ስፖርት፤ ጥር 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 25.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥር 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት እየገሰገሰ ነው። ሊቨርፑል ኖርዊችን በሜዳው እስከመጨረሻው ተናንቆ ነጥብ ነጥቆ ተመልሷል። አርሰናል እታች በሚዋዥቀው ቸልሲ ጉድ ኾኗል። ሪያል ማድሪድ ነጥብ ጥሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ሰኞ ጥር 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም ከአንጎላ ጋር ተጫውቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:26
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:26 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በመፋለም ኖርዊች ሲቲን በሜዳው 5 ለ4 አሸንፎታል። ለጀርመናዊው አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት የመጀመሪያው ድል ኾኖ ተመዝግቦላቸዋል። በባከነ ሰአት 5ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ግብ ለድል የበቃው ሊቨርፑል አሠልጣኝ ከዓይናቸው የማይለየው መነፅራቸው በስተመጨረሻ ተሰብሯል። «ለነገሩ ኹለት መነፅሮች ነው ያሉኝ» ያሉት አሠልጣኝ «ኾኖም» ሲሉ ቀጠሉ፤ «ኾኖም መነጽርን ያለመነጽር መፈለግ ትንሽ ያስቸግራል» ሲሉ በቀልድ መልክ ደስታቸውን ገልጠዋል።

ላይስተር ሲቲ ስቶክ ሲቲን 3 ለባዶ በማሸነፍ የመሪነቱን ቦታ ከአርሰናል ዳግም ተረክቧል። 47 ነጥብ አለው። ማንቸስተር ዩናይትድ በሳውዝሐምፕተን 1 ለዜሮ ተሸንፏል። ዋትፎርድ ኒውካስትልን 2 ለ 1 ድል አድርጓል። ዌስት ብሮሚች ከአስቶን ቪላ 0 ለ 0፤ ሠንደርላንድ ከበርንማውስ አንድ እኩል እንዲሁም ዌስትሐም ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር 2 ለ2 ተለያይተዋል። ነጥብ የተጋራው ማንቸስተር ሲቲ በ44 ነጥብ ሁለተኛ ነው።በ10 ተጨዋች ለመጫወት የተገደደው አርሰናል ትናንት በሜዳው በቸልሲ 1 ለባዶ ድል በመደረጉ ከአንደኛ ደረጃ ወደ ሦስተኛ ወርዷል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚለያየው ግን በግብ ክፍያ ብቻ ነው። ከዋንጫ ሽሚያው መራቃቸው ገና ድሮ የተረጋገጠላቸው ቸልሲዎች አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ካሰናበቱ በኋላ በሰባት ጨዋታዎች አልተሸነፉም። በ28 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ስዋንሲ ትናንት ኤቨርተንን 2 ለ1 አሸንፏል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ዐርብ እለት ሌቫንዶቭስኪ ባስቆጠራቸው ግቦች ሐምቡርግን 2 ለ1 በመርታት የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ በተከታታይ ለአራት ዓመታት በመውሰድ የመጀመሪያው ቡድን ለመኾን ግስጋሴውን ቀጥሏል። 41 ነጥብ ይዞ የሚከተለው ቦሩሲያ ዶርትሙንድን በ8 ነጥብ ርቆታል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከትናንት በስትያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 ሸኝቶታል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሔርታ ቤርሊን ባየር ሙይንሽን ላይ ለመድረስ 16 ነጥቦች ይቀሩታል። ለመድረስ የሚደረገው ሩጫ ግን የኅልም ነው።

ወደ ቡንደስ ሊጋው ያደገው ዳርምሽታትድ ቅዳሜ ዕለት ሐኖቨርን 2 ለ1 ረትቷል። ዳርምሽታድትን ተከትሎ ወደ ቡንደስሊጋው ዘንድሮ የገባው ኢንግሎሽታድትም ድል ቀንቶታል። ማይንትስን 1 ለምንም ለማሸነፍ ችሏል። ኮሎኝ በሽቱትጋር 3 ለ1 ድል ተነስቷል። ሔርታ ከአውስቡርግ ያለምንም ግብ ሲለያዩ፤ ሆፈንሃይም እና ሌቨርኩሰን አንድ እኩል ወጥተዋል። ትናንት ቬርደር ብሬመን እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት ድል ቀንቷቸዋል። ብሬመን ሻልከን 3 ለ1፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 ማሸነፍ ችለዋል።በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ግስጋሴውን ቀጥሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ቅዳሜ ዕለት ማላጋን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 48 አድርሷል። አትሌቲኮ ማድሪድ በግብ ልዩነት ባርሴሎናን ይከተላል። ከሴቪላ ጋር ትናንት ያደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። ትናንት ከቤቲስ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ የተጋራው ሪያል ማድሪድ 44 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው። ዲፖርቲቮ ላኮሩኛ ከቫለንሺያ ጋር አንድ እኩል ሲወጣ፤ አትሌቲኮ ቢልባዎ አይበርን 5 ለ2 አንኮታኩቶዋል። ዛሬ ማታ ሌቫንቴ ከላፓልማ ጋር ይፋለማል።

አፍሪቃውያን የሀገር ውስጥ እግር ኳስ ተጨዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የቻን ውድድር ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በምድብ ለ አንድ ነጥብ ይዛ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ በዜሮ ነጥብ ከወዲሁ መሰናበቷን ካረጋገጠችው አንጎላ ጋር ዛሬ ተጫውታለች። በ6 ነጥብ እና በ5 ንጹሕ ግቦች ምድቡን የሚመራው የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ማለፉን አረጋግጧል። በተመሳሳይ ሰአት ከአንጎላ ጋር የመጨረሻ ጨዋታውን አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አቋም ምን ይመስላል? ጥንካሬ እና ድክመቱ እንዴት ይታያል? በአጭር ጊዜ ውስጥስ ምን መደረግ አለበት? ጨዋታዎቹ ከመጀመራቸው ከሰአታት በፊት ከጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጌ ነበር። ኢብራሒም የቀድሞው የአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ነው። የኢትዮጵያ ብሔታዊ ቡድን እስካሁን ያደረጋቸው ጨዋታዎች ሊጋችን የት እንዳለ አመላካች ነው ሲል ያብራራል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዛሬ ተሰላፊዎች እነማን እንደኾኑ ፌዴሬሽኑ በኢሜል መልእክቱ አስታውቋል። እነሱም፦ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ ስዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባየህ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ አሥራት መገርሣ፣ ተስፋዬ አለባቸው፣ ራምኬል ሎክ፣ በኃይሉ አሠፋ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና ሙሉዓለም ጥላሁን ናቸው።

Keiner wie der Andere...የስፖርት አልባሳትን በማምረት የሚታወቀው የጀርመኑ ግዙፍ ኩባንያ አዲዳስ፥ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ ማኅበር ጋር የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር የማስታወቂያ ውል ማቋረጡን ይፋ አድርጓል። አዲዳስ ከማኅበሩ ጋር የነበረው 33 ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የስፖንሰርነት ውል ሊያበቃ ገና ሦስት ዓመታት ይቀሩት ነበር። አዲዳስ ውሉን ያቋረጠው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ ማኅበር በሰውነት አበረታች ቅሌት እና ሙስና መዘፈቁ ባለፈው ሣምንት ይፋ በመኾኑ ነው። የአትሌቲክስ ማኅበሩ እና የማስታወቂያ ሸሪኩ ዴንትሱ ውሉ በመቋረጡ 10 ሚሊዮን ዶላር ያጣሉ ተብሏል።

በተያያየዘ ዓለም አቀፍ የስፖርት ቅሌት ጀርመን የዛሬ 16 ዓመት የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ደቡብ አፍሪቃን በጠበበ ልዩነት ያሸነፈችው በሙስና ነው የሚለውን ክስ የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ (FBI)እየተመለከተው መኾኑ ተገልጧል። በሙስና ቅሌቱ የ6.7 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈጽሟል በመባሉ፤ የያኔው የዓለም ዋንጫ የጀርመን አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበረው ፍራንስ ቤከን ባወር ሥራውን መልቀቁ ይታወሳል። ቤከን ባወርም ኾነ እሱን ተከትለው ሥልጣናቸውን የለቀቁት የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዎልፍጋንግ ኒርስባኅ ክሱን አስተባብለዋል። ቅሌቱ የቀድሞ የፊፋ ምክትል ፕሬዚዳንት ጃክ ዋርነር ከዩናይትድ ስቴትስ የመባረር ጥላ እንዲያጠላባቸው አድርጓል። የ72 ዓመቱ ጃክ ዋርነር ላለመባረር በክርክር ላይ ናቸው።

በብሪታንያ የሜዳ ቴኒስ ታሪክ ከ32 ዓመታት ወዲህ አንዲት ተወዳዳሪ በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ለሩብ ፍፃሜ ማለፍ ችላለች። ከዝነኞቹ ሴሬና ዊሊያምስ እና ማሪያ ሻራፖቫ ጋር ለሩብ ፍፃሜ ያለፈችው ዮሐና ኮንታ ትባላለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic