ስፖርት፤ ጥር 21 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 29.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥር 21 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

በሳምንቱ መጨረሻ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎችን ሲያከናውኑ የነበሩ የእንግሊዝ ቡድኖች ከነገ ጀምሮ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። አርሰናል እና ሊቨርፑል ስዋንሲ ሲቲን እና ሁደርስፌልድን ይገጥማሉ። በቡንደስሊጋው 31 ነጥብ ይዞ በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዋና አጥቂውን ለአርሰናል ሊያስረክብ ጫፍ ደርሷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:16

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል የደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ስዋንሲ ሲቲን ነገ ይገጥማል። ዌስትሀም ዩናይትድ ክሪስታል ፓላስን በተመሳሳይ ሰአት ይፋለማል። 42 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው አርሰናል የነገው ጨዋታ ሊቀለው ይችል ይሆናል። የነገውን ጨዋታም አርሰናል ቢያሸንፍ ለጊዜው ከቶትንሀም ጋር እኩል ነጥብ ይኖረዋል።  45 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያደርገው ረቡዕ እለት ነው።

በ53 ነጥቡ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በሁለተኛነት ጉብ ካለው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ቶትንሀም ከባድ ፈተና ሳይገጥመው አይቀርም። ቶትንሀም በኤፍ ኤ ካፕ አራተኛ ዙር ግጥሚያ ቅዳሜ እለት ከኒውፖርት ካውንቲ ጋር የተለያየው አንድ እኩል ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ በሚገኘው ስዋንሲ ሲቲ ባለፈው ሳምንት ሰኞ  የ1 ለ0 ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠመው ሊቨርፑል ነገ ከሁደርስፊልድ ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ ምን እንደሚጠብቀው ዐይታወቅም። ሊቨርፑል በኤፍ ኤ ካፕ የቅዳሜ ግጥሚያ በዌስት ብሮሚች 3 ለ2 መሸነፉ አይዘነጋም። 47 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ከነገ በስትያ ዳግም ያልተጠበቀ ሽንፈት ከገጠመው በፕሬሚየር ሊጉ ቦታውን ለቶትንሀም ለማስረከብ ይገደዳል።

በፕሬሚየር ሊጉ 50 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ በርንመስን፤ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ዌስትብሮሚችን ከነገ በስተያ ምሽት ላይ ይገጥማሉ። ማንቸስተር ሲቲ ከቸልሲ በ15 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። በነገራችን ላይ በትናንቱ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ቸልሲ ኒውካስልን 3 ለ0፤ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ካርዲፍን 2 ለ0 ድል አድርገዋል።

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ማይንትስን ትናንት 2 ለ0 ድል የነሳው ባየር ሌቨርኩሰን የፊታችን ቅዳሜ ከመሪው ባየር ሙይንሽን  ጋር ይጋጠማል። 34 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን የቅዳሜው ጨዋታ እንደትናንቱ የሚቀለው አይሆንም። በትናንቱ ጨዋታ ማይንትስን ያሸነፈው ባየር ሌቨርኩሰን ቡድን አሰልጣኝ  ሐይኮ ሔርሊሽ ቡድናቸው በጨዋታው ጎልቶ መውጣቱን ተናግረዋል። ኾኖም ግን ተጨዋቾቻቸው የተሻለ መጫወት እና ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ይችሉ እንደነበር አልሸሸጉም።

«ኳሱን በብዛት ተቆጣጥረን ነበር፤ ብዙ እድሎችም አጋጥሞን ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሦስት ግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎች አግኝተን ነበር። ከ2 ለ0ም በላይ ግብ ማስቆጠር፤ የተሻለም መጫወት እንችል ነበር። በዚህም አለ በዚያ ግን ጨዋታውን በበላይነት ተቆጣጥረናል። ማይንትሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ በሚባል መልኩ ተከላክለዋል፤ እኛም ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ ለመግባት በእውነት አስቸጋሪ ኾኖብን ነበር። እንዲያም ኾኖ ግን ወደ መጨቸረሻዎቹ ላይ በጣም ጥሩ ተጫውተናል። ወሳኙ ነገር አስተማማኝ ግቦችን ማስቆጠራችን ነው። ስለዚህ ድሉ ጥሩ የሚባል ነው።»

በትናንቱ ግጥሚያ የባየር ሌቨርኩሰን ሁለት ታዋቂ ተጨዋቾች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ላርስ ቤንደር እና ጁሊያን ባውምጋርትሊንገር የደረሰባቸው ጉዳት ለረዥም ጊዜ ከጨዋታ ውጪ እንደማያደርጋቸው ቡድናቸው ዛሬ አስታውቋል። ባየር ሌቨርኩሰን ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ ተጨዋቾች በቂ ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን በዚህ ሳምንት ውስጥ ልምምድ እንደሚጀምሩ አስታውቋል። ምናልባትም ከፍራይቡርግ ጋር በሚኖረው የቅዳሜው ግጥሚያ ሊሰለፉ ይችላሉ።

ከመሪው ባየር ሙይንሽን በ16 ነጥብ ልዩነት ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን ትናንት ድል ሲቀናው፤ ሐኖቨር ግን አልተሳካለትም። ሐኖቨር በቮልፍስቡርግ 1 ለ0 ተገኝቷል። በመከላከል ላይ አተኩሮ የነበረው ቮልፍስቡርግ ምንም እንኳን የትናንቱን ጨዋታ ማሸነፍ ቢሳካለትም ከ13ኛ ደረጃው ግን ፈቅ ለማለት አልኾነለትም። በቮልፍስቡርግ የተሸነፈው ሐኖቨር ቡድን አሰልጣኝ አንድሬ ብራይተንራይተር ቡድናቸው በቀላሉ በመሸነፉ ደስተኛ አለመኾናቸውን ገልጠዋል።

«እጅግ በመከላከል ላይ የተመሠረተ አሰላለፍ ይዞ የገባ ቡድን ነው የገጠመን። በመከላከል ላይ ብቻ ነበር ያተኮሩት። በክንፍ በኩል ያደረግነው ሙከራ በሚያሳዝን መልኩ የተሻማችው ኳስ በአግባቡ አልደረሰችም፤ ግን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ብዙ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር። ምን ያደርጋል በሁለተኛው አጋማሽ በተገኘ አንድ ሙከራ ሽንፈት ገጠመን። ሲበዛ የማይታመን ነው።»

በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን በ50 ነጥብ ሲመራ፤ባየር ሌቨርኩሰን በ34 ይከተላል። ሻልከ በተመሳሳይ ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 33 ነጥብ ያለው አይንትራኅት ፍራንክፉርትን ላይፕሲሽ በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በአምስተኛ ደረጃ ይከተላል።

የቦሩስያ ዶርትሙንድን ተጨዋቾችን ይዞ በሚጓዝ አውቶቡስ ላይ የፍንዳታ ጥቃት ያደረሰው የ28 ዓመቱ ተጠርጣሪ የክስ ሒደት ዛሬ ጀርመን ውስጥ ታይቷል። በፍርድ ቤት ውሎው የዶርትሙንዱ ተከላካይ ማርክ ባርትራ በርካታ ሚስማሮች እና ስለታማ ነገሮች የታጨቁበት ጓዳ ሠራሽ ቦንድ የአውቲቡሱን መስኮቶች ሲያረግፍ የምሞት መስሎን ነበር ብሏል። ሠርጌቭ በሚል ስም የሚታወቀው የ28 ዓመቱ ተጠርጣሪ አውቶቡሱ ላይ ጥቃት ቢያደርስም ተጨዋቾቹ ላይ ግድያ ለመፈጸም አስቦ እንዳልነበር ባለፈው ወር ተናግሯል። ተጠርጣሪው በወቅቱ ጥቃቱን ያደረሰው በኢንተርኔት የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ነበር።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ፒየ ር ኤመሪክ ኦባማያንግም ለምስክርነት መገኘት ይገባው ነበር። ኾኖም የቡድኑ ጠበቃ አልፎንስ ቤከር ኦባማያንግ «በሕመም ምክንያት» መገኘት አለመቻሉን ተናግረዋል። ፒየ ር ኤመሪክ ኦባማያንግ  ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ እንግሊዙ አርሰናል ቡድን በ63 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ሊዘዋወር መኾኑን ዛሬ የተለያዩ ጋዜጦች ዘግበዋል። በኦባማያንግ ምትክ በአሁኑ ወቅት ቻይና ውስጥ የሚጫወተው የኮሎኙ አንቶኒ ሞዴስተ ወደ ዶርትሙንድ ለማስመጣት ድርድር መጀመሩ ተገልጧል።

የሜዳ ቴኒስ

በአውስትራሊያ ዓመታዊው ታላቅ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ስዊዘርላንዳዊው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ሮጀር ፌዴሬርስ ትናንት ታሪክ ሠርቷል። በዓመታዊው ታላቅ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ለ30ኛ ጊዜ ለፍጻሜ መድረስ የቻለው የ36 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊ የትናንቱ ድሉ 20ኛ ኾኖ ተመዝግቦለታል። ሮጀርስ ፌዴሬር ትናንት በአምስት ዙር   ግጥሚያ  ያሸነፈው የክሮሺያው ተጋጣሚ ማሪን ቺሊችን  ነው። በዚህ ውጤቱ መሠረትም፦ ሮጀርስ ፌዴሬር የአጠቃላይ ዓመታዊ ታላላቅ ውድድሮች ድምር ውጤቱ ከመሪው ስፔናዊው ራፋኤል ናድል ጋር አቀራርቦታል። ራፋኤል ናድል በሜልቦርኑ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ነው ከውድድር የወጣው። ሮጀር ፌዴሬር በአውስትራሊያ ግራንድ  የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የትናንት ድሉ 20 ጊዜ በማሸነፍ እነ ሴሬና ዊሊያምስ፣ ማርጋሬት ኮርት እና ሽቴፊ ግራፍን ተቀላቅሏል። በነገራችን ለይ ሌላኛው የዓለማችን ድንቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ዛሬ ይፋ በኾነው አጠቃላይ ነጥብ መሠረት 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic