ስፖርት፤ ጥቅምት 18 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.  | ስፖርት | DW | 27.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥቅምት 18 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው 16 እጩዎችን አወዳድሮ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን በፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧታል። በምርጫው የክልል መንግሥት ተጽዕኖ አርፏል ሲሉ አንዳንዶች አስተያየት ሰጥቷል። ምርጫውን በቅርበት የተከታተለች የስፖርት ጋዜጠኛ እና ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን በስልክ አነጋግረናል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት ባከናወነው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ 16 እጩዎችን አወዳድሮ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲል መርጧታል። ምርጫው ላይ የክልል መንግሥት ተጽዕኖ አርፏል ሲሉ አንዳንድ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። ምርጫውን በቅርበት የተከታተለች የስፖርት ጋዜጠኛ እና ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን በስልክ አነጋግረናል።  በጀርመን ቡንደስ ሊጋ  የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ቡድን የቁልቁለት ሽምጡን ተያይዞታል። ትናንትናም በሔርታ ቤርሊን ጉድ ኾኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልና ቸልሲ ነጥብ ሲጥሉ፤ አርሰናል ወሳኝ ሦስት ነጥብ ትናንት አግኝቷል። ማንቸስተር ሲቲ ብቻውን በቀዳሚነት እየገሰገሰ ነው።

በቅድሚያም አትሌቲክስ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት ባከናወነው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ወክላ የቀረበችው ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን በተቀዳሚት ምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል።  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሥራ አስፈጻሚነት በመመረጧ የተሰማትን ደስታ ስትገልጥ «ሴቶች አደርጋለሁ፤ እሠራለሁ ብለው ራሳቸውን ያቅርቡ። ራሳቸውን ለአመራርነት ያቅርቡ» የሚለውን መልእክትም በማከል ነው።

አፋርን ወክለው የቀረቡት ወ/ሮ ፎዚያ እድሪስም የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ተወስኗል።  ጋዜጠኛ ሃና ገ/ሥላሴ በኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ላይ የኦሎምፒያድ ስፖርት መሰናዶ ዋና አዘጋጅ ናት። ሃና በትናንቱ ምርጫ ሴት ባለሞያዎች ወደ ስፖርቱ አመራር ብቅ ማለታቸው ወደ አመራሩ ለመምጣት ለሚያስቡ ሌሎች ሴቶች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጣለች። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአንድ ወር በፊት ደብረዘይት ወይንም ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤውን አከናውኖ ነበር። በወቅቱ በይደር ከተያዙ ነጥቦች መካከል ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የአመራር ምርጫን በተመለከ የተነሳው ጥያቄ  አንዱ ነበር።  የትናንቱ አስቸኳይ ጉባኤም አንዱ ዓላማው ጥያቄዎቹን ውሳኔ ለመስጠት እንደነበር ተገልጧል። አምስት እና ከአምስት በላይ ቡድኖችን ያደራጁ የክልል ፌዴሬሽኖች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውስጥ ሁለት ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርጓል።  በተጨማሪም በሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሥራ ተዋረድ መሰረት ከፕሬዚዳንቱ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ መካከል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት እንዲካተት መደረጉንም ጋዜጠኛ ሃና አክላ ተናግራለች። 

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በደረጃ ሰንጠረዡ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ሁደርስፌልድን 2 ለ1 አሸንፏል።  አርሰናል በበኩሉ የትናንቱን ወሳኝ ጨዋታ ከበርንሌይን ጋር አከናውኖ በ1 ለ0 ድል አጠናቋል። ተቀናቃኞቹ ሊቨርፑል እና ቶትንሀም ሆትስፐርን በልጦም የአራተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ነገ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከዋትፎርድ እንዲሁም ኒውካስል ከዌስት ብሮሚች ጋር በተመሳሳይ ሰአት ይጋጠማሉ። 

የአርሰናሉ ተከላካይ ሎረን ኮሲይልኒ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ቶትንሀም ሆትስፐርን ከማሸነፉ ይልቅ ትናንት በርንሌይ ድል ማድረጉ የበለጠ ወሳኝ እንደነበር ተናግሯል። ሎረን የተጋጣሚዎቹን ብርታት አስመልክቶ ሲናገርም እንዲህ ብሎ ነበር፦ «እነሱም ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ነጥብ ነበር የነበራቸው፤ በዛ ላይ በጣም ቀጥ ያለ እግር ኳስ ነበር ሲጫወቱ የነበሩት። የሚያሻሟቸው ኳሶች በጣም ድንቅ ነበሩ፤ ከፊት ለፊትም በብቃት ግብ ማስቆጠር የሚችሉ የተወሰኑ ተጫዋቾች አሏቸው። ስለዚህ በጣም አስቸጋሪ ነበር።» 
በኤሚሬትስ ስታዲየም ሆትስፐርን 2 ለ0 ድል አድርገው የነበሩት መድፈኞቹ ትናንት በርንሌይን አሸንፈው ያገኙት ሦስት ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛነትን እንዲቆናጠጡ አስችሏቸዋል። ሊቨርፑል ከቸልሲ ጋር ባከናወነው የትናንቱ ግጥሚያ አንድ እኩል በመለያየቱ  ከደረጃው ዝቅ ብሏል። ቸልሲ በበኩሉ 29 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛነት ከሚከተለው ማንቸስተር ዩናይትድ በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።ማንቸስተር ሲቲ በ37 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በርቀት እየመራ ይገኛል። ቶትንሀም ሆትስፐር እና ሊቨርፑል 24 እና 23 ነጥብ ይዘው የአምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

 

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች እጅግ አስደማሚ የነበረው ዶርትሙንድ ከሻልከ ጋር ያከናወኑት ጨዋታ ነበር። ሻልከዎች በመጨረሻዎቹ የባከኑ ሰአቶች ባስቆጠሯቸው ግቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው ባየር ሙይንሽን ዝቅ ብሎ 2ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር አራት እኩል አቻ ወጥተዋል።  በዚህ ግጥሚያ ማሪዮ ጎይትሰ ቁርጭምጭሚቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህም የተነሳ ዳግም ከጨዋታ  ውጪ መቆየቱ የማይቀር ነው። በ12ኛው ደቂቃ ላይ በኦበሜያንግ የመጀመሪያውን ግብ አራተኛዋን ደግሞ በድንቅ ኹናቴ 25ኛው ደቂቃ ላይ በጌሬሮ ያስቆጠረው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የማታ ማታ ድል አልቀናውም። ከ61ኛው ደቂቃ አንስቶ በተከታታይ ባስቆጠራቸው አራት ግቦች ሻልከ አቻ በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። 

ሌላኛው በደረጃ ሰንጠረዡ ዝቅ ብሎ 15ኛ የሚገኘው የሰሜን ጀርመኑ ሐምቡርግ ቡድን ሆፈንሀይም ትናንት 3 ለ0 አሸንፏል።  የደረጃ ሠንጠረዡ ጠርዝ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቡድን ደግሞ ዳግም ሽንፈት ቀምሷል።  ኮሎኝ ትናንት 2 ለ0 ድል የተነሳው በሔርታ በቤርሊን ነው። ኮሎኝ በዚህ አያያዙ ከቡንደስሊጋው መሰናበቱ የማይቀር ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ


 

Audios and videos on the topic