ የኑሮ እና የትምህርት እድል ለመፍጠር እና ለሀገሩ ድርሻ የሚያበረክት ዜጋ ለማፍራት ጥረት ጀምረናል። ግን፣ ይህን ማሳካቱ በወቅቱ ቀላል አይደለም። በዚህም የተነሳ ነው አሁን ወደ ሙኒክ በመምጣት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የርዳታ ጥሪ ያቀረብነው። የጀመርነው ፀጥታ የማስጠበቁ ትግል እና የኤኮኖሚው ልማት የተያያዙ እንደመሆናቸው መጠን ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ርዳታ፣ ለምሳሌ፣ ወጣቶቹ እውቀቱ እና ችሎታው እንዲኖራቸው ወሳኝ እና አስፈላጊ የሆነው የሙያ ስልጠና እንዲቀርብልን ጠይቀናል። »

የሶማልያ ፕሬዚደንት ሼኽ መሀሙድ ሁሴን በሚውኒኩ የፀጥታ ጉባዔ ተሳትፎአቸው ወቅት ስለዚሁ ጉዳይ ከጀርመን የመከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ጋር ተገናኝተው መምከራቸውን ብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ አብዲራህማን ሼክ ኢሴ አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic