ስፖርት፤ ጥቅምት 13 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.  | ስፖርት | DW | 23.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥቅምት 13 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ቡድኖች የየእግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ የደጋፊዎች ግጭት ታዳሚያን ጉዳት ደርሶባቸዋል። ኢትዮጵያውያቱ ተፎካካሪዎች በቶሮንቶ ማራቶን ድል ተቀዳጅተዋል። ብሪታንያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድር ዋንጫን ሊያነሳ ተቃርቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:04
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:04 ደቂቃ

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቶሮንቶ ማራቶን የሩጫ ውድድር፤ ኢትዮጵያውያቱ ተፎካካሪዎች ድል ቀንቷቸዋል፤ ከሦስተኛ ደረጃ በስተቀር ከአንደኛ እስከ አራተኛ ተከታትለው ገብተዋል። በወንዶች የሦስተኛነት ደረጃ ተገኝቷል። ብሪታንያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድር ዋንጫን ሊያነሳ ተቃርቧል። ሳምንት በሜክሲኮው ፉክክክር ካሸነፈ ለአራተኛ ጊዜ ድሉ የእሱ ይኾናል። ቡንደስ ሊጋ እና ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎችንም እንዳስሳለን።

በቅድሚያም አትሌቲክስ

እሁድ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቶሮንቶ ካናዳ ውስጥ በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ በድል አጠናቀዋል። በቶሮንቶ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ የኾነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማርታ መርጋ 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ሆናለች። በውድድሩ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሱቱሜ አሠፋ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች፤ ከማርታ በአንድ ደቂቃ ከሰባት ደቂቃ ነው የተበለጠችው። የሶስተና ደረጃውን ያገኘችው ሣራ ጀቤት የተባለች የኬንያ አትሌት ስትኾን እሷን ተከትላ ኢትዮጵያዊቷ ፋጡማ ሳዶ በአራተኛነት አጠናቃለች። 

በአንጻሩ ኬናያውያን ጎልተው በወጡበት የቶሮንቶ ማራቶን የወንድ አትሌቶች የሩጫ ፉክክር ፊልሞን ሮኖ ክብርወሰን በማሻሻል የአንደኛ ደረጃን ተጎናጽፏል። ፊልሞን አንደኛ የወጣው ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ የማነ ጸጋዬ ተይዞ የነበረውን ሰአት በሦስት ሰከንዶች በማሻሻል ነው። ፊልሞን ሮኖ በትናንቱ ፉክክር የገባበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ነው። ክብርወሰን በማሻሻሉ $50,000 ዶላር በአጠቃላይ  $115,000 ዶላር ይዞ ነው ወደ ሀገሩ የሚገባው።  በዚሁ ውድድር  ዲክሰን ቹምቤ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ደቅሲሳ  የሦስተኛነት ደረጃን አግኝቷል።


 
በ28ኛው ዓመታዊ የቶሮንቶ ማራቶን ሩጫ ወደ 25,000 ግድም ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸው ተገልጧል። ተወዳዳሪዎቹ በሦስት ዘርፍ ማለትም በአምስት ኪሎ ሜትር፤ በግማሽ ማራቶን እና በማራቶን ነው የተሳተፉት። ከ74 ሃገራት የተውጣጡ ሯጮች በተሳተፉበት ፉክክር ወደ 200 ግድም ካናዳ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች ለቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን  3,5 ሚሊዮን ዶላር ግድም መለገሳቸው ተዘግቧል።  

እግር ኳስ

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊዎች ግጥሚያ በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ረብሻ የደረሰው አይነት ጉዳት እንዳይከሰት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ ተገለጠ።  ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ0 ባሸነፈበት በአዲስ አበባ ስታዲየሙ የትናንቱ የእግር ኳስ ግጥሚያ  ታዳሚያን ወንበር እየነቃቀሉ በመወራወር ጉዳት ሲያደርሱ ታይተዋል። ጨዋታውን የተከታተለው የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ መራኄ አርታኢ ኦምና ታደለ በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች መጎዳታቸው እና ጨዋታው ደብዝዞ መጥፎ በኾነ ሁናቴ መጠናቀቁ ያሳዝናል ሲል ገልጧል። ኦምና በጨዋታው ወቅት ለየት ባለ መልኩ የታዘበውን በማብራራት «ጨዋታውን ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 ነው ያሸነፈው። ኮትዲቫራዊው አጥቂ ኢብራሒም ፎፋና ነበር ግቡን ያስቆጠረው። ዓምና በተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድንን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ እና የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ኢብራሒም ፎፋና ነበር ግቦቹን ያስቆጠረው። አሁንም ድጋሚ  ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን የዋንጫ ባለቤት አድርጓል።»


የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ሊቨርፑል በሳምንቱ መጨረሻ ነጥብ ሲጥል አርሰናል ድል ቀንቶታል። በአርሰናል 5 ለ2 አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው ኤቨርተን ቡድን አሰልጣኝ ሮናልድ ኮይማን መሰናበታቸው ዛሬ ተገልጧል። አሰልጣኙ የተሰናበቱት ቡድኑን ለተደጋጋሚ ሽንፈት ዳርገው ወደ ወራጅ ቃጣናው በማሽቆልቆላቸው ነው ተብሏል። ሆኖም ላለፉት 27 ዓመታት ቡድኑን ካሰለጠኑ  7 አሰልጣኞች ጋር ሲነጻጸር ሮናልድ ኮይማን በአማካይ ከሁሉም የተሻለ ነጥብ ነው ያላቸው። ኤቨርተን በ8 ነጥብ በ18ኛ ደረጃ ላይ ይገናኛል። 

በቶትንሀም ድንቅ ጨዋታ ተበልጦ 4 ለ1 የተረታው ሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ በበኩላቸው ለሽንፈታቸው መቶ በመቶ ተጠያቂው ቡድናቸው መሆኑን ተናግረዋል። የቶትንሀም ሆትስፐር ጨዋታን ያደነቁት አሰልጣኙ «በአንድ ግብ ልዩነት መሸነፍ ምንም ማለት አልነበረም፤ ልናስተካክለው እንችል ነበር» በማለት የ4 ለ1 ሽንፈቱን የቡድናቸው ድክመት ውጤት ነው ብለዋል። 

ቅዳሜ እለት በርንሌይን 3 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ በ25 ነጥቡ በደረጃው የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶትንሀም በእኩል 20 ነጥብ ሆኖም በአምስት ግብ ክፍያ ልዩነት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው ይከታተላሉ። ቸልሲ ከትናንት በስትያ ዋትፎርድን 4 ለ2 በማሸነፍ የሰበሰበው 3 ነጥቡ ተደምሮለት በጥቅል  16 ነጥብ ደረጃው አራተኛ ነው። አርሰናል በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ሊቨርፑል 13 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ 

የጀርመን ቡንደስ ሊጋ

እሁድ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከናወኑ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሦስት የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ደግሞ በአቻ ነጥብ ተጠናቀዋል። ከቬርደር ብሬመን ጋር የገጠመው ኮሎኝ ያለምን ግብ ተለያይቷል። ፍራይቡርግ እና ሔርታ ቤርሊን እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ከሆፈንሐይም አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። 

ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ እለት ሐምቡርግን 1 ለ 0 ቢረታም፤ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ሁለት እኩል የተለያየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል። 20 ነጥብ ይዞም በሦስት ግብ ክፍያ ልዩነት ባየር ሙይንሽንን የሚበልጠው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ጠንከር ማለቱ በርካታ ጨዋታዎች እየቀሩት የዋንጫ ባለቤት መሆን ለለመደው ባየርን ሙይንሽን ከወዲሁ ራስ ምታት ፈጥሯል። 


የመኪና ሽቅድምድም

ከፊታችን ገና ሦስት ቀሪ ውድድሮች እያሉ ብሪታንያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ዋንጫን ለአራተኛ ጊዜ ለማንሳት ተቃርቧል። ትናንት በዩናይትድ ስቴትስ ግራንድ ፕሪ ውድድር ጀርመናዊ ተፎካካሪው ሰባስቲያን ፌትልን በመቅደም በአንደኛነት ያጠናቀቀው ሌዊስ ሐሚልተን ውድሩን በ66 ነጥቦች በመምራት ላይ ይገኛል። 

የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ዘንድሮ ሊጠናቀቅ ሦስት ዙር ፉክክሮች ቢቀሩትም በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ በሚኖረው የሜክሲኮ ግራንድ ፕሪ ውድድር ሌዊስ ሐሚልተን ካሸነፈ የዋንጫው ባለቤት ይኾናል። በዘንድሮ የፎርሙላ አንድ አጠቃላይ ውድድር ሌዊስ ሐሚልተን 331 ነጥቦች ሲሰበስብ፤ የፌራሪ አሽከርካሪ ተፎካካሪው ሠባስቲያን ፌትል 265 ነጥቦች አሉት።  በሦስተኛነት ደረጃ ላይ የሚገኘው ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫልተሪ ቦታስ 244 ነጥብ ይዞ ሰባስቲያን ፌትልን እጅግ በቅርብ ርቀት ይከተለዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic