ስፖርት፤ ጥር 11 ቀን፣ 2012 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 20.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥር 11 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የቡሩንዲ አቻውን በ5 ለ0 ሰፊ ልዩነት ድል አድርጓል።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሞ ሳላህ የባከነ ሰአት ግብ ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድን 2 ለ 0 አሸንፎ በዋንጫ ግስጋሴው ገፍቶበታል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 1 ደረጃ ዝቅ ሲል ባየር ሙይንሽን ከፍ ብሎ ደረጃውን ተረክቦታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:09

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሳምንቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የቡሩንዲ አቻውን አምስት ለዜሮ በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርጓል።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሞ ሳላህ የባከነ ሰአት ግብ ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድን 2 ለ 0 ድል አድርጎ በዋንጫ ግስጋሴው ገፍቶበታል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አንድ ደረጃ ዝቅ ሲል ባየር ሙይንሽን ከፍ ብሎ ደረጃውን ተረክቦታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድም ቀንቶታል። በሜዳ ቴኒስ የአውስትራሊያ ግጥሚያ የ15 ዓመቷ ታዳጊ ዕውቋን አሜሪካዊት የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ድል ነስታታለች።  

እግር ኳስ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የሴቶች የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ የመጀመሪ ዙር ግጥሚያዎች ኢትዮጵያ እና የምዕራብ አፍሪቃዊቷ ጊኒ ቢሳዎ ከሜዳቸው ውጪ አስተማማኝ ድል አስመዝግበዋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ ከሜዳው ውጪ ቡጁምቡራ ከተማ ልዑል ርዋጋሶሬ ስታዲየም ውስጥ ከብሩንዲ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ  5 ለ0 አመርቂ ድል አስመዝግቧል። ብሔራዊ ቡድኑ ይኽን ድል ያስመዘገበው የዝግጅት ጊዜ ማጠር ችግሮች እንደገጠመው በተነገረበት ወቅት ነው።  

እንደ ኢትዮጵያ ኹሉ ጊኒ ቢሳዎም ማውሪታንያን በሜዳዋ ኑዋክቾት ስታዲየም 6 ለ0 ነው የግብ ጎተራ አድርጋ ኩም ያደረገቻት። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ሌሎች ግጥሚያዎች ቡርኪና ፋሶ በመዲናዋ ዋጋዱዱጉ ጋምቢያን 3 ለ2፤ ደቡብ አፍሪቃ ዛምቢያን በሜዳዋ ሉሳካ ከተማ ውስጥ 2 ለ0 ሲያሸንፉ፤ ማላዊ እና ዚምባብዌ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ጋቦን ከዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ጋር የነበራት ግጥሚያ ባለቀ ሰአት በኮንጎ ከውድድሩ መውጣት ሳይከናወን ቀርቷል።

ትናንትናም ኮንጎ ከአንጎላ፤ ደቡብ ሱዳን ከአልጄሪያ፤ ላይቤሪያ ከጊኒ እንዲሁም ናሚቢያ ቦትስዋና ጋር ተጋጥመዋል። የመልሱ ግጥሚያ በሚቀጥለው የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ይከናወናሉ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ፈረንሳይ ውስጥ በተከናወነው የሴቶች የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ ስፔንን 3 ለ1 ድል አድርጋ ዋንጫውን የወሰደችው ጃፓን ናት።   

ፕሬሚየር  ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል አኹንም ከግስጋሴው የሚያስቆመው አልተገኘም። ትናንት ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ተጋጣሚው ማንቸስተር ዩናይትድን ገጥሞ 2 ለ0 ድል በማድረግ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል። የመጀመሪያዋን ግብ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ለሊቨርፑል ከመረብ ያሳረፈው ተከላካዩ ቪርጂል ቫን ጂክ ነው። የትናንቱ የሊቨርፑል ሁለተኛ ግብ ሞሀመድ ሳላኅ ማንቸስተር ላይ ለመጀመሪያ ያስቆጠራት ግብ ኾና ተመዝግባለች። ሊቨርፑልም ከ30 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት በግስጋሴው እንዲገፋ አስችሎታል።

ሊቨርፑል ለዓመታት የተመኛትን ዋንጫ ለማንሳት ከእንግዲህ ማሸነፍ የሚጠበቅበት 10 ጨዋታዎችን ብቻ ነው። ሊቨርፑል እስካሁን ባደረጋቸው 22 የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች 21ንም ድል አድርጓል። ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ16 ነጥብ ልዩነት የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው።  

ደጋፊዎች በትናንቱ ግጥሚያ አንፊልድ ስታዲየም ውስጥ፦ «ሊጉን እናሸንፋለን» እያሉ ሲዘምሩ ተሰምተዋል። ኾኖም ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዩዑርገን ክሎፕ ለፈንጠዝያው ገና ነን በማለት ቀሪ ጨዋታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ባለፈው የፕሬሚየር ሊግ 38 ግጥሚያዎች ሊቨርፑል 97 ነጥብ አግኝቶ ዋንጫ ከማግኘት የተስተጓጎለው ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ብቻ በልጦት ነበር።  

በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል 64 ነጥብ አለው። ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ 48፤ ላይስተር ሲቲ 45 ነጥብ አላቸው። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ 39 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ 34 ነጥብ አለው። አርሰናል በዐሥረኛ ደረጃ ላይ 29 ነጥብ ይዞ ይገኛል። አስቶን ቪላ፤ ቦርሞስ እና ኖርዊች ሲቲ ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ይገኛሉ።

ትናንት በሊቨርፑል ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂው ሰርጂዮ ሮሜሮ ከመኪና አደጋ ለጥቂት መትረፉ ብዙዎችን አስደንግጧል። ግብ ጠባቂው ከጉዳት ቢተርፍም 200.000 ዩሮ የምታወጣው ላምቦርጊኒ ተሽከርካሪው ግን የማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ አቅራቢያ በሚገኘው ጎዳና ላይ ከፊት ለፊት ተጨራምታለች። በትናንቱ የማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ግጥሚያ የተሰለፈው ዴቪድ ደ ጊያ ነበር። ሰርጂዮ ሮሜሮ ብዙውን ጊዜ የተሰለፈው በአውሮጳ ሊግ፤ ኤፍ ኤ ካፕ እና የእንግሊዝ ሊግ ግጥሚያዎች ላይ ነው።

ቡንደስሊጋ

ከክረምት ረፍት በኋላ ዳግም በጀመረው የቡንደስሊጋ የመክፈቻ ጨዋታ ዓርብ እለት ሻልከ ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን በጨዋታ በልጦ 2 ለ 0 አሸንፏል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የዛሬ ወር በ17ኛ ዙር ግጥሚያ ወቅት ከሔርታ በርሊን ጋር ያለምንም ግብ በመለያየቱ ነጥብ ጥሎ ነበር። አሁንም በድጋሚ ነጥብ በመጣሉ ከኹለተኛ ደረጃው ወደ ሦስተኛ ተንሸራቷል።

የመክፈቻ ጨዋታው ዓርብ ማታ ሲጠናቀቅ ሁለተኛው የጀርመን ቴሌቪዥን (ZDF)  በተሰኘው የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እንደተለመደው የጨዋታ ትንታኔ ሲሰጥ በቲቪ የስፖርት ባለሞያ ኾኖ የሚቀርበው ኦሊቨር ካን የሻልከ አሰልጣኝ ባሉበት የቀረበለት ጥያቄ እና መልስ የመገናኛ አውታሮችን ትኩረት ስቦ ነበር።

ኦሊቨር ካን ከዘንድሮ የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ የባየር ሙይንሽን አመራር አባል መኾኑ ተገልጧል። በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ስፍራ የነበረው የ50 ዓመቱ ኦሊቨር ካን ለባየር ሙይንሽን ቡድን 14 ዓመታት በግብ ጠባቂነት አገልግሏል። አሁን ደግሞ በአመራር አባልነት። ይኸው የኦሊቨር ካን ቡድን ባየር ሙይንሽን የሻልከ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኑይብልን ሳይወስደው አልቀረም ተብሎ ይነገራል።

የ23 ዓመቱ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደርን ባየር ሙይንሽን በበጋው ወራት የ5 ዓመት ውል እንደሚያስፈርመው ገልጦ ነበር እናም ሞጭልፎ ሳይወሰደው እንዳልቀረ ይነገራል። በዓርቡ ግጥሚያም ለሻልከ የተሰለፈው በፊት ኹለተኛ ግብ ጠባቂ የነበረው ማርኩስ ሹበርት ነበር።

የቲቪ አስተናጋጁ ኦሊቨር ካንን ስለ ግብ ጠባቂው የጠየቀው እንዲህ ሲል ነበር። «በእውነቱ ግብ ጠባቂው ማርኩስ ሹበርትን እንዴት አገኘኸው? አኹን ከኹለተኛ ግብ ጠባቂነት ወደ አንደኛ ከፍ ብሏል አይደል?» ሲል ነበር፤ ጥያቄው  ምጸት አዘል ነው። ጥያቄውን ኦሊቨር ካን ከመመለሱ በፊት ግን የሻልከው አሰልጣኝ ዳቪድ ቫግነር ሳቅ ብለው በፍጥነት «አኹን ይኼ የምር ያስቃል፤ ጥያቄው ለሱ ሲቀርብለት አይደል?»አሉ። ኦሊቨር ካንም ቡድኑ የሠራውን ስለሚያውቅ ነው መሰል ለአፍታ ሳቅ ቢያፍነውም ወዲያው ግን ጥያቄውን ባግባቡ መልሷል።

አሌክሳንደር ኑይብል የቀይ ካርድ ቅጣት ስላለበት በሚቀጥለው ቅዳሜ ሻልከ ከባየር ሙይንሽ ጋር ሲጫወትም መሰለፍ አይችልም። ከዚያ በኋላ ግን የቀይ ካርድ ቅጣቱ ይነሳለታል። እናም ከሻልከ ጋር ይቀጥላል አለያስ ወደ ባየር ሙይንሽን እንደተባለው ይሄዳል ያኔ ይለይለታል። ሻልከ ቅዳሜ ዕለት ሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ፕሮይስን በወጣት ተጨዋቾቹ 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ይኸው ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኑይብል 90 ደቂቃ ተሰልፎ ነበር።

የሻልከ ደጋፊዎች ቅዳሜ ዕለት በወዳጅነት ጨዋታው ምንም ባይሉም ዓርብ ዕለት ግን ስታዲየም ውስጥ፦ «ኑይብል ይውጣ፤ ሹበርት ይግባ!» እያሉ በመዘመር የሻልከ ኹለተኛ ግብ ጠባቂን መፈለጋቸውን አሳይተዋል።

33 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባለፈው በሆፈንሀይም 2 ለ1 መሸነፉ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። በ18ኛው ዙር ግን ቅዳሜ ዕለት ቀንቶታል። አውስቡርግን ያሸነፈው 5 ለ3 ነው።

ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 አሸንፎ የክረምት ረፍት ያደረገው ባየርን ሙይንሽን ቡንደስሊጋው ከረፍት መልስ ሲጀምርም ቀንቶታል። ሔርታ ቤርሊንን ትናንት በሜዳው የግብ ጎተራ አድርጎ 4 ለ 0 አሸማቆታል። የአሠልጣኝ ዬርገን ክሊንስማን ቡድን ሔርታ ቤርሊን ለአንድ ሰአት ያኽል ግቡን ሳያስደፍር ቆይቶ ነበር። በ60ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቶማስ ሙይለር የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። በ73ኛ ደቂቃ ላይ የተሰጠችው ፍጹም ቅጣት ምት ግን እንደ ክሊንስማን ተገቢ አይደለችም።

የቤርሉኑ አሰልጣኝ ዬይርገን ክሊንስማን ምንም እንኳን በሰፋ ልዩነት ሽንፈት ቢገጥመው ሜዳ ላይ የነበሩትን 11ዱን ተጨዋቾች ግን አድንቋል። ክሊንስማን አድናቆትን የቸረው ቡድኑ ሊሸነፍ የቻለው ይኽች ፍጹም ቅጣት ምት በሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ከመረብ በማረፏ ነው ሲል ተከራክሯል። ሦስተኛዋን ቲያጎ፤ አራተኛዋን ፔሪሲች በ76 እና 84ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። በዚህም ባየር ሙይንሽን 36 ነጥብ ይዞ የቦሩስያ ሞይንሽን ግላድላድባኅን ኹለተኛ ደረጃ መረከብ ችሏል። ከመሪው ላይፕሲሽ የሚበለጠው በ4 ነጥብ ሲኾን፤ ሞይንሽንግላድባኅን በ1 ነጥብ በልጧል።

በሌሎች የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ባየር ሌቨርኩሰን ፓዴርቦርንን ትናንት 4 ለ1 ድል አድረገዋል።  ላይፕሲሽ ኡኒየን ቤርሊንን 3 ለ1፤ ፍራይቡርግ ማይንትስን 2 ለ1፤ ቬርደር ብሬመን ፎርቱና ዱይስልዶርፍን 1 ለ0 ያሸነፉት ቅዳሜ ዕለት ነው። ዶርትሙንድ አውስቡርግን 5 ለ3 ሲያሸንፍ፤ ኮሎኝ ቮልፍስቡርግን 3 ለ1 አሸንፏል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሆፈንሃይምን 2 ለ1 ድል አድርጓል።  ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በሻልከ 2 ለ 0 የተሸነፈው ከክረምት ረፍት በተመለሰው ቡንደስሊጋ መክፈቻ ዕለት ዐርብ ነው።

የሜዳ ቴኒስ

በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሜልቦርን ውስጥ የ15 ዓመቷ ኮኮ ጋውፍ ልምድ ያላት ያገሯ ልጅ አሜሪካዊቷ ቬኑስ ዊሊያምስን ዛሬ ማሸነፏ አስደምሟል። ኮኮ ብቃቷን ማሳየት የጀመረችው ባለፈው ዓመትም የ39 ዓመቷ ቬኑስ ዊሊያምስን በዌምብልደንን የመጀመሪያ ዙር በማሸነፍ ነበር።  ልክ እንደዓምናው ሁሉ ዛሬም 7 ለ6 እና  6 ለ3 ነው ያሸነፈቻት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic