ስፖርት፤ ጥር 30 ቀን፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 08.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥር 30 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ማንቸስተር ዩናይትድ የማሸነፍ ዕድሉ የማታ ማታ በቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ መክኖበታል። አሠልጣኝ ቫን ጋል በጨዋታው ደስተኛ አለመሆናቸው ተገልጧል፤ በተለይ በተከላካዮቻቸው። በቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ በጥንካሬ የገሰገሰው ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋንጫውን ወስዷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:13 ደቂቃ

የጥር 30፤ 2008 ዓ.ም ዘገባ

አዘጋጇ ሀገር ሩዋንዳ በካፍ ተወድሳለች። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከታች ያደጉት ሁለት ቡድኖች ጥንካሬያቸውን እያሳዩ ነው። ሁለቱም አሸንፈዋል። በስፔን ላሊጋ ሪያል ሶሴዳድ ዛሬ ከስፓኞላ ጋር ይገጥማል። ትናንት ኃያላኑ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ አሸንፈዋል። ለዓመታት አቅሉን ስቶ የሚገኘው ዝነኛው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ተወዳዳሪ፤ ጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር የጤና ሁናቴ አንዳችም መሻሻል እንዳልታየበት ተነግሯል።

ቸልሲን በሜዳው ለመግጠም ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ያቀናው ማንቸስተር ዩናይትድ በትናንቱ ጨዋታ ከተጋጣሚው የተሻለ ብቃት አሳይቷል። ጄሲ ሊንጋርድ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል የተላከለትን ኳስ በድንቅ ኹናቴ ተቆጣጥሮ በመጠማዘዝ ከመረብ ሲያሳርፍ ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ አያያዙ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ነበር የሚመስለው። ኾኖም የጨዋታው 90ኛ ደቂቃ ተጠናቆ በባከነው ጭማሪ ሰአት ዲዬጎ ኮስታ ባስቆጠራት ግብ ቸልሲ ከመሸነፍ ድኗል፤ ማንቸስተር ዩናይትድ የማታ ማታ ድሉን ከእጁ አስነጥቋል። ቸልሲ በ30 ነጥብ ቁልቁል 13ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሌዊ ቫን ጋል ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በቢቢሲ ስፖርት ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «ድል ከእጃችን ነው ያመለጠው። ቡድናችን ድንቅ ነበር። ብዙ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር። እናም ያ ሲሆን የነበረብህ ማሸነፍ ነው። እስከ መጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ጥሩ ተጫውተናል። ብዙ ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ያን ግን አላደረግንም። እንዲያም ሆኖ ጨዋታውን በደንብ መቆጣጠር ይገባሃል። ያን አላደረግንም።» ብለዋል በቁጭት።

ማንቸስተር ዩናይትድ በደረጃ ሠንጠረዡ እስከ ሦስተኛ ድረስ በአስተማማኝ ነጥብ ለመዝለቅ ከቸልሲ ጋር ያደረጋቸውን አይነት ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻል እንደነበረበት አሠልጣኙ ጠቅሰዋል። «ባለፈውም ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ስንጫወት በባከነ ሰአት ተመሳሳሳይ ነገር ነበር የተከሰተው» ብለዋል። ለሽንፈታቸው ምክንያትም የተከላካዮች አለመቀናጀት እና ኳሱን በዘፈቀደ መለጋት፣ ዳኛው ተገቢ ያልሆኑ ቅጣት ምቶችን መስጠቱ እንዲሁም ኳሷን በአግባቡ አለመቆጣጠር እንደነበር ጠቅሰዋል።

አኹን ማንቸስተር ዩናይትድ ከመሪው ላይስተር ሲቲ በ12 ነጥብ ርቀት ዝቅ ብሎ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዋትፎርድን 1 ለምንም ያሸነፈው ቶትንሐም ሆትስፐር በ48 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ተቆናጧል። አርሰናል በተመሳሳይ ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ ነው። ትናንት በርንመውስን 2 ለዜሮ ድል አድርጎታል። በሣምንቱ ማሳረጊያ ከባድ ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ሲቲ 47 ነጥብ ይዞ አራተኛ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት በላይስተር ሲቲ 3 ለ1 ድባቅ ተመቷል። የማንቸስተር ሲቲን ሽንፈት ተከትሎ፦ ጋዜጦች «ይኼኔ ነው የፔፕ ጓርዲዮላ አስፈላጊነት» ሲሉ በቡድኑ ተሳልቀዋል። የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ማብቂያ ላይ ማንቸስተር ሲቲን ሊያሰለጥኑ ወደ እንግሊዝ ያቀናሉ።የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ቡድናቸውን ወደፊት ለፔፕ ጓርዲዮላ እንደሚያስረክቡ መግለጣቸው በተጫዋቾቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሳይፈጥር አልቀረም ተብሏል። ፔፕ ጓርዲዮላ ወደ እንግሊዝ እንደሚያቀኑ ይፋ መኾኑ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ላይ ሌላ ጫና ፈጥሯል።

ቅዳሜ ዕለት ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር ባደረጉት ግጥሚያ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታቸው ግራ በመጋባት የተዋጠ ነበር። ባየር ሙይንሽኖች በጨዋታው ፍፃሜ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል። ሆኖም ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በ53 ነጥብ ቡንደስ ሊጋውን እየመራ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ከሔርታ ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ45 ነጥብ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከባየር ሙይንሽን ጋር የ8 ነጥብ ልዩነት አላቸው። ሔርታ ቤርሊን በ35 ነጥብ ሦስተኛ ነው።

በቡንደስ ሊጋው ከታች ያደጉት ዳርምሽታድት እና ኤንግሎሽታድት ትናንት እና ከትናንት በስትያ አሸንፈዋል። ዳርምሽታድት ትናንት 2 ለዜሮ ድል ያደረገው ሆፈንሐይምን ነው። ኢንግሎሽታድት ደግሞ አውስቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል።

በስፔን ላሊጋ መሪው ባርሴሎና ትናንት ሌቫንቴን 2 ለባዶ ድል አድርጓል። ዳቪድ ናቫሮ በ21ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ግብ በራሱ ቡድን ላይ አስቆጥሯል። ሉዊስ ሱዋሬዝ ማሳረጊያዋን ሁለተኛ ግብ በመደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ማብቂያ 91ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል። ሊዮኔል ሜሲ ብቃት በተሞላበት ሁኔታ ወደፊት ገፍቶ የላካትን ኳስ ሉዊስ ሱዋሬዝ ግብ ጠባቂው ባጠበበበት በኩል በመላክ ውብ በሆነ መልኩ ነበር ያገባው።ሪያል ማድሪድን እሁድ በተመሳሳይ ውጤት ግራናዳን 2 ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ለሪያል ማድሪድ በ30ኛው ደቂቃ ካሪም ቤንዜማ የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። በ60ኛው ደቂቃ ላይ ግን የግራናዳው ዩሱፍ ኤል አራቢ በግብ ጠባቂው እግር ስር የላካት ኳስ ግራናዳ አቻ ለማድረግ ችላለች። በ85ኛው ደቂቃ ሉካ ሞድሪች ከርቀት አክርሮ የለጋት ኳስ ከመረብ ያረፈችው በድንቅ ኹኔታ ነበር።

ላሊጋውን ባርሴሎና በ54 ነጥብ ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ51 ይከተላል። ቅዳሜ ዕለት አይባርን 3 ለ 1 አሰናብቶታል። ሪያል ማድሪድ በ50 ይሰልሳል።

ሩዋንዳ ባዘጋጀችው የዘንድሮው ቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የዋንጫው ባለቤት ለመኾን ችሏል። የ19 ዓመቱ ወጣት የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ አጥቂ ኤሊያ ሜቻክ ዶምቦስኮ በስተግራ በኩል ኳሷን እየገፋ በፍጥነት በማምራት ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ እጅግ ድንቅ ነበረች። ኤሊያ ወደ ግራ በኩል ያጠበበውን የግብ ጠባቂውን አቋቋም በማየት በግራ በኩል ኾኖ በቀጥታ ወደ ግቡ የቀኝ አቅጣጫ የላካት ኳስ መረቡ ላይ ማረፍ ችላለች። የመጀመሪያ ግቧ የተቆጠረችው ጨዋታው በተጀመረ 29ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

34ኛው ደቂቃ ላይ ማሊዎች ጥሩ የግብ ዕድል አምልጧቸዋል። በስተቀኝ በኩል የተመታችው ቅጣት ምት በተከላካይ ብትመለስም፤ ከሰላሳ ሜትር ርቀት ገደማ በቀጥታ ወደ ግብ የተላከችውን ኳስ ግብ ጠባቂው ላይ ማታምፒ በድንቅ ሁናቴ አየር ላይ ተንሳፎ በቡጢ በመደለቅ ግብ ከመኾን አድኗል። ተደጋጋሚ የማሊ ሙከራዎችን ማጨናገፍ የቻለው ይኽ የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግብ ጠባቂ ቡድኑ ዋንጫውን በእጁ ሲያስገባ እሱም ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተሸልሟል።በ62ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋንም ግብ ያስቆጠረው ኤሊያ ሜቻክ በውድድሩ በአጠቃላይ 4 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ተመርጧል። ምርጥ ተጨዋች ተብሎም የተሸለመው ይኸው የ19 ዓመት ወጣት ነው። ለዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሦስተኛዋን ግብ በ73ኛው ደቂቃ ላይ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ከመረብ ያሳረፈው ደግሞ ጆናታን ቦሊንጊ ነው። ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለው ግን ኤሊያ ሜቻክ ነበር።

ሀገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ማሰለፍ በሚፈቀድበት በዚህ ግጥሚያ ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 ሃገራት ተሳትፈውበታል። ውድድሩ የሀገር ውስጥ የሊግ ቡድኖችን ጥንካሬ መፈተሻም ነው። ለሦስት ሣምንታት በዘለቀው ውድድር ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በፍፃሜው ማሊን ገጥሞ 3 ለ ዜሮ በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል። የመጀመሪያውን ውድድርም ከ7 ዓመታት በፊት ያሸነፈው ይኸው ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነበር። የመጀመሪያውን ውድድር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ዓመት ያስተናገደችው ኮትዲቯር ትናንት ለደረጃ በተደረገው ግጥሚያ ጊኒን 2 ለ1 በማሸነፍ ሦስተኛ ወጥታለች።

ሩዋንዳ ውስጥ የተከናወነው የዘንድሮው የቻን ውድድር ከአንድ ክስተት ውጪ ስኬታማ እንደነበር ተጠቅሷል። የሩዋንዳ ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የመገናኛ አውታሮች ግንኙነት ባለሙያ ቦኒ ሙጋቤ በእርግጥም ዝግጅቱ ስኬታማ ነበር ብለዋል።

«መንግሥት ሁሉም አቅርቦት በጊዜ መሟላቱን ለማረጋገጥ በተቻለ አቅም የበኩሉን ለማድረግ ሞክሯል። የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች እና ሆቴሎች ሌላው ቀርቶ የመጓጓዣ አቅርቦቱ የተሟላ ነበር። ሁሉም ነገር በውድድሩ መሟላቱ ለሩዋንዳ ስኬት ነው። ይኽን ካፍ ከጥቂት ቀናት በፊት ባኪያሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጧል።»

በእርግጥም የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (CAF) በሩዋንዳው የቻን ውድድር ዝግጅት መደነቁን እና መደሰቱን አስታውቋል። 24 ሚሊዮን ወጪ የተደረገበት ውድድር ላይ የተከሰተው እንከን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በምድብ ግጥሚያው ከካሜሩን ጋር ሲገናኝ ለ15 ደቂቃዎች መብራት መቋረጡ ነበር።

የኢትዮጵያ ቡድን በዚህ ውድድር የዋንጫው ባለቤት ከኾነው ከዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨምሮ በምድቡ ሦስት ጨዋታዎችን አከናውኖ አንድም አላሸነፈም። አንድ ግብ በማስቆጠር አንድ ጊዜ አቻ ሲወጣ፤ አምስት ግቦችን አስተናግዶ፤ በአንድ ነጥብ ተወስናም የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ መሰናበቱ ይታወሳል። የፍፃሜውን የዋንጫ ግጥሚያ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና በርካታ ሩዋንዳውያን ስታዲየም ታድመው መከታተላቸውም ተዘግቧል።

በመኪና ሽቅድምድም ዝነኛ የነበረው ጀርመናዊ ሚሻኤል ሹማኸር በበረዶ ሲንሸራተት ራስ ቅሉ ተጎድቶ የአልጋ ቁራኛ ከኾነ 2 ዓመታትን አስቆጥሯል። ሚሻኤል ሹማኸር በወቅቱ የደረሰበት የራስ ቅል አደጋ «በሚያሳዝን መልኩ ሕይወቱን አበላሽቶታል» ሲሉ ጣሊያናዊው የፌራሪ ሥራ አስኪያጅ ሉካ ዲ ሞንቴሴሞሎስ ገልጠዋል። ዝርዝር ማብራሪያ ግን አልተሰጠም።

የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን (DFB) ፍራንስ ቤከን ባወርን እና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽንን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) ለመክሰስ መዘጋጀቱን አስታውቋል። የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክሱን የሚጀምረው የ25 ሚሊዮን ዩሮ ጉዳት እንዳይደርስበት መኾኑን ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ


Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች