ሶማሊያ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋዜማ | አፍሪቃ | DW | 07.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሶማሊያ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋዜማ

ከተደጋጋሚ ቀነ ቀጠሮዎች በኋላ ነገ የካቲት 1 ይካሄዳል ለተባለው የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 22 ተወዳዳሪዎች ተሰልፈዋል፡፡ የምርጫው ሂደት በሙስና፣ ማጭበርበር እና ማስፈራራት የጠለሸ ነው የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ አሉታዊ ጥላ አጥልቷል የሚሉ ታዛቢዎች አሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57

ኢትዮጵያ በምርጫው ጣልቃ ገብታለች ተብሏል

ሶማሊያ ምጥ ላይ ነች፡፡ ለወራት ያረገዘችውን የምርጫ ሽል ልትገላገል አፋፍ ላይ ደርሳለች፡፡ አስራ ሰባት አባላት ያሉበት የአዋላጆች ስብስብ ከየአቅጣጫው በሽሉ ጤንነት ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡

የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኮሚቴ በመባል የሚታወቀው ስብስብ ምርጫው ቀናት ሲቀሩት ከ18 ዕጩዎች የቀረበለትን ቅሬታ ተቀብሎ የድምጽ መስጫ ቦታው እንዲቀየር አድርጓል፡፡ በሀገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ፕሬዝዳንቷን በቀጥታ የህዝብ ድምጽ የማትመርጠው ሶማሊያ ኃላፊነቱን ለ329 የህግ መወሰኛ እና ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰጥታለች፡፡

የምክር ቤት አባላቱ ተሰብስበው ድምጽ እንዲሰጡ የታሰበው በዋና ከተማይቱ ሞግዲሾ በሚገኘው የፖሊስ አካዳሚ ነበር፡፡ ሆኖም የሀገሪቱ ፖሊስ አዛዥ አሁን በስልጣን ለሚገኙትና በድጋሚ ለሚወዳደሩት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ድጋፋቸውን በግልጽ በማሳየታቸው ለምርጫው መጭበርበር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ በሚል በሌሎች ዕጩዎች ቅሬታ ቀርቦባቸዋል፡፡ በሙስና እና ማጭበርበር ጉዳይ “እንኳን ዘንብቦሽ…” የሆነውን የሶማሊያ የምርጫ ሂደት ከውዝግብ ለማጽዳት ያሰበ የመሰለው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኮሚቴ የድምጽ መስጫ ቦታውን በሞግዲሹ አየር ማረፊያ ወደሚገኝ አዳራሽ አዛውሮታል፡፡

የምርጫ አስፈጻሚው ኮሚቴ በዚህ ብቻ አልተገታም፡፡ ምርጫው የሚካሄድባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እዚያው በምክር ቤት አባላት ፊት ታትመው እንደሚሰራጩ ይፋ አድርጓል፡፡ ለማጭበርበር ቀዳዳ ላለመክፈት የድምጽ መስጫ ወረቀቶቹ በምክር ቤቱ አባላት ልክ እንደሚታተሙም ገልጿል፡፡ የምርጫ ኮሚቴው የምርጫውን ተዓማኒነት ለመጠበቅ እና ግልጽነትን ለማስፈን እንዲህ ቢሞክርም በምርጫው ዙሪያ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እየገቡ ነው የሚለው ጉምጉምታ ደምቆ ይሰማ ይዟል፡፡

ስለ ውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በይፋ አስተያየታቸውን ካሰፈሩ የሶማሊያ ልሂቃን መካከል መሐመድ ሽሬ አንዱ ናቸው፡፡ ቀድሞ ለሶማሊያ መንግስት በአማካሪነት የሰሩት እና አሁን በጸጥታና ልማት ዙሪያ የሚያማክሩት መሐመድ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ ኳታር እና ቱርክ ከመካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ በሶማሊያ ምርጫ እጃቸውን ሰድደዋል ይላሉ፡፡ 

“በቀጠናው ያሉ ሀገራትና ሌሎች ሀገራት በሶማሊያ ላይ ፍላጎት ቢኖራቸው ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ሶማሊያ አሁን ከግጭት የወጣች ሀገር ነች፡፡ የጸጥታ ጉዳዩች አሉ፡፡ ከመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ጋር የተያያዙ ሌሎችም ፍላጎቶች አሉ፡፡ ሶማሊያ በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የተቀመጠች ነች፡፡ የኢትዮጵያ ስጋት ይበልጥ ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለእርሷ ስጋት የማትሆን ነገር ግን ደህንነቷ የተጠበቀ ሶማሊያን ማየት ትፈልጋለች፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ገንዘብ በመስጠት የአካባቢ ምርጫዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ትሞክራለች የሚል ጭምጭምታ አለ፡፡ ኢትዮጵያ የምክር ቤት አባላት ድምጻቸውን ለአሁኑ ፕሬዝዳንት እንዲሰጡ ጫና እያሳደረች ነው፤ በከፍተኛ ደረጃም እየተሳተፈች ነው የሚል ጭምጭምታ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ አሉ፡፡ ህዝቡ ዲሞክራሲያዊው ምርጫ ለጥቅም ማቻቻያ ይሆናል የሚል ስጋት አድሮበታል” ይላሉ አማካሪው፡፡  

ገንዘብ ይረጭበታል በሚባለለት በዚህ ምርጫ ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ በራሱ አስር ሺህዎች ዶላር ያስወጣል፡፡ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ 23 የነበሩት ዕጩዎች ሁሉም በምርጫው በእጩነት ለመመዝገብ 30 ሺህ ዶላር የመክፈል ግዴታ ተቀምጦባቸዋል፡፡ የዕጩዎቹ ብዛት በሌሎች ሀገር ከተለመደው የበዛ ቢመስልም በምርጫው የመሪነት ረድፍ የተቀመጡት ግን አራት እንደሆኑ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ እና ከአምስት ዓመት በፊት የሶማሊያ የፌደራል የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት የነበሩት ሼክ ሸሪፍ አህመድ በተንታኞች ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ኦማር ሻርማርኬ እና ሙሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆም ከሚጠበቁት ተርታ ተመድበዋል፡፡ መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው ሶማሊያዊው ጋዜጠኛ ሊባን አህመድ ቅድሚያውን ለሼክ ሸሪፍ ይሰጣል፡፡   

“እኔ እንደማስበው ሼክ ሸሪፍ አህመድ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ትናንት ምሽት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰይድ ፣ ከአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡመር አብዱራሺድ እና ከፑንትላንድ ፕሬዝዳንት አብዱ ዋሌ ጋስ ጋር ተገናኝተው ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድን ከመንበራቸው ለማስለቀቅ ጥምረት የመሰረቱ ይመስላል፡፡ ሼክ ሸሪፍ አህመድ ዘላቂ ጥምረት በመመስረት ሰፊ ልምድ አላቸው፡፡ ቀጣዩ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እርሳቸው ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ” ሲል ቅድሚያ ግምቱን አጋርቷል፡፡    

ሊባን የጠቀሰው የጥምረት ውጤት ውሎ ሳያድር የታየ ይመስላል፡፡ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የነበሩት የቀድሞው የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ፍሮሌ በ11ኛው ሰዓት ራሳቸውን ከምርጫ አግልለዋል፡፡ ዕጩው ከምርጫው ለመውጣታቸው ምክንያታቸውን ባይገልጹም የተወዳዳሪዎቹን ቁጥር ግን በአንድ ቀንሰዋል፡፡ የ22 ዕጩዎች ሩጫ መጨረሻ ነገ ይታወቃል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

 

  

Audios and videos on the topic