ስፖርት ሪፖርት | ስፖርት | DW | 24.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት ሪፖርት

በወቅቱ ብራዚል ውስጥ የሕዝብ ቁጣና ተቃውሞ ጋርዶት በመካሄድ ላይ ያለው የእግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜው ዙር ተሸጋግሯል።

ውድድሩና ያጀበው ተቃውሞ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ብቻ ሣይሆን ለመጪው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫና ከዚያም ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ አዘጋጆችም ፈታኝ ነገር መሆኑ አልቀረም። ሰንበቱ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችም ሲካሄዱበት ዛሬ ደግሞ በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት የቴኒስ ውድድሮች አንዱ የዊምብልደኑ መክፈቻ ዕለት ነው።

ብራዚል ውስጥ በፊታችን 2014 ዓ-ም የሚካሄደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ካነሣን ለዚሁ ለመድረስ በሚደረገው የአፍሪቃ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪቃን አሸንፎ የምድብ አንደኝነቱን ካረጋገጠ በኋላ ሁለት ቢጫ ካርድ ያገኘ ተጫዋች በማሰለፍ ስህተት መስራቱን ፌደሬሺኑ ቢያምንም የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ የምርመራ ውጤት ገና በይፋ አልቀረበም። ሆኖም ጉዳዩ አሁንም በማነጋገር ላይ ነው።

በብራዚሉ የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር እንጀምርና በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ የሰነበተው የመጀመሪያ ዙር ትናንት አብቅቶ አራት ቡድኖች ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል። በምድብ-አንድ ውስጥ አስተናጋጇ ብራዚል በጅምሩ ጃፓንን 3-0፤ ከዚያም ሜክሢኮን 2-0 እና ኢጣሊያንም 4-2 በመርታት የምድብ ጨዋታዋን በሙሉ ዘጠኝ ነጥቦች ስታጠቃልል በፍጹም ልዕልና ወደ ቀጣዩ ዙር መሻገሩ ሰምሮላታል።

የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ባለፉት በርካታ ወራት የቀድሞ ግርማ ሞገሱን እያጣ የመጣው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ሤሌሳዎ እንደገና የዓለም ዋንጫን የማግኘት ሕልም እንዲያልም እያደረገው ነው። የ 21 ዓመቱ ወጣት ኮከብ ኔይማር፣ ፍሬድና መሰሎቻቸው እስካሁን ባሣዩት ጨዋታ ቡድኑ በጥሩ ዕርምጃ ላይ እንደሚገኝ ለማስመስከር ችለዋል። ከኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ብዙም የራቁ አይመስሉም።

በምድብ-አንድ ውስጥ ኢጣሊያ ምንም እንኳ በብራዚል ብትሸነፍም 6 ነጥቦችን ይዛ በሁለተኝነት ለግማሽ ፍጻሜው ዙር ደርሳለች። የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን ሜክሢኮንና ጃፓንን ሲያሸንፍ ከብራዚል ባደረገው ግጥሚያም ግሩም ጨዋታ አሳይቶ ነበር። ሜክሢኮ በአንጻሩ ጃፓንን ብቻ 2-1 ስታሸንፍ በውድድሩ ሂደት ያን ያህል የተጠበቀው ጥንካሬ አልታየባትም። በመሆኑም ከምድቡ መጨረሻ ከጃፓን ጋር ከወዲሁ ከውድድሩ መሰናበቱ ግድ ነው የሆነባት።

በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓኝ እንደ ብራዚል ሁሉ ሶሥት ግጥሚያዎቿን በሙሉ በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥቦች ፍጹም ልዕልና ስታሳይ የደቡብ አሜሪካዋ ሻምፒዮን ኡሩጉዋይም ናይጄሪያንና ታሂቲን በማሸነፍ በሁለተኛነት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሻግራለች። የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ናይጄሪያ ታሂቲን ከማሸነፍ አልፋ የምድቡን ጠንካራ ተጋጣሚዎች ለመቋቋም አልቻለችም። በመሆኑም በሶሥት ነጥቦች ብቻ በመወሰን ከታሂቲ ጋር ከወዲሁ ስንብት ማድረጉ ግድ ነው የሆነባት።

የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በያዝነው ሣምንት አጋማሽ ላይ የሚካሄዱ ሲሆን እንዳጋጣሚ ታሪክ ራሱን የደገመ የሚመስልበት ሁኔታም ተፈጥሯል። አስተናጋጇ ብራዚል ከኡሩጉዋይ የምትጋጠም ሲሆን ኡሩጉዋይ በጎርጎሮሳውያኑ 1950 ዓ-ም ብራዚልን በአገሯ የዓለም ዋንጫን ነጥቃ የሄደች አገር እንደነበረች የሚታወስ ነው። ኡሩጉዋይ እርግጥ ከዚያን ወዲህ ደከም ብላ ብትቆይም በ 2010 የዓለም ዋንጫ አራተኛ በመውጣትና በዓመቱም የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮን በመሆን ብራዚልን ከኋላዋ ለማስቀረት በቅታ ነበር።

በመሆኑም ብራዚል በፊታችን ረቡዕ መጠንቀቅ እንደሚኖርባት አሰልጣኟ ፌሊፔ ስኮላሪ ራሳቸው ከማሳሰብ ወደ ኋላ አላሉም። ሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ በፊታችን ሐሙስ የሚካሄደው ባለፈው የአውሮፓ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሰው በነበሩት ሁለት አውሮፓውያን ቡድኖች በስፓኝና በኢጣሊያ መካከል ነው። የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ከ 2010 ዓ-ም ወዲህ በውድድር ግጥሚያዎች አንዴም ያልተሸነፈ ሲሆን በኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ናይጄሪያን 3-0 ሲረታ በተከታታይ 28ኛው መሆኑ ነበር። እናም የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓኝ አሁንም ለኢጣሊያ ቀላል ተጋጣሚ የምትሆን አይመስልም። የብዙ ታዛቢዎች ምኞት ደግሞ ብራዚልና ስፓኝ ለፍጻሜ ደርሰው ግሩም ጨዋታ ማየት ነው።

IAAF Athletik Weltmeisterschaften

በትናንትናው ዕለት በሰሜን-ምሥራቅ እንግሊዝ በጌትስሄድ በተጠናቀቀው ሁለት ቀናት የፈጀ የአውሮፓ የቡድን ሻምፒዮና ሩሢያ ለሶሥተኛ ዓመት በተከታታይ አሸናፊ ሆናለች። ሩሢያ ድሏን ለማረጋገጥ የቻለችው በተለይም ትናንት በመጨረሻዎቹ ሶሥት ዲሢፕሊኖች በርካታ ነጥቦችን በመሰብሰብ ነበር። ሩሢያ በአጠቃላይ 354 ተኩል ነጥብ ድሏን ስታረጋግጥ ጀርመን በ 347 ተኩል ሁለተኛ ሆናለች፤ በ 338 ነጥቦች ሶሥተኛ የወጣችው ደግሞ ብራታኒያ ናት። ጀርመን ከጠቅላላው አርባ ውድድሮች 37ቱ ተጠቃለው እየመራች ሳለ ሩሢያ መልሳ ግንባር ቀደም የሆነችው ዲሚትሪይ ታራቢን ጦሩን 85,99 ሜትር በመወርወር ካሸነፈ በኋላ ነበር።

ከዚያም በ 4x400 ሜትርና በሴቶች የክፍታ ዝላይ የተገኘው ውጤት ለሩሢያ የበላይነት ወሣኝ ሆኗል። በአጠቃላዩ ውጤት ከሩሢያ፣ ከጀርመንና ከብሪታኒያ ቀጥሎ ፈረንሣይ አራተኛ ስትሆን ፖላንድ አምሥተኛ፤ ኡክራኒያ ደግሞ ስድሥተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽመዋል። በተረፈ ከ 12ቱ ሃገራት መካከል የመጨረሻዎቹ ሶሥት ተሳታፊዎች ቤላሩስ፣ ግሪክና፣ ኖርዌይ ወደታች ሲከለሱ በሚቀጥለው ዓመት በቼክ ሬፑብሊክ፣ በስዊድንና በኔዘርላንድ የሚተኩ ናቸው።

ሞስኮ ላይ በፊታችን ነሐሴ ወር የሚካሄደው የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እየተቃረበ ሳለ አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ትናንት አዮዋ ላይ በ 200 ሜትር ሩጫ የዓመቱን ፈጣን ጊዜ 19,74 ሤኮንድ በማስገንዘብ የጃማይካው ኮከብ የዩሤይን ቦልት ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን አሳይቷል። ጌይ ባለፈው አርብ በ 100 ሜትርም ግሩም 9,75 ሤኮንድ ጊዜ ሲያመዘግብ በመጪው የዓለም ሻምፒዮና በሁለቱም ዲሢፕሊኖች ለመወዳደር በማቅማማት ላይ መሆኑም አልቀረም።

በአሜሬካው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በርናርድ ላጋት በ 5000 ሜትር ሲያሸንፍ በሴቶች በዚሁ ርቀት ጄኒፈር ሢምሰን ቀዳሚ ሆናለች። በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ኤቫን ዬገር ሲያሸንፍ በሴቶች 400 ሜትር መሰናክልም ዳሊላህ ሙሐማድ አንደኛ ወጥታለች።ከዚሁ ሌላ በወንዶች 800 ሜትር ዱዌይን ሶሎሞን ሲያሸንፍ አሊሢያ ጆንሰን ሞንታኖም በዚሁ ርቀት ቀዳሚዋ ነበረች።

ከዚህ ሌላ በምዕራባዊው ፈረንሣይ በበላንጉው ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረው 23ኛ ዓለምአቀፍ የአሥር ኪሎሜትር የጎዳና ሩጫ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ተሥፋዬ አበራና ፋንቱ እቲቻ ለድርብ ድል በቅተዋል።15 ሺህ ገደማ የሚጠጉ ተመልካቾች አደባባይ በወጡበት ውድድር 190 አትሌቶች ሲሳተፉ በወንዶቹ ከተሥፋዬ አበራ ቀጥለው የፈረንሣዩ አብደልአቲፍ ሜፍታህ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ኬንያዊው ሚልተን ሮቲች ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሴቶች ያለፈው ዓመት አሸናፊ ፈረንሣዊቱ ክሪስቴል ዳውናይ ፋንቱን ተከትላ ሁለተኛ ስትወጣ ኬንያዊቱ ሌዎኒዳ ሞሶፕ ደግሞ ሶሥተኛ ሆናለች።

ብራዚል ውስጥ በ 2014 ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለመድረስ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በሚደረገው ማጣሪያ ኢትዮጵያ በቢጫ ካርዶች የታገደ ተጫዋችን በማሰለፍ ቦትሱዋናን አሸንፋ ያገኘቻቸውን ሶሥት ነጥቦች መልሳ የማስረከቧ ሁኔታ አሁንም ማነጋገሩን የቀጠለ ጉዳይ ነው። ፌደሬሺኑ ባለፈው ሣምንት ስህተት መሠራቱን ሲያምን በሌላ በኩል ግን ይህን መሰሉ ነገር ወደፊት እንዳይደገም አስፈላጊውን ለውጥ በማድረጉ ረገድ ምን ዕርምጃ እንደሚወሰድ እስካሁን በተጨባጭ የሚታወቅ ነገር የለም።

ሆኖም ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት የፌደሬሺኑ ዋና ጸሐፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ ሥራቸውን እንዲለቁ መወሰኑ፤ ምክትላቸው አቶ ብርሃኑ ከበደ ያቀረቡት የስንብት ማመልከቻም እንዲሁ የፌደሬሺኑን ተቀባይነት ማግኘቱ ተነግሯል። ፌደሬሺኑ ጠቅላይ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባው ግዮን ሆቴል ተሰብስቦ ሲውል በርካታ ውሣኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ እየተጠበቀም ነው። ውሣኔው የፌደሬሺኑን ተግባር ተገቢውን መስመር ለማስያዝ የሚበጅ ከሆነ ምንኛ በበጀ!

ኢትዮጵያ ከሶሥት ዓሠርተ-ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ አፍሪቃ የእግር ኳስ መድረክ ከተመለሰች ወዲህ ብዙ ነገር ተለውጧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ መልሶ ትንሣዔ እያደረገና ብሄራዊ ተጫዋቾቹም የሕዝብ መኩሪያ እየሆኑ ሲሄዱ እስካሁን ያስመዘገቡት ውጤት አገሪቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳትፎ የማብቃትን ተሥፋ የሚያዳብር ነው።

እርግጥ ትግሉ ፍሬ እንዲሰጥ ተገቢው አመራር፣ ግልጽ የሥራ ክፍፍልና በፌደሬሺን ደረጃ ሳይቀር የአሠራር ዲሲፕሊን መኖሩ ግድ ነው። ይህ ቢሆን ኖሮ የማይፈቀድለትን ተጫዋች በማሰለፍ ቡድኑን ችግር ላይ ሊጥል የሚችል አደጋ ባልተፈጠረ ነበር። ፌደሬሺኑ ዛሬ ምንም ወሰን ምን የስፖርቱ ባለሙያዎች ሚና ከፍ የሚልበት ሁኔታ ካልተመቻቸ የረባ ለውጥ መጠበቁ አዳጋች ነው የሚሆነው።

በተቀረ የዘንድሮው የዊምብልደን የቴኒስ ውድድር በዛሬው ዕለት ሲከፈት የመጀመሪያውን ዙር ውጤቶች በጥቂቱ ለመጥቀስ በወንዶች የስዊሱ ሮጀር ፌደረር የሩሜኒያ ተጋጣሚውን ቪክቶር ሃኔስኩን 6-3,6-2,6-0 ሲያሸንፍ የአውስትሪያው ዩርገን ሜልሰር ደግሞ የኢጣሊያውን ፋቢዮ ፎግኒኒን እንደዚሁ በሶሥት ምድብ ጨዋታ ሶሥት ለባዶ ረትቷል። በሴቶችም ሰርቢያዊቱ አና ኢቫኖቪች የፈረንሣይ ተጋጣሚዋን ቨርጂኒ ራዛኖን 7-6,6-0 ረትታለች።

በሌላ በኩል የፖርቶ ሪኮዋ ሞኒካ ፑዊግ ኢጣሊያዊቱን ሣራ ኤራኒን ባልታሰበ ሁኔታ ማሸነፏ ማንም የጠበቀው አልነበረም። በወንዶች ከሮጀር ፌደረር ሌላ ራፋኤል ናዳል፣ ኤንዲይ መሪይና ኖቫክ ጆኮቪች ታላላቆቹ ተሳታፊዎች ሲሆኑ የሴቶቹ ውድድር በተለይም የሤሬና ዊሊያምስና የማሪያ ሻራፖቫ የሻምፒዮንነት ፉክክር የሰመረበት ሆኖ እንደሚሰነብት ይጠበቃል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic