ስፖርት፤ የካቲት 23  ቀን፣ 2012 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 02.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ የካቲት 23  ቀን፣ 2012 ዓ.ም

በለንደን ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያዊው ዕውቅ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ክብረ-ወሰን ሰብሮ አሸንፏል። በቶኪዮ ማራቶንም ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሃኑ ለገሰ ድል ተቀዳጅቷል። በቱር ደ ርዋንዳ አጠቃላይ ፉክክር የኤርትራው ብስክሌተኛ አሸናፊ ኾኗል። የሆፈንሃይሙ እና የባየር ሙይንሽን ጨዋታ ዲትማር ሆፕ ላይ ስድብ በመሰንዘሩ ጨዋታ ተቋርጦ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:20

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የጀርመኑ የእግር ኳስ ቡድን ባየር ሙይንሽን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋራ ያዘጋጁት የባየር 2020 የታዳጊዎች ውድድር የካቲት 19 እና 20 በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጓል፡፡ ከቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ አማራ አና ሱማሌ ክልሎች ከሚገኙ የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች እና ማዕከላት የተገኙ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ የእግርኳስ ተጨዋቾች ተሳትፈዋል፡፡

ውድድሩ በሚያዚያ ወር መጨረሻ በሙይንሽን በሚካሄደው የታዳጊዎች ውድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጨዋቾችን ለመመልመል እንዳገዘ የባየር ሙይንሽን እግር ኳስ ክለብ የታዳጊዎች አሰልጣኝ ክርስቶፈር ሎኽ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

«ይህ ውድድር የባየር ሙይንሽን ታዳጊዎች ውድድር ይሰኛል፡፡ በሃገራችን የታዳጊዎች ሻምፒዮና በየዓመቱ ሙይንሽን ውስጥ እናዘጋጃለን።  እናም በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ቡድኖችን፦ ለምሳሌ ለናይጄሪያ፣ ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለኦስትሪያ እንዲሁም እዚሁ ጀርመን ውስጥ ለሚገኙ ቡድኖች ጥሪ አድርገን እናሳትፋለን፡፡ ውድድሩ ሚያዚያ ወር ላይ ሙይንሽን ውስጥ በ12 ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ነው፡፡ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ወድድር የሚደረገው አልያንስ አሬና ውስጥ ነው፡፡»

ሙይንሽን ውስጥ በሚደረገው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ስትሳተፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚሆነው፡፡ በውድድሩ ላይ ተስጥዖ ያላቸው 20 ተጨዋቾች የተመረጡ ሲሆን፤ በምርጫው ላይ የባየር ሙይንሽን መልማዮች እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ክፍል አባላት ተሳትፈዋል፡፡ የከማል አህመድ አካዳሚ፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ ሰውነት ቢሻው አካዳሚ እና የሱማሌ ክልል ሚያዚያ ላይ ለሚደረግ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጨዋቾች ያስመረጡ ሆነው አልፈዋል፡፡ ውድድሩ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ተስጥዖቸውን እንዲያሳዩ በር የከፈተ ነው፡፡ በብዛት ጥሩ ግብ አስቆጣሪዎች እና የቴክኒክ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች በስፋት በታዩበት ውድድር አብዛኞቹ ቡድኖች ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ይዘው መቅረብ ችለዋል፡፡

ባየር ሙይንሽን ከአንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጋር በትብብር ለመሥራት እና የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ለማቋቋም ከተስማማ ወዲህ የአሰልጣኞች ስልጠና ሲያሰናዳ ቆይቷል፡፡ ዘገባውን የላከልን የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛው ዖምና ታደለ ነው። ቀጣዩንም መረጃ አክሎ ልኮልናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኩባንያ ሽርክና ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መቋቋሙን የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ቅዳሜ የካቲት 21 አዲስ አበባ ላይ በተደረገ የሊጉ የአንደኛው አጋማሽ ዙር ግመገማ ላይ ተናገረዋል፡፡ ኩባንያው ዓርብ የካቲት 20 አስፈላጊ የሆኑትን ሕጋዊ ሰነዶች አሟልቶ መመስረቱ ታውቋል፡፡ በግምገማው ላይ ከዚህ ቀደም አብይ ኮሚቴ በመባል ይታወቅ የነበረው ይህ አካል አሁን ወደ ኩባንያነት ስያሜውን መለወጡን አስታውቋል።

16 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በሽርክና የሚያስተዳድሩት ኩባንያ አውቃቀር ከጎረቤት ሃገሮች ሊጎች ልምዶችን ወስዶ ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል፡፡ ኩባንያው የሊጉን ውድድር በበላይነት ከመምራት በተጓዳኝ ሊጉ የስያሜ እና የቴሌቭዥን ስርጭት መብት አንዲኖረው እና ክለቦች ተጨማሪ ገቢ እንዲኖራቸው ይሠራል ተብሏል፡፡ በቅርቡም የሊጉ የስያሜ መብት አና የቴሌቭዥን ስርጭት መብት ፍላጎት ላላቸው አካላት በጨረታ እንደሚሸጥ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የራሱን ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ከፍቶ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን አንደሚሠራ ይጠበቃል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሊጉን ያስተዳደረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ውድድሩን ለክለቦች በዓመቱ መጀመሪያ አሳልፎ ከሰጠ ወዲህ በርካታ በጎ ጅምሮች የታዩ ሲሆን፤ የኩባንያው ሕጋዊ መሰረት ኖሮት መቋቋም ደግሞ ይበልጥ የተጠናከረ የሊግ አደረጃጀት በኢትዮጵያ እንዲኖር ተስፋ አንደሚፈነጥቅ ታምኖበታል፡፡

ቡንደስሊጋ እና ፕሬሚየር ሊግ

በጀርመን ቡንደስሊጋ እና በፕሬሚየር ሊጉ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የፕሬሚየር ሊጉ መሪው ሊቨርፑል ለመጀመሪያ ጊዜ መሸነፉ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል። ሊቨርፑል በዘንድሮ ውድድር በወራጅ ቃጣና ስር ሲዋዥቅ በነበረው ዋትፎርድ ቡድን ነው በአስደንጋጭ ኹኔታ 3 ለ0 የተሸነፈው። በጨዋታው የሊቨርፑል ተከላካይ ክፍል ከፍተኛ ድክመት ታይቶበታል። አጠቃላይ ቡድኑም የቀድሞ የማሸነፍ የጋለ ስሜቱ አልተስተዋለበትም። በአንጻሩ ዋትፎርዶች ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው፤ በጨዋታም ልቀው የሚገባቸውን ነጥብ አግኝተዋል። በውጤቱም ከወራጅ ቃጣናው መውጣት ችለዋል።

ሊቨርፑል ቀጣይ ጨዋታው የፊታችን ቅዳሜ ከቦርመስ ነው። ከዚህ ቀደም በነበሩ በርካታ ጨዋታዎች አንጻር ሊቨርፑል ዝቅተኛ ነጥብ ያለው ቡድን ሲገጥመው እጅግ ሲቸገር ይታያል። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ከጨዋታው በኋላ በመልበሻ ክፍል ተጨዋቾቻቸውን ኃይለ ቃል ሳይናገሩ ሜዳ ውስጥም አበረታትተው ነው የላኳቸው። ይልቁንም ዋነኛ ትኩረታቸው አኹን ነገ ከቸልሲ ጋር ለሚደረገው የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር መኾኑን ዐሳውቀዋል። በዚህ አጋጣሚ በሊቨርፑል ሽንፈት አርሰናል ቡድን እና ደጋፊዎች እጅግ መደሰታቸውን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ገልጠዋል። ምናልባትም በሊቨርፑል ሽንፈት ዋትፎርዶች ከተደሰቱበት በማይተናነስ ኹኔታ የሌሎች ቡድኖች ደጋፊዎች ጮቤ ረግጠዋል። ሊቨርፑል በ79 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው። ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ነጥቡን 57 አድርሷል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይስተር ሲቲ  50 ነጥብ አለው።

ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል ጋር ሊያደርግ የነበረው የፕሬሚየር ሊግ ተስተካካይ ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። አርሰናል በኤፍ ኤ ካፕ አምስተኛ ዙር ግጥሚያ ዛሬ ከፖርትስማውዝ ጋር ይገጥማል። ምናልባትም የሊቨርፑል ደጋፊዎች ምሽቱን ከፖርትስማውዝ ጎን ተሰልፈው አርሰናሎች ላይ ብዙ እንዲከሰት ይመኙ ይኾናል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ  በሳምንቱ መጨረሻ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ባየር ሙይንሽን ከሆፈንሃይም ጋር ባደረገው ግጥሚያ የሆፈንሃይሙ ደጋፊ ባለሐብት ዲትማር ሆፕ ላይ ደጋፊዎች ስድብ በመሰንዘራቸው ጨዋታው ተቋርጦ ነበር። ምንም እንኳን ባየር  ሙይንሽን 6 ለ0 እየመራ የነበረ ቢኾንም፤ ዲትማር ሆፕን በመደገፍም የባየር ሙይንሽን እና ሆፈንሀይም ተጨዋቾች ለ13 ደቂቃ ኳሷን መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ሲቀባበሉ ነበር። በስታዲየሙ «የትም ቦታ ይኹን ይኽን ጽሑፍ አንሱ» የሚል ማስታወቂያ የተነገረ ሲኾን ጨዋታው ተስተጓጉሎ ነበር።  ተጨዋቾቹ ዝም ብለው ኳሱን ሲቀባበሉም የባየርን ሙይንሽን ሊቀመንበር ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ እና የሆፈንሃይሙ ዲትማር ሆፕ አጨብጭበዋል። የባየር ሙይንሽን ደጋፊዎች ሆፕን የሚዘልፍ የብልግና ስድብ ስታዲየሙ ውስጥ በግዙፍ ጨርቅ ዘርግተው መያዛቸው ነበር ቁጣውን የቀሰቀሰው። መሰል የስነምግባር ጥሰት በስታዲየሞች ውስጥ መከሰቱ ብዙ ሊያነጋግር ይችላል ተብሏል።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሀኑ ለገሠ በተከታታይ ለኹለተኛ ጊዜ በጃፓን መዲና ቶኪዮ በተካሔደው የማራቶን የሩጫ ውድድር ትናንት አሸናፊ ኾኗል። ብርሀኑ በአብዛኛው ሰው አልባ በኾኑት የቶክዮ ጎዳናዎች አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ሮጦ ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከአስራ አምስት ሰከንዶች ነበር። በኮሮኖና ተሐዋሲ የተነሳ የቶኪዮ ነዋሪዎች ቀደም ሲል በየጎዳናዎች ጥግ እንዳይቆሙ ተመክረው ነበር። በውድድሩ ታዋቂ አትሌቶች ከመሳተፋቸው ባሻገር ኮሮናን ፍራቻ እንደተለመደው ከ30,000 በላይ አማተር ሯጮች ተሳታፊ አልነበሩም። ጃፓን ውስጥ 940 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መያዛቸውን ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል።  አትሌት ብርሃኑ ትናንት ለድል ቢበቃም ከሦስት ዓመት በፊት በዊልሰን ኪፕሳንግ የተያዘውን የ2:03.58 ክብረ-ወሰን ግን ለጥቂት ሳይሰብር ቀርቷል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን 5 ሺህ ሜትር፦ ፎቶ ከማኅደር

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን 5 ሺህ ሜትር፦ ፎቶ ከማኅደር

በለንደን የግማሽ ማራቶን ውድድርም ትናንት ቀነኒሳ በቀለ ከዚህ ቀደም በሞ ፋራህ የተያዘውን የቦታውን ክብረ ወሠን በመስበር አሸንፏል። ቀነኒሳ ውድድሩን ያጠናቀቀው በአንድ ሰዓት ከ22 ሰከንድ ነው። ብሪታንያዊው ክሪስቶፈር ቶምሰን  የኹለተኛ ደረጃን ሲይዝ ጄክ ስሚዝ በሦስተኛነት አጠናቋል። የትናንቱ ውድድር  ከኹለት ወር ግድም በኋላ በሚከናወነው የ42 ኪሎ ሜትር የለንደን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ማማሟቂያ ነበር።  በለንደን ማራቶን ሩጫ ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓም በዋናነት ቀነኒሳ በቀለ እና የኦሎምፒክ ባለድሉ ኬኒያዊው አትሌት ኢሊውድ ኪፕቾጌ ይሳተፉበታል የተባለው ፉክክር በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በተመሳሳይ ዘርፍ በሴቶች በተካሔደው ውድድር የብሪታንያዋ ሊሊ ፓትሪጅ 1:10:50 በመሮጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ ሆናለች።

የብስክሌት ሽቅድምድም

በቱር ደ ሩዋንዳ የብስክሌት ሽቅድምድም የኤርትራው ብስክሌተኛ  ናትናኤል ተስፋጺዮን አሸናፊ ኾኗል። 8ኛ ዙር የቱር ደ ርዋንዳ የ89 ኪሎ ሜትር የብስክሌት ግልቢያ የፍጻሜ ፉክክር ትናንት ርዋንዳ መዲና ኪጋሊ ውስጥ ከተከናወነው በኋላ ባለው አጠቃላይ ነጥብ የኤርትራው ብስክሌተኛ ተስፋጺዮን ናትናዔል አንደኛ ደረጃን በመያዝ አሸነፈ። የ20 ዓመቱ ተስፋጺዮን ቱር ደ ርዋንዳ ላይ አሸናፊ ሲኾን ሦስተኛው የኤርትራው አሽከርካሪ ኾኗል። ከዚህ ቀደም ዳንኤል ተክለሃይማኖት እና መርሃዊ ቅዱስ ከ10 እና 11 ዓመት በፊት በተመሳሳይ ውድድር ለድል በቅተው ነበር። ተስፋጺዮን ምርጥ የአፍሪቃ ብስክሌት ጋላቢ፤ ምርጥ ወጣት ብስክሌተኛ እንዲሁም  የዘንድሮ ውድድር ቢጫ መለያ ለባሽነት ማዕረግን ተቀዳጅቷል።  ኒፖ ዴልኮ ፕሮቬንስ ቡድን ውስጥ ታቅፎ የሚወዳደረው ኢትዮጵያዊው የብስክሌት አሽከርካሪ ኃይለሚካኤል ክንፈ 9ኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ በዐሥረኛነት ያጠናቀቀው ሌላኛው የኤርትራ ብስክሌተኛ ኄኖክ ሙሉብርሃን ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ መለሰ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች