ሶማሊያ በአልሻባብ ላይ ጦርነት ልታውጅ ነው | አፍሪቃ | DW | 21.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሶማሊያ በአልሻባብ ላይ ጦርነት ልታውጅ ነው

ባለፈው ቅዳሜ በሶማሊያ ለደረሰው የቦምብ ፍንዳታ የሶማሊያ መንግስት ተጠያቂ ነው ባለው አልሻባብ ላይ የጦርነት ዘመቻ ያውጃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡ በፍንዳታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 358 ያሻቀበ ሲሆን 56 ሰዎች እስካሁንም የደረሱበት አልታወቀም፡፡ 

በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ እንደሚታወጅ በሚጠበቀው በዚህ አዲስ ዘመቻ ዩናይትድ ስቴትስ የአጋዥነት ሚናዋ ከፍተኛ እንደሚሆን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሶማሊያ ወታደራዊ መኮንን ለአሶሴትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ለሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ አስቸኳይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ተነግሯል፡፡ የሶማሊያ ጦር ቃል አቃባይ ሻምበል አብዱላሂ ኢማን እንደተናገሩት አዲሱ ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን የሚያሳትፍ ነው፡፡ የዘመቻው ዋና ኢላማ የአልሻባብ ተዋጊዎችን ከጠንካራ ይዞታዎቻቸው የታችኛው እና የመካከለኛው ሸበሌ ማስወጣት እንደሆነ ቃል አቃባዩ ገልጸዋል፡፡ ተዋጊዎቹ እነዚህን ይዞታዎች በሶማሊያ መዲና ሞቅዲሹ ላይ እና በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ የጦር ሰፈሮች ላይ ለሚያደርሷቸው ጥቃቶች እንደመንደርደሪያነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ 


አልሻባብ በሶማሊያ ታሪክ አስከፊ ነው ለተባለለት የባለፈው ሳምንት ጥቃት እስካሁን ኃላፊነቱን አልወሰደም፡፡ አልሻባብን ተጠያቂ የሚያደርጉት የሶማሊያ የደህንነት ባለስልጣናት ግን ጥቃቱ የመጀመሪያ ኢላማው የነበረው በርካታ ኤምባሲዎች ያሉበትን የዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አካባቢ ነበር ይላሉ፡፡  ባለስልጣናቱ ህዝብ በሚበዛበት የሞቅዲሹ ስፍራ የፈነዳው ቦምብ ከ600 እስከ 800 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን ይገምታሉ፡፡ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር አብዲራህማን ኦስማን አርብ ማምሻውን እንዳስታወቁት በፍንዳታው ከሞቱት እና ደብዛቸው ከጠፉት የሀገሪቱ ዜጎች ሌላ 228 ሰዎች ቆስለው በህክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 122ቱ ወደ ቱርክ፣ ኬንያ እና ሱዳን ለተሻለ ህክምና ተልከዋል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ