ስፖርት፤ ጥቅምት 4 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 13.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥቅምት 4 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

ዳግመኛ እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል። ለሩዋንዳ «መልካም እድል» ብሎም ወደ ነበረበት ተመልሷል። ከተሰናበተበት የቻን ማጣሪያ በድጋሚ ተሰናብቷል፤ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን። ፌዴሬሽኑ ደግሞ እሰጥ አገባ ውስጥ ይገኛል። በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ድል ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:44

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ዳግመኛ እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል። ለሩዋንዳ አቻው «መልካም እድል» ብሎም ቀድሞ ወደ ነበረበት ተመልሷል። ከውድድሩ ከተሰናበተበት የቻን ማጣሪያ በድጋሚ ተሰናብቷል፤  የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን።  እሰጥ አገባ ውስጥ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ ደግሞ በአጠቃላይ ጉባኤው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫውን ለ45 ቀናት ማራዘሙ ተሰምቷል። በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ድል ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። 

አትሌቲክስ

ከ1500 ዓመት በፊት ማራቶን ሩጫ በተጀመረባት የግሪኳ አቴንስ ከተማ በተሰናዳው የአቴንስ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ የ18 ዓመት ወጣት በዳቱ ሂርጳ በዳኔ በአንደኛነት ድል ተቀዳጅታለች።  እጅግ ፈታኝ በነበረው የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አንደኛ የወጣችው 2 ሰአት ከ34 ደቂቃ ከ18 ሰከንዶች ሮጣ በመግባት ነው።

በወንዶች ፉክክር ኬንያውያን እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ጠራርገው ወስደዋል። በዚህ ፉክክር የ23 ዓመቱ ኬንያዊ ሣሙኤል ካላላይ አንደኛ ወጥቷል። ሣሙኤል  2 ሰአት ከ12 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ሮጦ ያሸነፈው የሀገሩ ልጅ ሚልቶን ኪፕላጋትን በመቅደም ነው። ግሪክ ውስጥ በተከናወነው የአቴንስ ማራቶን የሩጫ ውድድር ከዐሥር ግድም ሃገራት የተውጣጡ 18,500  ሯጮች ተሳታፊ ኾነዋል።

Marathon

በማራቶን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ490 ዓመተ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጠው ፋይዲፒደስ የተባለ አቴናዊ መልእክተኛ እንደሆነ ይነገራል። የማራቶን ሯጩ በያኔው አጠራር ፐርሺያዎች (ኢራኖች) ላይ የተገኘውን ድል ለማብሰር ሲልም ነበር ከማራቶን ከተማ ወደ አቴንስ 40 ኪሎ ሜትር ግድም ሲገሰግስ የደረሰው። ኾኖም በሞቃታማው የአየር ጠባይ በባዶ እግሩ ያላማቋረጥ በመገስገሱ እጅግ ከመዛሉ እና ከመዳቀቁ የተነሳ ፋይዲፒደስ አንዲት ቃል ብቻ ነበር መተንፈስ የቻለው። በግሪክኛ  (Nenikikamen) ሲል ተናገረ። «ደስ ይበለን ድል አድርገናል» እንደማለት ነው።  ይህን ብስራቱን ነግሮ እንዳበቃ ግን አፍታም አልቆየ፤ ወዲያው ሕይወቱ ማለፏ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። 

በሰሜናዊ ስፔን ተራራማዋ ጥንታዊት በኾነችው አነስተኛዋ ከተማ አታፑርካ በተከናወነ  አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል። በትናንቱ 14ኛው የአታፑርካ አገር አቋራጭ የሩጫ ፉክክር በወንድም በሴትም አሸናፊዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በወንዶች ፉክክር ጌታነህ ሞላ አሸናፊ ሲሆን፤ የዩጋንዳው ሯጭ ጃኮብ ኪፕሊሞ ሁለተኛ ወጥቷል። ሦስተኛ ደረጃን ያገኘው የኤርትራው አትሌት አሮን ክፍሌ ነው።   በሴቶች ውድድር ደግሞ ሰንበሬ ተፈሪ አሸናፊ ኾናለች።

እግር ኳስ

አፍሪቃውያን የሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ ተሰልፈው በሚጫወቱበት የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮና (CHAN) ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያገኘውን ሁለተኛ ዕድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሳይጠቀምበት ቀረ። ትናንት ሩዋንዳ ኪጋሊ ውስጥ በተከናወነው የመልስ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም ግብ አልተቆጠረም። ኾኖም ሩዋንዳ ቀደም ሲል አዲስ አበባ ውስጥ 3 ለ2 በማሸነፏ ሞሮኮ ውስጥ ወደሚከናወነው ውድድር ማለፍ ችላለች። ሁለቱ ቡድኖች ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በሱዳን  እንዲሁም ሩዋንዳ በኡጋንዳ ተሸንፈው ከማጣሪያው የወጡ ቢሆንም፤ ዳግመኛ ዕድሉን ያገኙት የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ መሳተፍ አለመቻሉን በመግለጡ ነበር። የቻን ውድድር ላይ 16 የአፍሪቃ ሃገራት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ውድድሩም ከጥር 4  እስከ 27 ቀን 2010 ዓም ድረስ ይከናወናል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት በሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን 3 ለ2 ተሸንፎ ከውድድሩ መውጣቱን በተመለከተ ትናንት በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ተከታታዮቻችን አስተያየት እንዲሰጡ ጋብዘን ነበር። አስተያየቶቹንም በዛሬው የስፖርት ዝግጅት እንደምናካትት ቃል በገባነው መሠረት የተወሰኑትን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።  በረከት ተካ በሰጠው አስተያየት፦ «የቤተሰብ ጥርቅም እንጂ የእግር ኳስ ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የለም» ብሏል። ዓማኑ ሰኢድ ደግሞ፦«የኢትዮጵያ እግር ኳሥ የኢትዮጵያ ህዝብን ጨጓራ በሽተኛ አደረገን። ወይ ኳሱ አይሻሻል ወይ እኛም ተሥፋ ቆርጠን አልተቀመጥን በተጫወተ ቁጥር መሸነፍ። እኛ ፍላጎታችን እና ጉጉታችን በጣም ከፍተኛ፤ እንዳው ምን ይሻላላል?» ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

«ብራቮ ታዲያ በሃይላንድ የሚደባደብ ፌዴሬሽን እየመራው ሊያልፍ! ኑሯል» ያለው ደግሞ ግሩም ቢኤም ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያከናውን በተመራጮች መካከል እሰጥ አገባ እና ግብግብ እንደነበር በቦታው እንደተገኙ የገለጡ ሰዎች ጽፈዋል።  የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት እና የትግራይ ክልልን በመወከል ለሥራ አስፈጻሚነት ተወክለው የነበሩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ አደረጉት የተባለው ንግግርም እጅግ አወዛግቧል። ጉባኤው ቀደም ሲል መቀሌ ውስጥ ሊደረግ ታስቦ እንደነበር ሆኖም ሰመራ የታሰበው ከሚዲያ ሽሽት መሆኑን በመግለጥ፤ ጉባኤው መቀሌ ከተማ የመኪያሄዱን አስፈላጊነት ከከተማው «ቆነጃጅት» ጋር አያይዘው መናገራቸው በተለያዩ የመገናኛ ዘርፎች ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸዋል።

በፌስቡክ ገጻችን ከተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች መካከል፦ እዮብ እስክስታ «ያልፋል ብላችሁ አስባችሁ ነበር እንዴ?» ሲል ጌታሰው መንገሻ ደግሞ «የት ሊደርስ ነበር» የሚል አስተያየት አስፍሯል። «ደግነቱ ጎሉ አልበዛም» ያለው ደግሞ ወንድሙ ወልደማርያም ነው። አቤ ለታ በአጭሩ «ግልግል» ብሏል።  

ለዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ዛሬ ማታ ጣሊያን ከስዊድን ጋር ሁለተኛ ዙር ግጥሚያዋን ታከናውናለች። ስዊድን ለመጨረሻ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ያለፈችው ከ11 ዓመት በፊት በ2006 ዓም ነው። አየርላንድ እና ዴንማርክ ነገ ማታ ይጋጠማሉ። ትናንት በተከናወኑ ግጥሚያዎች ስዊዘርላንድ እና ሰሜን አይርላንድን ያለምንም ግብ ቢለያዩም፤ ስዊዘርላንድ በደርሶ መልስ አሸንፋለች። በግሪክ እና ክሮሺያ ግጥሚያም ግብ መቆጠር ባይችልም፤ ክሮሺያ በድምር ውጤት 4 ለ1 አሸንፋለች።

አፍሪቃውያን ሃገራት ባከናወኑት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ግብጽ ከጋና ጋር ትናንት አንድ እኩል አቻ ተለያይታለች። ከምድቡ 13 ነጥብ ያላቸው ግብጾች ቀደም ሲል ኮንጎ ብራዛቪልን ያሸነፉ ጊዜ ነው ለዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡት።  ኮንጎ ከኡጋንዳ ጋርም በተመሳሳይ አንድ እኩል ነው የተለያየችው። ኡጋንዳ በምድቡ 9 ነጥብ ይዛ ፈርኦኖቹን ትከተላለች። በ2 ነጥብ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኮንጎን ጋና በአምስት ነጥብ ትበልጣለች፤ ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ አላለፈችም።

ዩናይትድ ስቴትስ በሴቶች ጣምራ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ከ2000ዓም ወዲህ  ማሸነፍ ችላለች። ዩናይትድ ስቴትስ 3 ለ2 ያሸነፈችው ቤላሩስን ነው። በብራዚል ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ደግሞ የፌራሪ አሽከርካሪው ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል አንደኛ ሲወጣ፤ ባቫልተሪ ቦታስ በመርሴዲሱ 2ኛ ደረጃን አግኝቷል። የ3ኛ ደረጃው ለፌራሪው አሽከርካሪ ኪም ራይኮነን ኾኗል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን በአራተኛናነት አጠናቋል። ኾኖም ሌዊስ ሐሚልተን የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን ያነሳው በሜክሲኮው ውድድር ነበር።

 ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic