ስፖርት፤ ሰኔ 3 ቀን፣ 2011 ዓ.ም  | ስፖርት | DW | 10.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ሰኔ 3 ቀን፣ 2011 ዓ.ም 

ፍሎሬንስ ጣልያን ውስጥ ኢትዮጵያዊው የጁጂትሱ ተፋላሚ አሸናፊ ኾኗል። በኔሽንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ ፖርቹጋል ኔዘርላንድስን ድል አድርጋ ዋንጫውን አንስታለች። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተቻለ መጠን መፍትኄ በመሻት የፕሬሚየር ሊጉን በፍጥነት ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:43

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኤርትራ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የአስመራ ማራቶን ኤርትራዊው አትሌት መሐሪ ፀጋይ አንደኛ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት  ታደሰ አሰፋ የኹለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ፍሎሬንስ ጣልያን ውስጥ ኢትዮጵያዊው የጁጂትሱ ተፋላሚ አሸናፊ ኾኗል። በኔሽንስ ሊግ የፍጻሜ ፍልሚያ ፖርቹጋል ኔዘርላንድስን ድል አድርጋ ዋንጫውን አንስታለች።  የዓለም እግር ኳስ የሴቶች ፉክክር ቀጥሎ ዛሬ እና ነገም ውድድሮች ይኖራሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተቻለ መጠን መፍትኄ በመሻት የፕሬሚየር ሊጉን በፍጥነት ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ገልጧል።

የፖርቹጋል ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት የኔዘርላንድ አቻውን አንድ ለዜሮ በኾነ ውጤት ድል በማድረግ የመጀመሪያውን «ኔሽንስ ሊግ» የተሰኘውን ውድድር ዋንጫ በማንሳቱ ፖርቹጋል በፈንጠዝያ አምሽታ ነግቶላታል።  የ34 ዓመቱ አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል ስዊዘርላንድን 3 ለ1 በረታችበት የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ሔትሪክ በማስቆጠር ቡድኑን ለፍጻሜ ቢያደርስም፤ የዋንጫዋን ግብ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ያስገኘው ግን ጎንሳሎ ጉዌዶሽ ነበር። ሔትሪክ ባስቆጠረበት ሦስት ግቦቹ  የኔሽንስ ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢnበመonu ግን ሮናልዶ ዋንጫውን አንስቷል። 

ኔሽንስ ሊግ፦ ቀደም ሲል በፊፋ በኩል ይደረግ የነበረው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታን ለመተካት ታስቦ የተዘጋጀ ውድድር ነው። ውድድሩ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (FIFA) የዓለም ዋንጫ እንደተጠናቀቀ በአራት ምድብ ድልድል ነበር የተጀመረው። የአውሮጳ 55 ሃገራት በአራት ምድብ ተከፍለው ወራጅ እና አዳጊ ቡድኖችን በማካተት እንዲሁም ተመሳሳይ ነጥብ ያላቸውን በቀጣይ ዓመት ውድድር በመለየት የሚከናወነው ይኽ ግጥሚያ ውስብስብ በመኾኑ ለመልመድ ጊዜ እንደሚወስድ  በርካቶች ገልጠዋል።

የየምድቦቹ አሸናፊዎች ለፍጻሜ ደርሰው ባደረጉት ፉክክር ፖርቹጋል ትናንት ድል ቀንቷታል። የዓለም ዋንጫ የአራት ጊዜያት አሸናፊው የጀርመን ቡድን በኔሽንስ ሊግ ውድድር በመጀመሪያው ዙር ከውድድር ውጪ መኾኑ በወቅቱ አነጋግሮ ነበር። ከአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ከአውሮጳ ሊግ በተጨማሪ የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ በየዓመቱ የሚከናወን ይኾናል። 

ከዚሁ ከእግር ኳስ ስፖርት ሳንወጣ ባለፈው ረቡዕ የታገደው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ መቀጠል እንዳለበት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚዎች ትናንት ተወያይቷል። መቼ እና እንዴት ይቀጥላል ለሚለው አቶ ባሕሩ ጥላሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋር ደውለን ነበር፦ «በቀጣይ በሚኖሩ ቀናት ጨዋታው በምን መንገድ ይቀጥላል የሚለውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የሚያሳውቅ ይኾናል» ብለዋል።የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት ከሰአት ባካሄደው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተወሰነ አለመግባባት እንደነበር የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ምንጮቹ እንደገለጡለት ነግሮናል። የፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ ዛሬ ከአሰአት ባደረገው ስብሰባ የፕሬሚየር ሊጉን ጨዋታ ለማስጀመር መግባባት ላይ እንደተደረሰም አክሎ ገልጧል። 

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ዓለም ዋንጫ በእግረ-ኅሊና አብረን እናቅና። ባለፈው ዐርብ ፈረንሳይ ውስጥ የተጀመረው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ውድድር ቀጥሎ ዛሬ ማምሻውን አርጀንቲና ከጃፓን  እንዲሁም ካሜሩን ከካናዳ ጋር ይጋጠማሉ። በሴቶች የዓለም ዋንጫ 24 ቡድኖች በ6 ምድቦች ተደልድለው ይገኝሉ። ካሜሩን፦ ኔዘርላን፣ ካናዳ እና ኒውዚላንድ በሚገኙበት ምድብ አምስት ላይ ነው የምትገኘው። ከአፍሪቃ፦ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ካሜሩን ተሳታፊ ናቸው። ናይጀሪያ ዐርብ እለት በኖርዌይ 3 ለ0 ስትሸነፍ፤ ደቡብ አፍሪቃ ቅዳሜ እለት በስፔን የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። 

በጁጂትሱ የትግል ስፖርት አትሌት ያሬድ ንጉሤ ትናንት ፍሎረንስ ጣሊያን ውስጥ ድል ተቀዳጅቷል። ያሬድ ከዚህ ቀደም ሞሮኮ ማራኬሽ ከተማ ቤንጒረር ውስጥ በተከናወነው ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ አትሌት ነው። ከፍሎረንስ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ከመብረሩ ቀደም ብለን በስልክ አነጋግረነዋል። በቅድሚያ እንኳን ደስ ያለህ በማለት ስለውድድሩ እንዲነግረን ጠይቀነዋል።

የጁጂትሱ ተፋላሚው ያሬድ ንጉሤ ከዚህ ቀደም ቪዬና ኦስትሪያ፣ ፖላንድ እንዲሁም ዱስልዶርፍ ጀርመንን በመሳሰሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ ያካበተ አትሌት ነው። 

ኤርትራ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የአስመራ ማራቶን ኤርትራዊው መሐሪ ፀጋይ በአንደኛነት አጠናቋል። በውድድሩ ኤርትራውያን፤ ኢትዮጵያዉያን፤ ኬንያዉያን፤ ኡጋንዳውያን፡ ደቡብ ሱዳናውያን እና ታንዛኒያውያን 60 አትሌቶች መሳተፋቸው ተገልጧል። አትሌት መሐሪ ጸጋይ 2 ሰአት ከ14 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ሮጦ በመግባት ነበር አሸናፊ የኾነው። ከሦስት ደቂቃ ግድም በኋላ መሐሪን ተከትሎ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ አሰፋ ኹለተኛ ወጥቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic