ስፖርት፤ ሰኔ  5  ቀን፣ 2009 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 12.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ሰኔ  5  ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ በጠንካራው የጋና ቡድን ኃያል ምት ገጥሞታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለለንደን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መምረጫ በኔዘርላንድ ሄንግሎ የሙከራ ውድድር አካሄዷል። ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አውሮጳውያን ባደረጉት ጨዋታዎች  ጀርመን  ደካማዋ ሳንማሪኖን እንደማይሆን አድርጋ  ሸኝታለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:05

የስፖርት ዘገባ

ዛሬም «ሠረገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ» አይነት ነው የኾነው። በአጭር ጊዜ ጥሪ የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ከጠንካራው የጋና ቡድን  ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ውድድር ኃያል ምት ገጥሞታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ16ኛው የለንደን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መምረጫ በኔዘርላንድ ሄንግሎ የሙከራ ውድድር አካሄዷል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም  ሌዊስ ሐሚልተን አሸናፊ ኾኗል። ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አውሮጳውያን ባደረጉት ጨዋታዎች  ጀርመን  ደካማዋ ሳንማሪኖን እንደማይሆን አድርጋ ሸኝታታለች።

ሐሙስ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓም ድንገት በአጭር ጊዜያት የተሰባሰቡት ዋሊያዎቹ ወደ ምዕራብ አፍሪቃዋ ጋና አቀኑ። ጥቋቁር ከዋክብቱን ሊገጥሙ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ከተከናወነው የዓለም ዋንጫ ወቅት ወዲህ ቁጥሩ በርከት ያለ ሰው በስታዲየም ሲታደም የትናንቱ የመጀመሪያው ነበር። ጥቋቁር ከዋክብቱ በኩማሲ ስታዲየም እዚህም እዚያም ሊወረወሩ አሰፍስፈዋል። 

ጨዋታው ተጀመረ።  10 ደቂቃ አላለፈም። ለቻይናው ሻንጋይ ቡድን ተሰላፊው አምበሉ አሳሞዋ ጊያን የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ አሳረፈ።  ቱርክ ውስጥ የሚጫወተው ጆን ቦዬ ደካማ ተከላካይ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን ላይ በአራት ደቂቃ ልዩነት ሁለተኛዋን ግብ ለማስቆጠር እምብዛም አልተቸገረም። ለጀርመን ሽቱትጋርት  በአማካይ የሚሰለፈው ኤቤኔዜር ኦፎሪ ያስቆጠራትን  አስደናቂ ሦስተኛ ግብ  ግን የሚስተካከል አልነበረም። 

መደበኛው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ኤቤኔዘር ኦፎሪ የኢትዮጵያ ተከላካዮችን አታሎ ከርቀት በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ነበር መረቡን ያርገበገበው። የመጀመሪያው አጋማሽ በጋና 3 ለ0 መሪነት ተጠናቀቀ። የጨዋታው ሁለተኛ  አጋማሽ ሲጀምር ጋና አራተኛውን ግብ በሦስት ደቂቃ ውስጥ ነበር ያስቆጠረችው፤ ስዊዘርላንድ ውስጥ ለዙሪክ ተሰልፎ በሚጫወተው አጥቂ  ራፋኤል ድዋሜና አማካኝነት።  ራፋኤል አምስተኛዋን እና የማሳረጊያዋንግ ግብ ከመረብ ያሳረፈው በ59ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ስድስተኛ ግብ የኢትዮጵያ ቡድን ላይ ለጥቂት ሊቆጠረም ነበር። የእግር ኳስ ጋዜጠኛው መንሱር አብዱልቀኒ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ  ቡድን እጅግ ደካማ እንደነበር ይናገራል። «ድክመቱ እጅግ የጎላ ስለሆነ ጥንካሬውን ማግኘት አስቸጋሪ ነው» ያለው መንሱር የኢትዮጵያ እና የጋና ብሔራዊ ቡድኖች ልዩነት ሰፊ እንደነበር ገልጧል። «የተጨዋቾች ስብስብ አለ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል፤ የተዋሀደ ቡድን ደግሞ በጋና በኩል አለ»  ሲል የልዩነቱን ስፋት አሳይቷል።

የጋና ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን 5 ለ0 ባሸነፈበት የትናንቱ ጨዋታ አምበሉ አሳሞዋ ጊያን ተቀይሮ ሲወጣ የአምበልነት መለያውን ለቡድኑ ሁለተኛ አምበል አንድሪው አዩ አለመስጠቱ በጋናውያን የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ሰፊ መነጋገሪያ ኾኗል። በርካቶች በሁለቱ ተጨዋቾች ቅራኔ አለ ሲሉ ተደምጠዋል። የጥቋቁር ከዋክብቱ አሠልጣኝ ክዌሲ አፒያህ ግን ምንም ቅራኔ የለም አሳሞሃ የአምበልነት መለያው ላይ የራሱ ምስል ስላለበት ቢቀየር መለያውን እንደማይሰጥ እናውቅ ነበር ብለዋል። የጋና እግር ኳስ ማኅበር ግን በፊፋ ደንብ መሠረት የአምበልነት መለያ ላይ ከቡድኑ መለያ ውጪ ሌላ ምስል ማድረግ ስለሚያስቀጣ አሳሞሃ ጊያን ከቅጣት አያመልጥም ብለዋል። ሚሊየነሩ አሳሞሃ ጊያን የሚቀጣው ግን ከ1000 እስከ 2,500 ዶላር ብቻ እንደሆነ ጋና ሶከር ኔት የስፖርት ድረገጽ ዘግቧል። 

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ጋና በ3 ነጥብ እና 5 ንጹህ የግብ ክፍያ ስትመራ፤ ኬንያን 2 ለ1 ያሸነፈችው ሴራሊዮን በሁለተኛ ደረጃ ላይ  ትገኛለች። ኬንያ በአንድ የግብ እዳ እና ዜሮ ነጥብ ኢትዮጵያን አስከትላ ከምድቡ ሦስተኛ ናት። 

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ሩስያ ውስጥ ለሚከናወነው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በአውሮጳውያን ቡድኖች መካከል ቅዳሜ እለት በተደረጉ ፉክክሮች ጀርመን በግብ ተንበሽብሻለች። ስድስቱን የማጣሪያ ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድብ ሀን የምትመራው ጀርመን ቅዳሜ እለት ሳን ማሪኖን በተዝናና ኹናቴ ያሸነፈችው 7 ለ0 ነው። የጨዋታው መለኪያ መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሆነ ጀርመን 83 ከመቶ የኳስ ቁጥጥ በማድረግ እጅግ ልቃ ታይታለች።  የጀርመን  ቡድን 9 ዒላማቸውን ያልሳቱ ምቶችን ጨምሮ 27 ጊዜ ወደ ግብ ሙከራ ሲያደርግ ሳንማሪኖ በአንጻሩ አንዳችም ሙከራ አላደረገችም ማለት ይቀላል።

ለጀርመን ሆፈንሐይም ቡድን ተሰልፎ የሚጫወተው ግዙፉ ሳንድሮ ቫግነር ለጀርመን ቡድን ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል።  ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ሲሰለፍ የቅዳሜው  ገና ሁለተኛው የነበረው የ23 ዓመቱ አሚን ዩኔስ ከሰባቱ ግቦች ተቋዳሽ በመሆን ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ግቡን  ማስቆጠር ችሏል። «ፋታ እንዲወስዱ የተደረጉ ድንቅ ድንቅ ተጨዋቾች አሉን። ያ ግን እኛም ችሎታችንን እንድናሳይ እድል ፈጥሮልናል» ሲል የአያክስ አምስተርዳም ተሰላፊው አሚን ዩኔስ ደስታውን ገልጧል። በእርግጥም የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዬዮኣሒም ሎይቭ የቡድናቸው ወጣት ተጨዋቾች ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ እና የተለያዩ የአጨዋወት ስልቶችን በመሞከር ይወደሳሉ። የቀሩትን ሦስት ግቦች ያስቆጠሩት የአርሰናሉ ተከላካይ ሽኮርዳን ሙስታፊ፤ የፓሪስ ሴን ጀርሜይኑ ዡሊያን ድራክስለር እና የባየር ሌቨርኩሰኑ ዡሊያን ብራንድት  ናቸው።

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ የሙከራ ውድድሮችን ሄንግሎ ኔዘርላንድ ውስጥ ቅዳሜ እና እሁድ አድርጓል። ይኽን ውድድር በተመለከተም ፌዴሬሽኑ በዋና ጽ/ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነገ ከቀኑ 8 ሰአት ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። 

ሞንትሪያል ካናዳ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የፎርሙላ አንድ  የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ ቡድን ቀንቶታል። ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል አራተኛ በወጣበት ውድድር ብሪታንያዊው ዋነኛ ተፎካካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ሽቅድምድሙን በአንደኛነት አጠናቋል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫልተሪ ቦታስ በሁለተኛነት ዋንጫውን አንስቷል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ዳንኤል ሪካርዶ ሦስተኛ በመውጣት የሻምፓን መራጨት ስርአቱ ተካፋይ ኾኗል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic