ስፖርት፤ ሰኔ 19 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 26.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ሰኔ 19 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

በፕሬሚየር ሊጉ ማብቂያ ደደቢት በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኝ ከነበረው ወላይታ ድቻ ጋር ያደረገው ግጥሚያ ብዙዎችን አነጋግሯል። በእግር ኳሱ ዙሪያ ትኩረት የሚያሻቸው አሻጥሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም የጠቆሙ አሉ። ጀርመን ካሜሩንን 3 ለ1 ረትታለች፤ ሐሙስ ዕለት በግማሽ ፍጻሜው ሜክሲኮን ትገጥማለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:38

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ቀደም ሲል ባለድል መሆኑን ባረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የዋንጫ ስነ ስርአት ቅዳሜ ዕለት ተጠናቋል። በቅዳሜው ጨዋታ ፕሬሚየር ሊጉን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ደደቢት በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኝ ከነበረው ወላይታ ድቻ ጋር ያደረገው ግጥሚያ ብዙዎችን አነጋግሯል። በእግር ኳሱ ዙሪያ ትኩረት የሚያሻቸው አሻጥሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም የጠቆሙ አሉ። የእግር ኳስ ስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል። ብሪታንያዊው የዓለማችን ቁጥር አንድ የመኪና አሽከርካሪ ከጀርመናዊ ተፎካካሪው ጋር እሰጥ አገባ ገጥሟል። እርስ በእርስም በመኪናዎቻቸው ተጎሻሽመዋል። የሩስያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር በመጠቀም ክስ ሊመሰረትባቸው ነው። እዛው ሩስያ ውስጥ የኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ ዋንጫ እየተኪያሄደ ነው። 

እግር ኳስ

ቅዳሜ ዕለት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች የዋንጫው ባለቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆኑ ከሳምንታት በፊት የታወቀ ቢሆንም  ወራጅ ቃጣናው ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ላለመውረድ ያደረጉት ትንቅንቅ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። ያም ብቻ አይደለም በተለይ ወላይታ ዲቻ እና ደደቢት ያደረጉት ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስን በቅርበት በሚከታተሉ ሰዎች በልዩ አዐይን ነው የታየው። ኦምና ታደለ የኢትዮሶከር ዳት ኔት  የስፖርት ድረ-ገጽ መራኄ አርታኢ ነው። እሱም በጨዋታው አጠራጣሪ ነገሮች መከሰታቸውን ታዝቧል። ኦምና «ፕሬሚየር ሊጉ እንደዚህ አይነት መላቀቅ [የመጠቃቀም] ኹኔታዎች ሲነገሩበት ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፉትም ዓመታት ይህን ነገር ሰምተናል» ብሏል።  

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ይከናወናሉ የሚባሉትን አጓጉል «መጠቃቀሞች» እግር ኳሱን የሚያቀጭጩ በመሆናቸው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሊያደርግበት ይገባል እንላለን። 

ሩስያ ውስጥ የሚከናወነው የኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ ጨዋታ ቀጥሎ ትናንት ጀርመን ካሜሩንን 3 ለ1 በማሸነፏ  በግማሽ ፍጻሜው የፊታችን ሐሙስ ሜክሲኮን ትገጥማለች። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ረቡዕ ደግሞ ፖርቹጋል እና ቺሌ ተቀጣጥረዋል።  የኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ የሚከናወንባት ሩስያ የመድኃኒቶች እና ንጥረ ነገሮች ሕገወጥ ዝውውር በሚወገዝበት ዓመታዊ ቀን ዋዜማ እግር ኳስ ተጨዋቾቿን ጨምሮ 30 አትሌቶች ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጧል። 

የሩስያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫ ወቅት የኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገር ተጠቅመው እንደሆን ለማወቅ  ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) ምርመራ በማከናወን ላይ ይገኛል። 

የመኪና ሽቅድምድም

በአዘርባጃኑ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን የጀርመናዊው ተፎካካሪው ሰባስቲያን ፌትል አነዳድን «አስቀያሚ» ሲል ገልጦታል። በውድድሩ ወቅት እየመራ የነበረው ሌዊስ ሐሚልተን «ሆን ብሎ እንዳልቀድመው ፍጥነቱን አቀዝቅዟል» በሚል ንዴት ነበር ሰባስቲያን ፌትል ሌዊስ ሐሚልተንን ከኋላው እንዲሁም ወደፊት ሄዶ ከጎን የገጨው።  በሬዲዮ ንግግሩም ወቅት ንዴት የተቀላቀለበት ቃላትን ሲጠቀም ተሰምቷል። ይህ ድርጊቱ በሌሎች ተወዳዳሪዎች ዘንድ ሲተች፤ በፎርሙላ አንድ አወዳዳሪዎች ደግሞ ለ10 ሰከንድ ቅጣት ዳርጎታል። የሌዊስ ሐሚልተን አነዳድ በአወዳዳሪዎቹ ሲተነተን ምንም ችግር የሌለበት እንደ ነበር ተገልጧል።

 

የቅዳሜ ሳምንት በሚጀምረው የአውትራሊያው ውድድር ላይም ሰባስቲያን ፌትል ጥፋት ፈጽሞ ሰከንዶች የሚቀነሱበት ከሆነ ከአውስትራሊያው ውድድር ቀጥሎ በሚኖረው የብሪታንያ የመኪና ሽቅድምድም ላይ እንዳይሳተፍ ሊታገድ ይችላል ተብሏል። የትናንቱ ሽቅድምድም አሸናፊ ዳኒኤል ሪካርዶ ሰባስቲያን ፌትል መረጋጋት እንደሚኖርበት ተናግሯል። 

በትናንቱ ሽቅድምድም በአጠቃላይ ነጥብ የሚመሩት ሌዊስ ሐሚልተን እና ሰባስቲያን ፌትል ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል። በውድድሩ ሰባስቲያን ቬተል አራተኛ እንዲሁም ሌዊስ ሐሚልተን አምስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። ዳንኤል ሪካርዶ አንደኛ፤ ቦታስ ሁለተኛ ሲወጣ በሦስተኛነት ያጠናቀቀው ስትሮል ነው። እስካሁን በተደረጉ ፉክክሮች በአጠቃላይ ነጥብ ሰባስቲያን ቬተል 153  ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚ ሲሆን፤ የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በ139 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ዳኒኤል ሪካርዶ ትናንት ለድል ያበቃውን ጨምሮ 92 ነጥብ በመሰብሰብ በሦስተኛነት ይከተላል። 

አትሌቲክስ
ፈረንሳይ ሊል ከተማ ውስጥ በተከናወነው የአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር የአውሮፓ ቡድን ውስጥ የታቀፈው የኤርትራው ስደተኛ አማናል ጴጥሮስ ሦስተኛ መውጣት ችሏል። የ22 ዓመቱ ወጣት ኤርትራዊው ስደተኛ ውድድሩን ያጠናቀቀውም 13:59,83 ሰከንድ በመሮጥ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች