ስፖርት ሪፖርት | ስፖርት | DW | 29.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት ሪፖርት

የያዝነው ሣምንት እንደገና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ ጨዋታ አፍቃሪዎችን ልብ የሚስቡ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች የሚጠበቁበት ነው።

የጀርመንና የስፓኝ ክለቦች ፉክክር መጨረሻው ምን ይሆናል? በመጀመሪያው ግጥሚያ ከባድ ሽንፈት የደረሰባቸው የስፓኝ ክለቦች ሊያገግሙ ይችላሉን? ንጹህ የጀርመን ክለቦች ፍጻሜ ወይስ ሌላ ውጤት? ይህ ሁሉ በወቅቱ ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፤ ወደ ኋላ ላይ እንመለስበታለን። 

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ብሄራዊ ሻምፒዮና እንጀምርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ በሰንበቱ ግጥሚያው ከአርሰናል 1-1 ቢለያይም ውድድሩ ሊጠቃለል አራት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ በ 85 ነጥቦች አንደኝነቱን እንዳረጋገጠ ቀጥሏል። ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ ዌስት ሃም ዩናይትድን 2-1 ሲረታ አንድ ግጥሚያ ጎሎት በ 71 ነጥቦች ሁለተኛ ነው።                                                                                                 

ቼልሢይ በፊናው ከመጀመሪያዎቹ አራት ክለቦች አንዱ በመሆን ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ለመብቃት በተያዘው ትግል ስዋንሢን 2-0 በማሸነፍ ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጓል። በ 65 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። የቅርብ ተፎካካሪው አርሰናል በአንጻሩ ነጥብ በመጣሉ ከሶሥት ወደ አራተኛው ቦታ ተንሸራቷል። በጥቅሉ ማንቼስተር ዩናይትድ ሻምፒዮንነቱን የማያጠያይቅ ነገር ባደረገበት ወቅት ለሁለት ዝቅተኛ ክለቦች ደግሞ ሰንበቱ የስንብት ነው የሆነው።

ሪዲንግና ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ በፕሬሚየር ሊጉ ውስጥ ለመቆየት ያደረጉት ረጅም ትግል  የታሰበውን ፍሬ አልሰጠም። ሁለቱ ክለቦች በሰንበቱ ግጥሚያቸው በ 0-0 ውጤት ሲወሰኑ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለሳቸው ከወዲሁ ተረጋግጧል። በጎል አግቢነት ፕሬሚየር ሊጉን የማንቼስተር ዩናይትድ ሆላንዳዊ አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርሢ 25 አስቆጥሮ የሚመራ ሲሆን በ 23 ጎሎች ሁለተኛው የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬስ ነው።                                        

በነገራችን ላይ የቶተንሃም ሆትስፐር የመሃል ሜዳ ኮከብ ጋሬት ቤል የእንግሊዝ ፕሮፌሺናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር የዓመቱ ድንቅ ተጫዋጭና የዓመቱ ወጣት ተጫዋች በመባል ተመርጧል። ከዌልስ የመነጨው የ 23 ዓመት ወጣት በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለክለቡ 19 ጎሎችን ሲያስቆጥር ለዚህ ክብር የበቃው ሶሥተኛው ተጫዋች መሆኑ ነው።  

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደምቱ ባርሤሎና ባለፈው ሰንበት ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ቡድኑ ከአትሌቲክ ቢልባኦ 2-2 መለያየቱ ነው። ባርሣ ተቀይሮ በገባው አርጄንቲናዊ ኮከቡ በሊዮኔል ሜሢና በአሌክሢስ ሣንቼዝ አማካይነት 2-1 ሲመራ ድል የነሳችው ጎል የተቆጠረችው ባለቀ ሰዓት ላይ ነበር። ባርሤሎና ይሁንና በ 85 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ምናልባትም በሚቀጥለው ሰንበት ይቀናው ይሆናል። በወቅቱ የ 11 ነጥቦች ብልጫ አለው።

በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ሁለተኛና ሶሥተኛ ክለቦች በሬያል ማድሪድና በአትሌቲኮ ማድሪድ መካከል የተካሄደው ግጥሚያ ደግሞ በሬያል የ 2-1 ድል ተፈጽሟል። ሬያል ማድሪድ ከሰንበቱ ግጥሚያ በኋላ በ 74 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን አትሌቲኮ በ 68 ሶሥተኛ ነው፤ ሬያል ሶሢየዳድ፣ ማላጋና ቫሌንሢያ ፈንጠር ብለው ይከተላሉ። በጎል አግቢነት ቀደምቱ ሪኮርድ 44 ግቦችን ያስቆጠረው ሊዮኔል ሜሢ ነው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከሬያል ማድሪድ በ 31 በሁለተኝነት ይከተላል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ከሁለት ሣምንታት በፊት ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሰንበትም ድክመት ሳይታይበት ፍራይቡርግን 1-0 በመርታት ነጥቦቹን ወደ 84 ከፍ አድርጓል። ቀደምት ኮከቦቹን ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የመልስ ግጥሚያ ለማሳረፍ በተቀያሪዎች ለተጫወተው ክለብ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ሤርዳን ሻኪሪ ነበር። ሁለተኛው ቦሩሢያ ዶርትሙንድም በተመሳሳይ ሁኔታ ዱስልዶርፍን 2-1 በማሸነፍ ሰንበቱን በስኬት አሳልፏል።                                                                             

ሶሥተኛው ሌቨርኩዝን በአንጻሩ አከራካሪ በሆነች ፍጹም ቅጣት ምት ነው በወቅቱ ብርቱ ችግር ገጥሞት የሚገኘውን ብሬመንን 1-0 የረታው። በዳኛ ስህተት የተከተለው ሽንፈቱ ብሬመንን አስጊ የመከለስ አደጋ ላይ የጣለ ነው። በተቀረ 18ኛው ግሮይተር ፉርት በሃኖቨር በደረሰበት 3-2 ሽንፈት በዓመቱ ከወዲሁ መከለሱ ሲረጋገጥ ሆፈንሃይም፣ አውግስቡርግና ዱስልዶርፍም ገና ፈተና ላይ እንዳሉ ናቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ጎረቤቱን ቶሪኖን 2-0 በማሸነፍ ናፖሊን በ 11 ነጥቦች አስከትሎ መምራቱን ሲቀጥል በፊታችን ሰንበት ፓሌርሞን ካሸነፈ ወይም እኩል-ለእኩል ከተለያየ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን ያረጋግጣል። ለዩቬ በመጨረሻዎቹ አምሥት ደቂቃዎች ጎሎቹን ያስቆጠሩት አርቱሮ ቪዳልና ክላውዲዮ ማርኪዚዮ ነበሩ። ናፖሊ ሁለተኛ ሲሆን ኤሢ ሚላን ሶሥተኛ ነው፤ ፊዮሬንቲና ድግሞ በአረተኝነት ይከተላል። በጎል አግቢነት ቀደምቱ 23 ያስቆጠረው የናፖሊው ኤዲንሶን ካባኒ ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ኤቪያንን 1-0 በመርታት ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በስኬት መራመዱን ቀጥሏል። ፔ እስ ዤ በዘጠኝ ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማርሢይ ሁለተኛ ነው፤ ኦላምፒክ ሊዮን ደግሞ በሶሥተኝነት ይከተላል። በጎል አግቢነት ሊጋውን የሚመራው እስካሁን 27 ያስቆጠረው የፓሪሱ ክለብ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ነው።                                                                  

በኔዘርላንድ አያክስ አምስተርዳም ብሬዳን 2-0 በማሸነፍ ለሻምፒዮንነት በጣሙን ተቃርቧል። ክለቡ ውድድሩ ሊጠቃለል ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ በአራት ነጥቦች ብልጫ መሪ ሆኖ ነው የሚገኘው። አይንድሆፈንና ፋየኖርድ በእኩል ነጥብ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሲሆኑ እርግጥ አያክስ ከተሰናከለ ገና ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። በፖርቱጋል ፕሪሜራ ሊጋም ውድድሩ ሊጠቃለል ሲቃረብ የቤንፊካ ሊዝበንና የፖርቶ የሻምፒዮና ፉክክር ባለበት እንደቀጠለ ነው። በኡክራኒያ ደግሞ ቀደምቱ ክለብ ሻህትያር ዶኔትስክ ትናንት ለተከታታይ አራተኛ ሻምፒዮንነቱ በቅቷል።

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ሁኔታ ከሞላ ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን በፕሮግራማችን መግቢያ ላይ እንደጠቀስነው ሣምንቱን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን ልብ ምርኮኛ እንዳደረገ የቀጠለው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ነው። የጀርመንና የስፓኝ ፉክክር በሰፈነበት ግማሽ ፍጻሜ  ባለፈው ሣምንት ባየርንና ዶርትሙንድ ሃያላኑን የአይቤሪያ ክለቦች 8 ጎሎች አስገብተው የሸኙበት ሁኔታ አሁንም ብዙዎችን ማስገረሙን የቀጠለ ጉዳይ ነው።

የመልስ ግጥሚያዎቹ ደግሞ ነገና ከነገ በስቲያ ረቡዕ በስፓኙ ክለቦች አስተናጋጅነት በዝነኞቹ ቤርናቤዉና ኑው-ካምፕ ስታዲዮሞች ይካሄዳሉ። የጀርመኑ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ  ባርሤሎናን ያህል ሃያል ክለብ 4-0 አሸንፎ ሲሸኝ ሁለተኛው የጀርመን ክለብ ዶርትሙንድም ሬያል ማድሪድን 4-1 መርታቱ አይዘነጋም። ይህ ያልተጠበቀ ውጤት የስፓኙን ክለቦች አሁን በመልሱ ግጥሚያ ዋዜማ ብርቱ ፈተና ላይ ጥሎ ነው የሚገኘው። ቢሆንም በስፖርት ተሥፋ አይቆረጥምና ተሸናፊዎቹ ክለቦች ጨርሶ አልቆላቸዋል ለማለት አይቻልም።

ለነገሩ የስፓኙ ክለቦች በተለይም ባርሤሎና በውጭ ሜዳ በብዙ ጎሎች የደረሰበትን ሽንፈት በመልስ ጨዋታው በሜዳው ማጠፉ በየጊዜው ታሳክቶለታል። ችግሩ ምናልባት በተለይም ባየርን ሙንሺን በብርቱ ጥንካሬ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው። ሬያልም ሆነ ባርሤሎና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የራሳቸውን በሮች ሳያስደፍሩ ቀድመው ስኬት ለማግኘት በተለየ ትኩረት መጫወት ይጠበቅባቸዋል። ጎል ቀድሞ ከገባባቸው ግን በበኩላቸው አምሥትና ስድሥት ጎሎች ማስቆጠር ስለሚኖርባቸው ዕድላቸው ይብስ የቀጨጨ ነው የሚሆነው።

ባርሣን በተመለከተ የባየርኑ አሠልጣን ዩፕ ሃይንከስ በዓለም ዝናን ያተረፈው የስፓኝ ግንባር ቀደም ክለብ  ከዚህ ቀደም ብዙ ሽንፈቶችን መገልበጡን በማስገንዘብ የጀርመኑ ክለብ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም ለሚደረገው ፍጻሜ ለመድረስ ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀው ነው የተናገረው። የዘጠኝ ጊዜው የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ሬያል ማድሪድም በዶርትሙንድ የደረሰበትን የ 4-1 ሽንፈት ለማጠፍ ያለፉ ተመሳሳይ ጨዋታዎች ስኬቱን በማንሣት የደጋፊዎችና የተጫዋቾቹን መንፈስ ሲያነቃቃ ነው የሰነበተው። በነገው ምሽት ግጥሚያው ምናልባትም በዶርትሙንድ ሜዳ ያስቆጠራት ጎል የስኬት ዋስትናው ልትሆን ትችል ይሆናል። ለማንኛውም ሁሉንም ጠብቀን እንደርስበታለን።

በዚህ በጀርመን ትናንት ተካሂዶ በነበረ የዱስልዶርፍ ከተማ ዓለምአቀፍ ማራቶን በወንዶችና በሴቶችም የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች አሸናፊዎች ሆነዋል። በወንዶች ደረጀ ቱሉ በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከ 48 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ኬንያውያኑ ፒዩስ ኦዶሮና ዳንካን ኮች ሁለተኛና ሶሥተኛ ወጥተዋል። ጊዜው ለዱስልዶርፍ እስካሁን ፈጣኑ መሆኑ ነው። በሴቶች ደግሞ መልካም ግዛው ኬንያዊቱን ሬቤካቼ ቼሢሬን በአንድ ደቂቃ ተኩል ጊዜ ከኋላዋ በማስቀረት ስታሸንፍ የፖላንዷ አግኔትስካ ሚርዤቭስኪም ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች።

በዩ ኤስ አሜሪካ-አዮዋ በተካሄደ የፔን-ሬሌይስ አትሌቲክስ ውድድር ደግሞ ጃማይካዊው አንድሩው ራይሊይ በ 110 ሜትር መሰናክል ሩጫ የለንደኑን ኦሎምፒክ ወርቅ ተሸላሚና የዓለም ሻምፒዮን አሪስ ሜሪትን ቀድሞ ለማሸነፍ በቅቷል። በውድድሩ ከዚሁ ሌላ አሜሪካውያኑ ማይክል ቲንስሊይ በ 400 ሜትር መሰናክልና ጄኒይ ሲምሰን በ 1,500 ሜትር፤ እንዲሁም የኩባው አትሌት ያሪስሊይ ሢልቫ በምርኩዝ ዝላይ በወቅቱ በዓለም ላይ ቀደምት የሆነ ውጤት አስመዝግበዋል።                                                       

በሴቶች የርዝመት ዝላይም አሜሪካዊቱ የኦሎምፒክና የሁለት ጊዜዋ የዓለም ሻምፒዮን ብሪትኒይ ሪስ አሸናፊ ሆናለች።  በረጅም ርቀት ሪሌይም የኢትዮጵያ አትሌቶች በረከት ደስታ፣ መሐመድ አማን፣ አብዮትና አማን ወቴ ኬንያውያንን ቀድመው አሸንፈዋል።

በትናንትናው ዕለት በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ሲደረጉ በባርሤሎና-ኦፕን በስፓኝ ተጋጣሚዎች መካከል በተካሄደ ጨዋታ ራፋኤል ናዳል ኒኮላስ አልማግሮን በለየለት 6-4,6-3 ውጤት አሸንፏል። ናዳል በጉልበት ጉዳት ሳቢያ ሰባት ወራት አርፎ ከተመለሰ ካለፈው የካቲት ወዲህ በስድሥት ውድድሮች ከፍጻሜ ሲደርስ ከትናንቱ የባርሤሎና ድሉ ሌላ በሣኦ ፓውሎ፣ አካፑልኮና በኢንዲያን ዌልስ ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የባርሤሎናው ድሉ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ስምንተኛው መሆኑም ነበር።

በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት ዓለምአቀፍ ውድድር ደግሞ ማሪያ ሻራፖቫ የቻይና ተጋጣሚዋን ሊ ናን ግሩም በሆነ አጨዋወት 6-4,6-3 በማሸነፍ ያለፈውን ዓመት ድሏን ደግማዋለች። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በወቅቱ ከሤሬና ዊሊያምስ ቀጥላ ሁለተኛ የሆነችው ሩሢያዊት በዚህ ግጥሚያ ፍጹም የበላይነት ነው ያሳየችው። በጥንድ ጀርመናውያኑ ዛቢነ ሊሢስኪና ሞና ባርቴል በፍጻሜው የአሜሪካና የሕንድ ጥንድ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ከዚሁ ሌና በማራኬሽ ዓለምአቀፍ ግጥሚያ ትናንት ኢጣሊያዊቱ ፍራንቼስካ ሺያቮኔ የስፓኝ ተጋጣሚዋን ሎውርድስ ዶሚንጌስን 6-1,6-3 ስታሸንፍ የቡካሬስት ባለድል ደግሞ የቼኩ ሉካስ ሮሶል ሆኗል። 

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic