1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2009

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል በሊቨርፑል አይቀጡ ቅጣት ገጥሞታል። በዓለማችን የቡጢ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ክፍያ በተፈጸመበት ውድድር ፍሎይድ ሜይዌዘር በ40 ዓመቱ 50ኛ ድሉን ተጎናጽፏል። በውድድሩ ሜይዌዘር እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚዝቅ ተዘግቧል። ሜይዌዘር በእሁዱ ፍልሚያ በደቂቃ 10 ሚሊዮን ግድም ተከፈለው ማለት ነው።

https://p.dw.com/p/2izTJ
USA Las Vegas Boxkampf Floyd Mayweather Jr. -  Conor McGregor
ምስል Reuters/USA Today Sports/M. J. Rebilas

ስፖርት፤ ነሐሴ 22 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል በሊቨርፑል አይቀጡ ቅጣት ገጥሞታል። የሳምንቱ መጨረሻ ውድድር ሊቨርፑል የቀድሞ ሰቀቀኑን የረሳበት አርሰናል ደግሞ ለዳግም ሽንፈት የተዳረገበት ነበር። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዴምቤሌን ወደ ባርሳ የላከው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ተተኪ ተጨዋች ፍለጋ ላይ ነው። ብሪታንያዊው የመኪና አሽከርካሪ በፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ጀርመናዊው ተቀናቃኙን በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በዓለም ዙሪያ የበርካታ ሚሊዮኖችን ቀልብ በሳበው የመካከለኛ ክብደት የቡጢ ፍልሚያ የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ዘንድሮም ጥንካሬውን አስመስክሯል። የ29 ዓመት ወጣት ተፎካካሪውን በዳኛ ውሳኔ መርታት ችሏል።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች አርሰናል ሽንፈት ገጥሞታል። ሊቨርፑል በአንፃሩ በየጊዜው ድንቅ ማሻሻል እየታየበት ነው። ትናንት አርሰናልን 4 ለ0 ያንኮታኮተው ሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ቡድናቸው ካለፈው የጨዋታ ዘመን የሽንፈት ኅመም ማገገሙን በኩራት ተናግረዋል።  «በጣም ጥሩ እንደነበርን ለማንም ግልፅ ነበር። እስካሁን  ካደረግናቸው ከእያንዳንዱ ጨዋታዎች በመማር የበለጠ አሻሽለናል። ከሆፈንሃይም ጋር ያረግነው ጨዋታ ደግሞ ይበልጥ የተሻለ ነበር» ሲሉ ስለ ቡድንቻው ጥንካሬ ገልጠዋል።

ሊቨርፑል ቀደም ሲል የጀርመኑ ሆፈንሃይምን በአጠቃላይ ድምር 6 ለ3 በመርታት በሻምፒዮንስ ሊጉ ቦታውን አመቻችቷል። ሊቨርፑል በትናንቱ ጨዋታ ግብ ጠባቂው ሚኙሌትን ሳይሆን ያሰለፈው ላሪስ ካሪየስን ነበር። በሁኔታው ሲሞን ሚኞሌት መናደዱ ተሰምቷል። ከአሰልጣኙ ጋር በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚሻ ተናግሯል።

በሻምፒዮንስ ሊግ የዙር ጨዋታ ሆፈንሃይምን በድምሩ 6 ለ3 የረታው የሊቨርፑል ቡድን
በሻምፒዮንስ ሊግ የዙር ጨዋታ ሆፈንሃይምን በድምሩ 6 ለ3 የረታው የሊቨርፑል ቡድንምስል Reuters/C. Recine/Action Images

ሊቨርፑል ከግብ ጠባቂው ሚኞሌት በተጨማሪ ወደ  ስፔኑ ባርሴሎና ቡድን ሊያቀና ጫፍ ደርሷል የተባለለትን ፊሊፕ ኮቲንሆን በድጋሚ ሳያሰልፍ ቀርቷል። ለሊቨርፑል ሮቤርቶ ፊርሚኖ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ሞሐመድ ሣላኅ እና ተቀይሮ የገባው ዳንኤል ስቱሪጅ ተከታታይ ግቦችን በማስቆጠር የአርሰናሉ አሰልጣኝ «ቬንገር ይወገዱልን» የሚለው መፈክር ይበልጥ እንዲስተጋባ መንገድ ከፍቷል። የአርሰናሉ አማካኝ ሜሱት ኦዚል በትናንቱ  ታላቅ ግጥሚያ ተዳክሞ ታይቷል። የኦዚል እና የአሌክሲስ ሳንቼዝ ውል በሚቀጥለው የበጋ ወር ላይ ያበቃል። እና ሜሱት ኦዚል አዲስ ውል ይገባዋል ወይ የሚል ጥያቄ ከወዲሁ አጭሯል።

በአጠቃላይ አርሰናል በትናንቱ ጨዋታ አማካኙ የተዳከመበት፤ ጭራሽ መኖሩ ያጠራጠረበት ነበር።  የመድፈኞቹ አማካዮች ግራኒ ሻቃ እና አሮን ራምሴ በቀያዮቹ ተቀናቃኞቻቸው እጅግ ተልቀው ታይተዋል። በሜዳው አንፊልድ አርሰናልን ድባቅ የመታው ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን ለመውሰድ ቆርጦ መነሳቱን ለዚያ ደግሞ አስፈላጊውን ነገር ከወዲሁ በማመቻቸት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ትናንት ከሊቨርፑል ባሻገር ቸልሲ ኤቨርተንን 2 ለ0 በመርታት ብርታቱን አሳይቷል። ቶትንሀም ሆትስፐር ከበርንሌይ እንዲሁም ዌስት ብሮሚች አልቢኖ ከስቶክ ሲቲ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ከትናንት በስትያ ማንቸስተር ዩናይትድ ላይሰተር ሲቲን 2 ለ ባዶ እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ቦርመስን 2 ለ1 አሸንፈዋል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ደግሞ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ኦስማኔ ዴምቤሌን  በ147 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ለባርሴሎና መሸጡ ተሰምቷል።  የባርሴሎና ኃላፊ ሮቤርት ፈርናንዴዝ የሊቨርፑሉ ፊሊፕ ኮቲንሆንም ለማስመጣት ከጫፍ መድረሳቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።  ወደ ስፔኑ ካምፕ ኑ ስታዲየም ዘንድሮ ሁለት ተጨማሪ ተጨዋቾች እንደሚመጡ የቡድኑ ኃላፊ አክለው ተናግረዋል።

Ousmane Dembélé
ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ ስፔኑ ባርሴሎና ያቀናው ዖስማኔ ዴምቤሌምስል picture-alliance/SvenSimon

ኦስማኔ ዴምቤሌ ከባርሴሎና ቡድን ጋር ዛሬ ውል መፈረሙ ተዘግቧል። በባርሴሎና ሜዳ ኳስ በግራ እና በቀኝ እግሩ ለማንቀርቀብ ሞክሮ ሲስት የሚታይበት አጠር ያለ የቪዲዮ ምስል በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ አውታር በፋት ተሰራጭቷል። በርካቶች 135.5 ሚሊዮን ፓውንድ የተከፈለበት ተጨዋች ላይ «እውነትም ከኔይማር ይሻላል» ሲሉ ተሳልቀዋል። ዴምቤሌ በበኩሉ «ከሊዮኔል ሜሲ ጋር ተሰልፎ መጫወት ለኔ ክብር ነው » ሲል መናገሩን የባርሴሎና ቡድን በትዊተር ገልጧል። «እሱ በእግር ኳስ ታሪክ ምርጡ ተጨዋች ነው» ሲል ስለ ሜሲ የተናገረው ዴምቤሌ «እኔ እዚህ የተገኘሁት ለመማር ነው» ሲል አክሏል። ኦስማኔ ዴምቤሌን ለባርሴሎና ያስረከበው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከትናንት በስትያ ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ0 ድል አድርጓል።

አትሌቲክስ

ባሳለፍነው ሳምንት ስዊዘርላንድ ዙሪክ ውስጥ የተከናወነውን የዳያመንድ ሊግ ውድድር ለመዘገብ ወደ ስፍራው የተጓዘችው የፓሪሷ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ የውድድሩ አሸናፊዎችን በስፍራው አነጋግራ ነበር። በሞ ፋራህ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የዙሪኩ የዳያመንድ ሊግ የፍጻሜ ውድድር የለንደኑ የ5 ሺህ ሜትር የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ባለድል ሙክታር እድሪስና ዮሚፍ ቀጀልቻ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በእነ ኃይሌ እና ቀነኒሳ ዘመን የነበረው የቡድን ሥራ ዛሬም ድረስ ሊመለስ እንዳልቻለ ተናግሯል። አትሌት ሙክታር እድሪስ በበኩሉ ዮሚፍ ቀጀልቻ ላይ መሰናከል እንዳልፈጠረ ይlልቁኑስ በውድድሩ ተገፍትሮ በመውደቅ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግሯል። «እሱም የሚሮጠው የራሱን ሩጫ ነው፥ እኔም የምሮጠው የእራሴን ሩጫ ነው» ብሏል። ሞ ፋራህ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ ለኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ልዩ ክብር እንዳለው ገልጧል። 

IAAF London Leichtathletik WM- 5,000 M Lauf
ሙክታር እድሪስ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና ሞ ፋራህ ምስል DW/H. Tiruneh

የመኪና ሽቅድምድም

በቤልጂየሙ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ድል ሲቀናው ጀርመናዊው ተፎካካሪው ሰባስቲያን ፌትል በ2 ሰከንድ ልዩነት ለጥቂት ተቀድሞ ሁለተኛ ኾኗል። በትናንቱ ውጤት መሰረት የሁለቱ ዋነኛ ተፎካካሪ አሽከርካሪዎች አጠቃላይ የነጥብ ልዩነት ወደ 7 መጥበብ ችሏል። በአጠቃላይ ድምር ውጤት የፌራሪው አሽከርካሪ ሰባስቲያን ፌትል  እስካሁን 220  ነጥብ በመሰብሰብ ውድድሩን በመምራት ላይ ይገኛል። የመርሴዲሱ አሽከርካሪ  ሌዊስ ሐሚልተን በበኩሉ ነጥቡን 213  ማድረስ ችሏል።  የፊታችን እሁድ ሞንትሳ ከተማ ውስጥ በሚከናወነው የጣሊያን ግራንድ ፕሪ ፉክክር ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ዳግም ይፋጠጣሉ።

ቡጢ

በዓለማችን የቡጢ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ክፍያ በተፈጸመበት ውድድር የመካከለኛ ሚዛን ቡጢኛው ፍሎይድ ሜይዌዘር በ40 ዓመቱ 50ኛ ድሉን ትናንት ተጎናጽፏል። የቡጢ ስፖርት አደራጅ እና ጡረተኛ ቡጢኛው ሜይዌዘር በ10ኛው ዙር ላይ ድል የነሳው በቁመት ከእሱ ዘለግ ያለው፣ የ29 ዓመቱ የአይሪሹ ተፎካካሪው ኮኖር ማክ ግሬጎርን ነው። 10ኛው ዙር ላይ የተዳከመውና ተደጋጋሚ የሜይዌዘር ቡጢዎች ያረፉበት ኮኖር ከባድ አደጋ ሳይደርስበት በፊት ዳኛው  ጨዋታው ተቋርጦ በቴክኒካዊ ዝረራ ሜይዌዘር እንዲያሸንፍ አድርገዋል። አንዳንድ ሰዎች ውድድሩ ያለጊዜው ነው የተቋረጠው ሲሉ ተችተዋል። ውድድሩ በተጠናቀቀበት ወቅት የሦስቱ ዳኞች አጠቃላይ ውጤት ድምርም የሚያመለክተው ሜይዌዘር ሙሉ ለሙሉ ይመራ እንደነበረ ነው። በውድድሩ ሜይዌዘር እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚዝቅ ተዘግቧል። ሜይዌዘር በትናንቱ ፍልሚያ በደቂቃ 10 ሚሊዮን ግድም ተከፈለው ማለት ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ