ስፖርት፤ የካቲት 6 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 13.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ የካቲት 6 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዛሬም አሰልጣኝ የለውም። ፌዴሬሽኑ የዋና አሠልጣኙ ማንነትን በጥቂት ቀናት ዐሳውቃለሁ ብሏል። የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሠንጠረዡ ጠርዝ ላይ በሚገኝ ቡድን መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። ዶርትሙንድ ለነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ  ከ3 ሰአት በረራ በኋላ ዛሬ የፖርቹጋሏ ሊዝቦን ከተማ ገብቷል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27

የስፖርት ዘገባ

ከተመሰረተ ከ70 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የመከላከያ እግር ኳስ ቡድን  ለአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅደመ-ማጣሪያ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። መከላከያ አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ትናንት ከካሜሩን አቻው ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ በምኅጻሩ ዮሳ ጋር ገጥሞ 1 ለ0 አሸንፏል። ሆኖም ጨዋታውን ከስታዲየም እንደተከታተለው የሶከር ኢትዮጵያ ዳት ኔት ድረ ገጽ መራሄ ኤዲተር ዖምና ታደለ ከሆነ፦ መከላከያ በተለይ ከጨዋታው አጋማሽ በኋላ ደካማ ነበር። «የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። በተለይ መከላከያ» ሲልም አክሏል።

በመሀል ተከላካዩ አዲስ ተስፋዬ አማካኝነት በጨዋታው አጋማሽ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ስላስቆጠረው የመከላከያ ቡድን እና የካሜሩኑ አቻው ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ ጨዋታን በተመለከተ ከተደረገው ቃለ-መጠይቅ ወደሌላኛው እንሻገር። 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌፌሬሽን «ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ መሰረት በቴክኒክ እና ልማት ቋሚ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ» በበላይ ውሳኔ የተሰጠበት እንዳልሆነ አስታውቋል። የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ፦ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ነው መባሉን አስተባብለዋል። የአሰልጣኝ ምርጫውም ሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌፌሬሽን ትናንት በላከው ተጨማሪ የኢሜል መልእክት እንደገለጠው ከሆነ ደግሞ በዘንድሮው የውድድር ዓመት  ተግባራዊ በሆነው የእድሜ ተገቢነት ምርመራ ለማድረግ ክለቦች ካቀረቧቸው 2010 ተጨዋቾች መካካል ምርመራውን ማለፍ የቻሉት 762 ብቻ  እንደሆነ  አስታውቋል። ትናንት እንደተጀመረ የተገለጠው ድንገተኛ የእድሜ የማረጋጋጥ ሥራ ውጤትም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ፌዴሬሽኑ ተናግሯል።

 

አትሌቲክስ

ትናንት በተከናወነው የሆንግ ኮንግ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ብዙነህ መላኩ በላቸው በወንዶች እንዲሁም ጉሉሜ ቶሎሳ ጫላ በሴቶች ፉክክር  አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል። 

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው የመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚገኘው በዳርምሽታድት 2 ለ1 መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። የዳርምሽታድት ተጨዋቾች ቅዳሜው እለት የሞት ሽረት ፍልሚያ ነበር ያከናወኑት። ቦሩስያ ዶርትሙንድን ቢያሸንፉም ግን በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ 18ኛነት ከፍ ሊሉ አልቻሉም። 

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሻምፒዮንስ ሊጉ ግጥሚያ ነገ ከፖርቹጋሉ ቤንፊካ ጋር ይገናኛል። በላሊጋው በመሪው ሪያል ማድሪድ በአንድ ነጥብ ብቻ የሚበለጠው የስፔኑ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጀርሜይን ጋር የሚጋጠመው ነገ በተመሳሳይ ሰአት ማታ ነው። 

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና በርመስ ዛሬ ተስተካካይ አንድ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ የዛሬውን ተስተካካይ ጨዋታ ካሸነፈ ከቶትንሀም በሁለት ነጥብ በልጦ የሁለተኛ ደረጃውን ይረከባል። ከተሸነፈ በግብ  ክፍያ እንደተበለጠ ከሊቨርፑል በታች ይቆያል ማለት ነው።
ቅዳሜ እለት በሊቨርፑሉ ሳዶ ማኔ ሁለት ግቦች የተረታው ቶትንሐምን በ50 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሁልሲቲን  በአሌክሲስ ሳንቼዝ ሁለት ግቦች ድል ያደረገው አርሰናል ከቶትንሀም ጋር ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦስተኛ ነው። 

ዋትፎርድን 2 ለ0 ድል ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድ 48 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  የደረጃ ሰንጠረዡን በ60 ነጥብ የሚመራው ቸልሲ ትናንት ከበርንሌ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።

ቡጢ
በመለስተኛ መካከለኛ ክብደት የቡጢ ፍልሚያ የ38 ዓመቱ ጡረተኛ ቡጢኛ ፊሊፒናዊው ማኒ ፓኪው ለዳግም ፍልሚያ የቡጢ ጓንቱን ከተሰቀለበት አውርዷል። 
ደጋፊዎቹንም ቀጣይ ተጋጣሚውን እንዲመርጡለት በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ጠይቋል። ምናልባትም የማኒ ፓኪው ተጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ አራት ቡጢኞች ስም ዝርዝር ወጥቷል። የብሪታንያዎቹ አሚር ካን እና ኬል ብሩክ አለያም የአውስትራሊያው ጄፍ ሆርን ወይንም አሜሪካዊው ቴሬንስ ክራውፎርድ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል። የስድስት ጊዜያት የመለስተኛ የመካከለኛ ክብደት ቡጢ ተፋላሚው ማኒ ፓኪው ወደ ቡጢው ዓለም የተመለሰው ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ 
 

Audios and videos on the topic