ስፖርት፤ ጥር  07 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 15.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ጥር  07 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

​​​​​​​በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ የማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴ ትናንት ባልተጠበቀ መልኩ ተገቷል። እስካሁን 20 ጨዋታዎችን አሸንፎ በሁለት ግጥሚያዎች አቻ በመውጣት ሳይሸነፍ የዘለቀው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት አንፊልድ ላይ ለሊቨርፑል እጁን ሰጥቷል። ሰፋ ያለ ዘገባ ይኖረናል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:07

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ የማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴ ትናንት ባልተጠበቀ መልኩ ተገቷል። እስካሁን 20 ጨዋታዎችን አሸንፎ በሁለት ግጥሚያዎች አቻ በመውጣት ሳይሸነፍ የዘለቀው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት አንፊልድ ላይ ለሊቨርፑል እጁን ሰጥቷል። ሰፋ ያለ ዘገባ ይኖረናል። በጀርመን  ቡንደስ ሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቡድን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን ቢያሸንፍም ከመጨረሻ 18ኛነቱ ግን ፈቅ ሊል አልቻለም። በስፔን ላሊጋ መሪው ባርሴሎና የሪያል ሶሴዳድ ግብ ጠባቂንም ተከላካዮችንም ባደነዘዘው  የሊዮኔል ሜሲ ቅጣት ምት ግብ አሸናፊ ኾኖ ወጥቷል።  ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ የዓለማችን ድንቅ ተጨዋች ዛሬም ድል ቀንቶታል።

አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በስምንት ደቂቃ ልዩነት ቡድናቸው ላይ  እንደ ውርጅብኝ የተከታተለውን ሦስት ግብ የተመለከተበት ዐይናቸውን ማመን ሳይሳናቸው የቀረ አይመስልም። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን አንዳች ሽንፈት ሳይገጥመው በመሪነት የገሰገሰው ቡድናቸው ማንቸስተር ሲቲ ያልጠበቊትን ሽንፈት ነው ያሳያቸው። ለፔፕ ጓርዲዮላ ድንገተኛው ሽንፈት ለሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዮይርገን ክሎፕ በአንጻሩ አንገት ያስደፋ ሽንፈታቸውን ያደሱበት ድል ነበር። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን መክፈቻ ሰሞን ማንቸስተር ሲቲ ቡድናቸው ሊቨርፑልን 5-0  ያንኮታኮተበት መሪር ሽንፈት መቼም የሚረሳቸው አይደለምና።

ሊቨርፑል ትናንት በሜዳው አንፊልድ ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ ላይ ነበር የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው። አሌክስ ኦክሳሌድ ቻምበርላይን ከአራት ተጨዋቾች መሀል ኾኖ በአስደናቂ ፍጥነት መሬት ለመሬት አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ በማረፍ ሊቨርፑልን ቀዳሚ አደረገች። በእርግጥም ወደ ስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ያቀናው የሊቨርፑሉ የቀድሞ አጥቂ ፊሊፕ ኮቲኖህን ከእንግዲህ ማን ይፈልገዋል አስብሏል። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ግን ማንቸስተር ሲቲ  የሊቨርፑል ደስታ ላይ ለጊዜውም ቢኾን ቅዝቃዜ ቸለሰበት። ሌሮይ ሳኔ የሊቨርፑል ተከላካዮችን አታሎ በድንቅ ኹኔታ አቻ የምታደርገውን ግብ ያስቆጠረው በአርባናው ደቂቃ ላይ ነበር። የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ሎሬስ ካሪዮስ ባጠበበት በኩል ነበር ግቧ የተቆጠረችው።

በ59ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂውን መውጣት የተመለከተው ሮቤርቶ ፊርሚኖ ተረጋግቶየላካት ኳስ ከመረብ በማረፍ ሊቨርፑልን ዳግም መሪ አደረገች። ይህች ግብ የማንቸስተር ሲቲን እጣ-ፈንታ የደመደመች ነበረች። ይህን አስመልክተው የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ፦ «የፊርሚኖ ግብ እስኪቆጠር ድረስ ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ ነበር የጀመርነው። ከዚያ በኋላ ግን ጨዋታውን መቆጣጠር ተስኖን በአንፊልድ ድባብ ተውጠናል» ሲሉ ሽንፈታቸውን በጸጋ ተቀብለዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ኳስ በብዛት ሜዳው ላይ ይዞ ቢመላለስም የተከላካይ ጥፋትን ተጠቅሞ ሞሐመድ ሣላህ የነጠቀውን ኳስ ሳዲዮ ማኔ በግራ እግሩ ተረጋግቶ በመምታት በ61ኛው ደቂቃ ለሊቨርፑል ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሯል። የግብ ጠባቂው ኤደርሰንን ስህተት የተመለከተው ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ ከመሀል ሜዳ በርቀት የላካት ኳስ 4ኛ ግብ ኾና ተመዝግባለች።

ተስፋ ያልቆረጡት የፔፕ ጓርዲዮላ ልጆች 84ኛው ደቂቃ ላይ በበርናንዶ ሲልቫ ሁለተኛ ግብ አስቆጠሩ። ሁለተኛውን ግብ ለበርርናንዶ ሲልቫ ያመቻቸው ኤካይ ጉንዴዋን በአራት የሊቨርፑል ከተከላካዮች መሀል ሆኖ ኳስ በደረት አብርዶ ከመረብ አሳርፏል። ኾኖም ግቧ የተቆጠረችው በጭማሪ የባከነ ሰአት ስለነበር ሊቨርፑል 4 ለ3 ድል አድርጎ ወጥቷል። በዚህም ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ የመጀመሪያው የኾነውን ሽንፈት ተከናንቧል። ከሚያዝያ 15 ወዲህ ማንቸስተር ሲቲ በሀገር ውስጥ ጨዋታ ሲሸነፍ የትናንቱ የመጀመሪያው ነው። ሚያዝያ ላይ ማንቸስተር ሲቲ ድል የተነሳው በኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ በአርሰናል ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ መሸነፈቻቸውን በተመለከተ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ተጠይቀው ሲመልሱ «እንደ ሊቨርፑል ካለ ጥሩ ቡድን ጋር ተጋጥሞ ያለሽንፈት መዝለቁ እጅግ ከባድ ነው» ብለዋል። «እግር ኳስን መተንበይ ይከብዳል» ያሉት የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ «እስከ ፕሬሚየ ርሊጉ ፍጻሜ ድረስ መታገል አለብን» ሲሉ አክለዋል። 

በትናንቱ ውጤት መሠረት ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ እና ከቸልሲ እኩል 47 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት በሦስተኛ ደረጃ መስፈር ችሏል። 62 ነጥብ ከሰበሰበው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ15 ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ማታ ከስቶክ ሲቲ ጋር ይጋጠማል። ቸልሲ ቅዳሜ እለት ከላይስተር ሲቲ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየቱ በሊቨርፑል በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን አሁንም መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ዐርብ እለት ባየር ሌቨርኩሰንን 3 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 44 አድርሷል። ከትናንት በስትያ ሻልከን በተመሳሳይ 3 ለ1 የረታው ላይፕሲሽ በ31 ነጥብ ይከተላል። ተሸናፊው ሻልከ 30 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሦስተኛ ነው። የደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ የሚገኘው የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ቡድን ትናንት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 ቢረታም ከ18ኛ ደረጃው ግን ፈቅ ሊል አልቻለም።  ኮሎንን ለድል ያበቃችውን ግብ ያስቆጠረው ሲሞን ቴሮዴ ደስታውን እንዲህ ገልጧል።

«ምንም ቃል የለኝም። በመጨረሻዎቹ ቅጽበት ዝም ብዬ ወደ ግቡ ዘንግ አመራሁ። ኳሷ በድንቅ ሁኔታ ስለነበር ተሻምታ የደረሰችን እናም ትንሽ ወደ ኋላ ወጣ ብዬ ጥግ ለጥግ በመምታት ግብ አስቆጥሬያለሁ። ከዚያ በኋላ ግን የሆነውም ትዝ አይለኝ።  ሲመስለኝ ዐሥር አለያም 15 ሰዎች እላዬ ላይ ተረባርበው ነበር።  የዛሬው ድል ፍጹም ጠቃሚ ነበር።»

ኮሎኝ እስካሁን 9 ነጥብ ብቻ ነው መሰብብሰብ የቻለው። የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አማካይ ፓትሪክ ሔርማን የትናንቱን ሽንፈት መሪር ብሎታል።

«ማመን ይከብዳል። እንዲህ ያለ መሪር ግጥሚያ አከናውነን አናውቅም። ከአንድ አካባቢ በመጣ ቡድን በዛ ላይ በኮሎኝ ባለቀ ሰአት ግብ ሲቆጠርብህ እጅግ ያማርራል። በጨዋታዎች ሁለተኛ አጋማሽ የተሻልን ነበርን። ሁለት እና ሦስት ምርጥ አጋጣሚዎችም ነበሩን፤ እናም ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባን ነበር።»

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ትናንት ድንቅ ግብ ያስቆጠረው የሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ባርሴሎና በ51 ነጥብ በመሪነት እየገሰገሰ ነው። ባርሴሎና ትናንት 4 ለ2 ድል ያደረገው ሪያል ሶሴዳድን ነው።በእለቱ አርጀንቲናዊው የኳስ ንጉሥ ሊዮኔል ሜሲ በተደረደሩ ተከላካዮች አናት የላካት የቅጣት ምት ከመረብ ስታርፍ የሪያል ሶሴዳዱ ግብ ጠባቂን አደንዝዛ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ በ9ኝ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። ባርሴሎና ትናንት ድል ቢቀዳጅም ፈረንሳዊው አጥቂ ኦስማን ዴምቤሌን በደረሰበት የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ለሚቀጥሉት አንድ ወር እንደሚያጣ ዛሬ ገልጧል።

ቅዳሜ እለት በቪላሪያል 1 ለ 0 የተሸነፈው የክርስቲያኖ ሮናልዶ ሪያል ማድሪድ በቫለንሺያ በስምንት ነጥብ ተልቆ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።   ዴፖርቲቮ ላኮሩኛን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 ድል ያደረገው ቫለንሺያ 40 ነጥብ ሰብስቦ በሦተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የማንቸስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ድንቅ ተጨዋች ሪያን ጊግስ የዌልስ ቡድን አሠልጣኝ ኾኖ ውል ፈርሟል። ሪያን ጊግስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1991 እስከ 2007 ባሉት 16 ዓመታት ውስጥ 64 ዋንጫዎችን ያሸነፈ ሲኾን፤ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበልነትም አገልግሏል። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013-14  የጨዋታ ዘመን ሲባረሩ፤ ሪያን ጊግስ የቡድኑ ተንከባካቢ በመሆን አራት ጨዋታዎችን መርቷል።

ስቶክ ሲቲም አዲስ አሰልጣኝ ሰይሟል። የስቶክ ሲቲ አዲስ አሰልጣኝ ተብለው የተሰየሙት የ48 ዓመቱ የቀድሞ የአስቶን ቪላ እና የኖርዊች አሰልጣኝ የነበሩት ፖል ላምበርት ናቸው። አሰልጣኝ ማርክ ሑግስ መባረራቸውን ተከትሎ ነው የ48 ዓመቱ የስኮትላንድ ተወላጅ በስቶክ ሲቲ አዲስ አሰልጣኝነት ብቅ ያሉት።

የሜዳ ቴኒስ

በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የዓለማችን ቊጥር አንድ ተጨዋቹ ራፋኤል ናድል የዶሚኒክ ሪፐብሊኩ ተጋጣሚው ቪክቶር ኤስትሬላ ቡርጎስን ዛሬ ድል አድርጓል። ስፔናዊው ራፋኤል በሮድ ላቨር መጋጠሚያ ሥፍራ 94 ደቂቃ በፈጀው ፍልሚያ በሰፋ ልዩነት ያሸነፈው 6-1 6-1 6-1 በኾኑ ተከታታይ ውጤቶች ነው።  የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ራፋኤል ናዳል የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜን ለሁለተኛ ጊዜ ብሎም ዋናውን የዓለማችን የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ዋንጫ ለ17ኛ ጊዜ መጠቅለል እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic