ስፖርት፤ ሰኔ  12  ቀን፣ 2009 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 19.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ሰኔ  12  ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

በየአራት ዓመቱ የሚከናወነው የፊፋ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ቅዳሜ እለት በአስተናጋጇ ሩስያ እና ኒውዚላንድ ግጥሚያ ተጀምሯል። በሜዳ ቴኒስ ውድድር የብሪታንያው አንዲ ሙራይ ነገ ወሳኝ ግጥሚያ ያደርጋል። ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚከናወነው የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ጽጋቡ ግርማይ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:19

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የፊፋ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተከናውኗል፤ ውድድራቸውን ዛሬ እንዲያከናውኑ የተመደቡት ጀርመን እና አውስትራሊያ ናቸው። የኮንፌዴሬሽን  ዋንጫ  የሚያስገኘው የፍጻሜ ውድድር ላይ ለመድረስ 16 ጨዋታዎች መከናወን ይገባቸዋል። 

የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የሚከናወነው ልክ እንደ ዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ በየአራት ዓመቱ ነው። የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ለዓለም ዋንጫ ውድድር እንደመነቃቂያ እና የዝግጅት መሞከሪያ እንዲሆነው ውድድሩን የሚያከናውነው ከዓለም ዋንጫ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነው።  ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሩስያ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫን እያስተናገደች ስትገኝ፤ ለውድድሩ ከመላው ዓለም 8 ሃገራት ተካፋይ ናቸው።

ከስምንቱ የውድድሩ ተካፋዮች ስድስቱ በፊፋ የኮንፌዴሬሽን አሸናፊዎች አሸናፊ የአኅጉራት የዋንጫ ባለድሎች ናቸው። አንዱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፤ ሌላኛው ሃገር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ነው። በዚህም መሠረት ቅዳሜ እለት በጀመረው የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ከስምንቱ ተካፋይ ሃገራት አዘጋጇ ሩስያን ጨምሮ ኒው ዚላንድ፣ ፖርቹጋል እና ሜክሲኮ በምድብ አንድ ውስጥ ይገኛሉ። በምድብ ሁለት ደግሞ  የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን፤ ቺሊ፣ አውስትራሊያ እና  ካሜሩን ተካፋይ ናቸው። 

አፍሪቃን ወክላ ወደ ሩስያ ያቀናችው ካሜሩን ትናንት ሩስያ መዲና ሞስኮው ውስጥ ባደረገችው ግጥሚያ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን (CONMEBOL) አሸናፊዋ ቺሌ የ2 ለ0 ሽንፈት ደርሶባታል። 

በትናንትናው ግጥሚያ የእግር ኳስ ዳኞችን በውሳኔ አሰጣጥ ሊያግዝ ይችላል የተባለለት አዲስ ስነ-ቴክኒክ ማለትም ዳኛ ደጋፊ ቪዲዮ (Video Assistant Referee) ተግባራዊ ኾኗል። ፖርቹጋል እና ሜክሲኮ አቻ በወጡበት ውድድር  ዳኛ ደጋፊ ቪዲዮው  ውጤታማ ሆኖ ታይቷል። ሆኖም የካሜሩን እና የቺሌ ውድድር ላይ ግን ሥነ-ቴክኒኩ ከማወዛገብም አልፎ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (FIFA) በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ላይ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀው አመላክቷል። 

የቺሌው ኤድዋርዶ ቫርጋስ በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ያስቆጥራል፤ ዳኛውም ግቡን ያጸድቃሉ። አፍታም ሳይቆዩ ግን በዳኛ ደጋፊ ቪዲዮው መረጃ መሠረት ግብ ያሉትን ውሳኔ ከጨዋታ ውጪ በሚል ይሽሩታል። ብዙዎች ኤድዋርዶ ከጨዋታ ውጪ ነው የተባለበትን ቪዲዮ በመተቸት ትከሻው ብቻ ከመሥመር ማለፉ ከጨዋታ ውጪ ሊያስብል አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል። የሚገርመው ነገር ግን ቺሌ 2 ለ0 ባሸነፈችበት ጨዋታ አሌክሲስ ሳንቼዝ ግብ ያስቆጠረው ከጨዋታ ውጪ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ ዳኛ ደጋፊ ቪዲዮ መረጃ ቺሌን የጠቀመ ይመስላል። ዳኛው ግቡን አጽድቀውታል። 

ትናንት ቺሌ ካሜሩንን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ጨዋታም ልቆ ታይቷል። በትናንቱ ጨዋታ ለቺሌ አሌክሲስ ሳንቼዝ እና ቪዳል ግብ አስቆጥረዋል። በተለይ ቪዳል ከፍ ብሎ በመዝለል በጭንቅላት ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ተብላ ተመዝግባለች። ሐሙስ ዕለት በነበረው ልምምድ ወቅት ቁርጭምጭሚቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ላይሰለፍ ይችላል ተብሎ የነበረው የ28 ዓመቱ የአርሰናል አጥቂ  አሌክሲስ ሳንቼዝ ከቅያሬ መልስ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል። የቺሌው አሰልጣኝ ኹዋን አንቶኒዮ ፒሲ ከጨዋታው በፊት አሌክሲስ ላይሰለፍ እንደሚችል ስጋታቸውን እንዲህ ገልጠው ነበር።«እንደ ምርመራ ውጤቱ ከሆነ የሚሻለው ነው የሚመስለው። ባየነው ነገር ተስፋ አድርገናል። ግን ደግሞ እስዳስተዋልነው ከሆነ ትንሽ ኅመም ብጤ ስለሚሰማው በደንብ  ሊሻለው ይገባል። ስለዚህ በነገው ጨዋታ መሰለፍ አለመሰለፉን የምንወስንበት ይኾናል።»

አሰልጣኙ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል የወሰኑ ይመስላል።  ሆኖም አሌክሲስ ሳንቼዝ የቊርጭምጭሚት ጉዳቱ በደንብ እንዳልተሻለው አሳይቷል። አሌክሲስ ሳንቼዝ ከጨዋታው በኋላ ከመልበሻ ክፍል ውስጥ ሆኖ ያበጠ የግራ እግሩ ቁርጭምጭሚትን የሚሳያይ ምስል በማኅበራዊ መገናኛ አውታር አሰራጭጭቷል። 

ከትናንት በስትያ በመክፈቻው የመጀመሪያውን ጨዋታ ከአስተናጋጇ ሩስያ ጋር የተጋጠመችው ኒውዚላንድ  የ2 ለ0 ሽንፈት ደርሶባታል። ውድድሩ እስከ ሰኔ 25 ድረስ ይከናወናል።   

የኮንፌዴሬሽን ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፍጻሜን ብራዚል ለሦስት ጊዜያት በተከታታይ በአጠቃላይ ደግሞ ለ4 ጊዜያት አሸንፋለች።  ዋንጫው በተከታታይ ብራዚል እጅ ከመግባቱ አስቀድሞ ፈረንሳይ  የዛሬ 14 እና 16 ዓመት ለሁለት ጊዜያት አሸናፊ ኾናለች። ሜክሲኮ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1999 ብራዚልን ተከትላ ለአንድ ጊዜ የዋንጫ አሸናፊ መኾን ችላ ነበር።  

አትሌቲክስ 
ስዊድን መዲና ስቶክሆልም ውስጥ ትናንት በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት አማን ወቴ  በ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል።  ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የትናንቱ ውድድር ኬኒያዊው ቲሞቲ ቼሪዮት በ3 ደቂቃ ከ30 ነጥብ 77 ሰከንድ አንደኛ ሲወጣ፤ የባህሬኑ አልሳዲቅ ሚኮህ አማንን በሽርፍራፊ ሰከንዶች በልጦ በሁለተኛነት አጠናቋል። አልሳድቅ ሁለተኛ

የገባበት ሰአት ሦስት ደቂቃ ከ31 ነጥብ 49 ሰከንድ ነው። አማን ከአልሳዲቅ ከአንድ ሰከንድ ባነሰ ጊዜ ተበልጦ በሦስት ደቂቃ ከ31 ነጥብ 63 ሰከንድ ማጠናቀቅ ችሏል።  

ዓማን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ( IAAF) ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ ውድድር ላይ በዚሁ በ1500 ሜትር ርቀት ውድድር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 በማጣሪያው አንደኛ በመውጣት በፍጻሜው ሁለተኛ ግን ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል። 
በወቅቱ አማን ሁለተኛ በወጣበት ውድድር አሸናፊ የነበረው የጅቡቲው አትሌት አያንለህ ሱሌይማን የገባበት ሰአት አማን ትናንት ሦስተኛ ከወጣበት እጅግ ዘግየት ያለ ነበር። የያኔው የአንደኛ ደረጃ ውጤት 3 ሰአት ከ37 ነጥብ 52 ሰከንድ ነበር። 

በ3000 ሜትር መሰናከል ሩጫ የትናንቱ የስቶኮልም ዲያመንድ ሊግ ውድድር ደግሞ ጫላ በዮ 8 ደቂቃ ከ22 ነጥብ 65 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ሆኖ አጠናቋል። በዚህ ውድድር የኤርትራው አትሌት የማነ ኃይለ-ሥላሤ በሁለተኛነት ጨርሷል። የገባበት ሰአትም 8 ደቂቃ ከ18 ነጥብ 29 ሰከንድ ነበር። ሦስተኛ የወጣው የኬንያው አትሌት ኒኮላስ ኪፕታኑይ ነው። 

የብስክሌት ሽቅድምድም
ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚከናወነው የጎዳና ላይ የብስክሌት ሽቅድምድም 9ኛ ዙር ውድድር ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ጽጋቡ ግርማይ ትናንት ከ144 ተወዳዳሪዎች መካከል 42ኛ ደረጃ አግኝቷል።  እስከዛሬ በተደረጉ 9 ውድድሮች በተሰበሰበ ነጥብ ጽጋቡ ከ140 ብስክሌተኞች የ24ኛ ደረጃ ይዟል። ጽጋቡ ከቀደማቸው ብስክሌተኞች መካከል እስከ ሰላሳኛ ድረስ ያሉትን ለመጥቀስ ያህል፦ የቼክ ሪፐብሊኩ ያን ሒርት፣ የካናዳው ሚካኤል ውድስ፣ የኔዘርላንዱ ዳኣን ኦሊቨር እንዲሁም የኤርትራው መቅሰብ ደበሰይ፣ የቤልጂየሙ ፊሊፕ ጂልበርት እና 30ኛ የወጣው የስዊዘርላንዱ ሚሻኤል ሻዬር ይገኙበታል።  በአጠቃላይ ድምር ውጤት ከ140 ተወዳዳሪዎች መካከል የኤርትራው መርሐዊ ቅዱስ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ጠንካራ ብስክሌተኛነቱን አስመስክሯል። 

የሜዳ ቴኒስ
ብሪታንያዊው ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች አንዲ ሙራይ በነገው ዕለት ለስድስተኛ ጊዜ በኲዊንስ ክለብ የሚያደርገው የአዬጎን ውድድር በዋነኛው የዌብልዶን ፍልሚያ በተነቃቃ መንፈስ እንዲጓዝ እንደሚያደርገው ገልጧል።  አንዲ ሙራይ ነገ የሚገጥመው አልያጅ ቤዴቤን ነው።  «ውድድሩ በየዓመቱ ለዌምብልዶን ፍልሚያ እንድዘጋጅ ይረዳኛል» ብሏል።  የ30 ዓመቱ አንዲ ሙራይ ነገ በሚወዳደርበት «ኲዊንስ ክለብ» ያለፉትን ሁለት ዓመታት ማሸነፍ ችሏል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic