ሶማሊያና የጀርመን ጦር ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 20.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሶማሊያና የጀርመን ጦር ዘመቻ

ይሁንና የማማከሩ ምግባር መሳካቱን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ይጠራጠራሉ።ምክንያታቸዉ የሶማሊያ ጦር ግልፅ አደረጃጃት የለዉም የሚል ነዉ።ማቲያስ ቬበር እንደሚሉት የሶማሊያ ጦር አደረጃጃትን ቅጥ ካሳጡት ዋናዉ በጎሳ ልይ የተመሠረተ መሆኑ ነዉ።

የሶማሊያን ወታደሮች እስካሁን ድረስ ዩጋንዳ ዉስጥ ሲያሠለጥኑ የነበሩት የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ወታደሮች ሥልጠናዉን እዚያዉ ሶማሊያ ዉስጥ ለመስጠት ወደ ርዕሠ ከተማ ሞቃዲሾ ሠሞኑን ይዘምታሉ።የአዉሮጳ ሕብረት የአሰልጣኞች ተልዕኮ ለሶማሊያ (EUTM Somalia) በተሰኘዉ ተልዕኮ የሚካፈሉት የጀርመን ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንዲዘምቱ የጀርመን መንግሥት ትናንት ወስኗል።የጀርመን ካቢኔ ትናንት ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ሃያ የጀርመን ወታደሮች ከሌሎች የአዉሮጳ ሕብረት ሐገራት ወታደሮች ጋር ሆነዉ ለበርካታ ዓመታት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥትና ጦር የሌላትን ሐገር ወታደሮች ለማሰልጠን በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ ይዘምታሉ።የአዉሮጳ ሕብረት ባጠቃላይ 125 አሰልጣኝና አማካሪ ወታደሮችን ለማዝመት ነዉ ያቀደዉ።ስፌን ፖለን የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

«በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የሐገሪቱን ጦር ማሰልጠን ግድ ነዉ።»አሉ የጀርመን መንግስት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት ትናንት፤ የሐገሪቱ ካቢኔ ወታደሮቹ እንዲዘምቱ መወሰኑን ሲያስታዉቁ።የሶማሊያ መንግሥት ጦር ግን፤ የፖለቲካ ተንታኝ ማቲያስ ቬበር እንደሚሉት ሠላም በማታዉቀዉ ሐገር ሠላም ከማስፈን አሁንም ሩቅ ነዉ።

«የሶማሊያ ጦር በመላ ሐገሪቱ ሠላም ማሰፈን የሚችሉ በቅጡ የተደራጁ ወታደሮች የሉትም።በሐገሪቱ አሁንም የተለያዩ ኃይላት ይዋጋሉ።በመንግሥቱም ዉስጥ ዉዝግብ አለ።»

ግጭት፤ ጥቃት፤ ሽብር የርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾም የዉሉ አምሽቶ እዉነታ ነዉ።ያም ሆኖ የመጀመሪያዉ የጀርመን የወታደሮች አማካሪ ጓድ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ ሞቃዲሾ ይንቀሳቀሳል።የጀርመንም ሆኑ የሌሎቹ የአዉሮጳ ሕብረት ወታደሮች የሚሠፍሩና የሚያሠለጥኑት በአፍሪቃ ሕብረት ጦር በጥብቅ በሚጠበቀዉ በሞቃዲሾ አዉሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ነዉ።

የሶማሊያ ጦር ከ12 ሺ እስከ 15 ሺ የሚደርሱ ወታደሮች አሉት ተብሎ ይታመናል።EUTM-Somalia በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የአዉሮጳ ሕብረት የአሠልጣኞች ተልዕኮ ማሠልጠን ከጀመረበት እንደ ጎርጎሮሳዉኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ ከ3600 በላይ የሶማሊያ ወታደሮች አስልጥኗል።ወደ ሞቃዲሾ የሚዘምቱት የጀርመን ጦር አባላት ከሥልጠናዉ ባሻገር የሶማሊያ ጦር አዛዦችን ሥለ ዉጊያ ሥልት ያማክራሉም።

ይሁንና የማማከሩ ምግባር መሳካቱን የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ይጠራጠራሉ።ምክንያታቸዉ የሶማሊያ ጦር ግልፅ አደረጃጃት የለዉም የሚል ነዉ።ማቲያስ ቬበር እንደሚሉት የሶማሊያ ጦር አደረጃጃትን ቅጥ ካሳጡት ዋናዉ በጎሳ ልይ የተመሠረተ መሆኑ ነዉ።

«የሶማሊያ ትልቁ ችግር የጎሳ መዋቅሯ ነዉ።ሶማሊያዊዉ ሥለ ሐገሩ ከማሰቡ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ለጎሳዉ ነዉ።ወታደሮቹም እንደ አንድ ጦር ባልደረብነታቸዉ ከአንዲት ሐገራቸዉ ይልቅ የየጎሳቸዉን ፍላጎትን የማስፈፀም ግድ አለባቸዉ።»

በጀርመኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ አጥኚ ወይዘሮ አኔተ ቬበር ከዚሕም እልፍ ብለዉ « የሶማሊያ ጦር በአብዛኛዉ የአንድ ጎሳ አባላትን መያዙ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል።» ባይ ናቸዉ።የደሞዝና የአበል አከፋፈልም የሶማሊያ ጦርን አንድነት ክፉኛ የሚፈታተኑ ችግሮች ናቸዉ።

ከአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ ደግሞ የችግሮች ሁሉ ትልቅ ችግር ነዉ።

ሶማሊያ የሠፈረዉ 22 ሺሕ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር (AMISOM) ከሶማሊያ መንግሥት ጦር ጋር በመሆን ደቡብና ማዕከላዊ ሶማሊያ ዉስጥ ከሸባብ ጋር ታጣቂዎች ጋር እየተፋለመ ነዉ።አሸባብ ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾን ለቅቆ ከወጣ፤ በተለይም ኪስማዩን የመሳሰሉ ሥልታዊ ከተሞችን ከተቀማ ወዲሕ ክፉኛ መዳከሙ ርግጥ ነዉ።ወይዘሮ አኔተ ቬበር እንደሚገምቱት የአሸባብ ተዋጊዎች ቁጥር ከሰወስት ሺሕ ወደ አንድ ሺሕ አሽቆልቁሏል።

ይሕ ማለት ሶማሊያ ሠላምና ፀጥታ ሰፈነባት-ፅንፈኛዉ ቡድንም አለቀለት ማለት አይደለም።እንዲያዉም አሸባብ የአላማ-ሥልቱን ለዉጦ-ከሞቃዲሾ-እስከ ናይሮቢ ማሸበሩ የተሳካለት ትላልቅ ከተሞችን ከለቀቀ በኋላ ነዉ።

«አሸባብ አሁን አላማዉ ግዛቶችን መቆጣጠር አይደለም።ሥልቱም ጥፋት ማድረስ፤ ብዙ አጥፍቶ ጠፊዎችን ማዝመት እና ማሸበር ነዉ።»

አሸባብ ከተሳካለት የጀርመን ወታደሮችን ለማጥቃት መሞከሩ አይቀርም።

«የጀርመን ወታደሮች ለአሸባብ የሚያስጎመዡ ዓሊማዎች ናቸዉ።የጀርመን ወታደሮች ከገድለ ግድያዉ በመላዉ ዓለም መገናኛ ዘዴዎች ሥለሚሰራጭ ለአሸባብ ፕሮፓጋንዳ ብዙ ጠቃሚ ነዉ።»

ይላሉ የፖለቲካ አጥኚ ማቲያስ ቬበር።

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic