ስፖርት ሪፖርት | ስፖርት | DW | 12.11.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት ሪፖርት

የብራዚል እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሩ ውቅቱ ሊጠናቀቅ ገና ሶሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ትናንት ከወዲሁ ለይቶለታል። የዘንድሮው ሻምፒዮንም በግሩም ጨዋታ ፓልሜራስን 3-2 የረታው ፍሉሚኔንዘ ነው።

የብራዚል እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሩ ውቅቱ ሊጠናቀቅ ገና ሶሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ትናንት ከወዲሁ ለይቶለታል። የዘንድሮው ሻምፒዮንም በግሩም ጨዋታ ፓልሜራስን 3-2 የረታው ፍሉሚኔንዘ ነው። ለፓልሜራስ የትናንቱ ሽንፈት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን የመከለስ ብርቱ አደጋን ነው የደቀነው። ቡድኑ ከትናንቱ ግጥሚያ ወዲህ ሃያ ክለቦችን በያዘው ሊጋ ውስጥ ወደ 18ኛው ቦታ አቆልቁሏል። ፍሉሚኔንዘ በበኩሉ በድንቅ አምበሉ በፍሬድ እየተመራ በሶሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ሻምፒዮንነቱ  ሲበቃ በ 35 ጨዋታዎች እስካሁን 76 ነጥቦችን መሰብሰቡም አቻ የሌለው ነው።                         

የፍሉሚኔንዘን የተለየ ጥንካሬ ሁለተኛው ግሬሚዮ በአሥር ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሚገኝ መሆኑ በጉልህ ያሳያል። ለክለቡ የዘንድሮው ድል በጥቅሉ አራተኛው ብሄራዊ ድል መሆኑ ነው። የቡድኑን ሻምፒዮንነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ባለፈው ምሽት በደቡባዊው የሪዮ አውራጃ በሚገኝ የክለቡ መቀመጫ ተሰብስበው ሲያከብሩ በየመንገዱ ታላቅ የትራፊክ መጨናነቅ ሰፍኖ ነው ያደረው። በተረፈ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለስ ከሚኖርባቸው አራት የመጨረሻ ክለቦች የሁለቱ ማንነት ከወዲሁ ለይቶለታል።

ብራዚልን ካነሳን ብሄራዊ ቡድኗ በሣምንቱ አጋማሽ በዓለም ዙሪያ ከሚካሄዱት በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎች የአንዱ ተሳታፊ ነው። ብራዚል የምትገናኘው ከኮሉምቢያ ጋር ሲሆን የሁለቱም ክለቦች የማጥቃት አጨዋወት ግጥሚያውን የደመቀ እንደሚያደርገው ይጠበቃል። አሠልጣኙ ማኖ ሜኔዜስ የአምሥት ጊዜዋን የዓለም ዋንጫ ባለቤት የተለመደ የአጨዋወት ስልት መልሶ ለማስፈን በያዙት ጥረት የካካ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ዓለምአቀፉ ውድድር መድረክ መመለስ ፍሬያማ ሣይሆን አልቀረም።                                                                                 

ቡድኑ ባለፈው ወር ከኢራቅና ከጃፓን ጋር ባካሄዳቸው ሁለት ግጥሚያዎች አሥር ጎሎችን ሲያስቆጥር የኦስካርና የካካ የመሃል ሜዳ መሃንዲስነት ከኔይማር የማጥቃት ጥንካሬ ተዋህዶ በዕውነትም ቡድኑን ሃያል እያደረገው ነው። ብራዚል ባለፈው ሰኔ ወር በአርጄንቲና አንዴ ከመሸነፏ በስተቀር ያለፉትን ስድሥት ግጥሚያዎቿን በሙሉ በድል ነበር የፈጸመችው። ይህ ደግሞ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዚያው በአገሪቱ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ተሥፋን የሚያጠናክር ነው።                                   

የብራዚል ሕዝብ እንደ አዘጋጅ አገር ቀርቶ ባይሆንም እንኳ በ 2014 በሚያስተናግደው ውድድር ከዋንጫ ድል ያነሰ ነገር እንደማይጠብቅ የማያውቅ የለም። በመሆኑም የቡድኑ እንደገና መጠናከርና ወደ ቀድሞ ጥበቡ መመለስ የሚያስደስተው ብራዚላውያኑን ብቻ ሣይሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሣምባ አጨዋወት ስልት አፍቃሪዎችን ሁሉ ነው። እርግጥ የቡድኑ ለዚህ ተሃድሶ መብቃት ገና እያደር የሚታይ ይሆናል።  

በመጪው ረቡዕ ምሽት ዓለምአቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሌሎች ማራኪ ጨዋታዎችም ሲኖሩ ከነዚሁ መካከልም ለምሳሌ ጀርመን ከኔዘርላንድ፤ ኢጣሊያ ከፈረንሣይና ስዊድን ከእንግሊዝ ጠንካሮቹ ናቸው። በተቀረ የዓለምና የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓን ከፓናማ፤ ጎረቤቷ ፖርቱጋል ከጋቦን፤ አልባኒያ ከካሜሩን፤ ካፕ ቬርዴ ከጋና፤ አርጄንቲና ከሳውዲት አረቢያና ሩሢያም ከዩ ኤስ አሜሪካ ይጋጠማሉ።

Marathonlauf an historischer Stätte

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት የተካሄደው 30ኛ የአቴን ክላሢክ ማራቶን ሩጫ ውድድር አሸናፊ ኬንያዊው ሬይመንድ ቤት ሆኗል። አምሥት ሌሎች ኬንያውያንም የ 28 ዓመቱን አሸናፊ ተከትለው ሲገቡ ፓውል ኮስጋይ ሁለተኛ፤ እንዲሁም አሌክስ ኪሩዊ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። ከሁለት ዓመት በፊትም አሸናፊ የነበረው ሬይመንድ ቤት ትናንት ድሉን የደገመው ባለፈው ዓመት የሞሮኮው ሯጭ አብደልከሪም ቡብከር በስፍራው አስመዝግቦት የነበረውን ጊዜም በማሻሻል ነው።                                                   

የፈጀበት ጊዜ ሁለት ሰዓት ከ 11 ደቂቃ ከ 35 ሤኮንድ ሲሆን ለነገሩ በንጽጽር ፈጣን የሚባል አልነበረም። ለማንኛውም በሴቶችም እንዲሁ ኬንያዊቱ ቼምታይ ያዳአ ስታሸንፍ የኡክራኒያ ተወዳዳሪ ስቪትላና ስታንኮ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ኬንያዊቱ ቪዮላ ኪሜቶ ሶሥተኛ ወጥታለች። በአቴኑ ክላሲክ ማራቶን በደርዘን ከሚቆጠሩ ሃገራት የተጓዙ 26 ሺህ ራጮች ተሳርፈዋል።                                                                                             

ሌላው የማራቶን ዜና ቻይና ከሁለት ሣምንት በኋላ በሚካሄደው የቤይጂንግ ማራቶን የጃፓን አትሌቶች እንዳይሳተፉ ያደረገችውን ውሣኔ መልሳ ማጠፏ ነው። እገዳው የተጣለው በሁለቱ ሃገራት የግዛት ውዝግብ የተነሣ በተፈጠረው ውጥረት ለስፖርተኞቹ የደህንነት ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም በሚል ነበር። ውሣኔው የተቀየረው በቤይጂንግ የጃፓን ኤምባሲም የበኩሉን ተቃውሞ ካሰማ በኋላ ነው።

ከዚህ ሌላ የሩሢያ ጸረ-ዶፒንግ ተቋም የአገሪቱ የለንደን ኦሎምፒክ የዲስክ ውርወራ የብር ሜራይ ተሸላሚ ዳርያ ፒሻልኒኮቫ ያልተፈቀደ የአካል ማዳበሪያ መድሃኒት መውስዷ በምርመራ የተደረሰበት መሆኑን አስታውቋል። የተቋሙ ባለሥልጣን ኒኪታ ካማየቭ እንዳስረዱት ጉዳዩ ለዓለም ጸረ-ዶፒንግ አካል ለዋዳ ቀርቦ ምርመራ እየተካሄደ ነው። የሩሢያ የረጅም ርቀት ሯጭ ኢንጋ አባቶቫ ደግሞ በተመሳሳይ ድርጊት የተነሣ ለሁለት ዓመት መታገዷን የአገሪቱ አትሌቲክስ ፌደሬሺን ባለፈው ሣምንት ገልጾ ነበር።                                          

በተቀረ የቪየትናም ርዕሰ-ከተማ ሃኖይ ከሰባት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን የ 2019 የእሢያ ጨዋታ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች። ቪየትናም ከዚህ ቀደም ያዘጋጀችው ታላቅ የስፖርት ትዕይንት የ 2003 የደቡብ ምሥራቅ እሢያ ጨዋታ ነበር። መጪውን የእሢያ ጨዋታ በ 2014 ደቡብ ኮሪያ የምታስተናግድ ሲሆን 18ኛው የእሢያ ጨዋታ በአራት ዓመት ፈንታ አምሥት ዓመት ቆይቶ የሚካሄደው በዝግጅት ምክንያት ነው።    

ወደ እግር ኳሱ ስፖርት እንመለስና በመጀመሪያ ዙሩ ላይ በሚገኘው የአውሮፓ ሊጋዎች ሻምፒዮና የቀደምቱ ክለቦች ፉክክር አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ሬያል ማዮርካን 4-2 በመርታት በ 11 ግጥሚያዎች ለአሥረኛ ድሉ ሲበቃ ሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድም በበኩሉ ጨዋታ ጌታፌን በቀላሉ አሸንፏል። ባርሣ ሁለት-ለባዶ ከተመራ በኋላ ወጤቱን ለውጦ ለማሸነፉ በተለይም ድንቅ ተጫዋቹን ሊዮኔል ሜሢን ሊያመሰግን ይገባዋል። ሶሥተኛው ሬያል ማድሪድ  ሌቫንቴን 2-1 ረትቶ ጠቃሚ ነጥቦቹን ለማረጋገጥ ብዙ መታገል ነበረበት። ሬያል በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር በሶሥተኝነቱ  ሲቀጥል ከሊጋው መሪ ከባርሤሎና ስምንት ነጥቦች ይለዩታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ሁለቱ የማንቼስተር ክለቦች ግንባር ቀደም እንደሆኑ ቀጥለዋል። ማንቼስተር ዩናይትድ ኤስተን ቪላን 3-2 በማሸነፍ  ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ  በ 27 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማንቼስተር ሢቲይም ቶተንሃምን 2-1 በመርታት በ 25 ነጥቦች ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። ቼልሢይ በአንጻሩ በገዛ ሜዳው ከሊቨርፑል 1-1 ሲለያይ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ማቂልቆሉ ግድ ነው የሆነበት። እርግጥ ከአመራሩ የሚለየው በሶሥት ነጥቦች ብቻ በመሆኑ አሰላለፉ በቀላሉ ሊለወጥ የሚችል ነው። በዚሁ የጠበበ የነጥብ ልዩነትም ሻምፒዮናው ማራኪ እንደሆነ ይቀጥላል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ብዙዎች ታዛቢዎች ቀደም ብለው እንደተነበዩለት  በፍጹም ልዕልና መምራቱን ሲቀጥል ሊጋውን በሰባት ነጥቦች ልዩነት በማያሻማ ሁኔታ ይመራል። ባየርን ባለፈው ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያ የፈረንሣዩን ክለብ ሊልን 6-1 ቀጥቶ ሲሸን ስንበቱን ያሳለፈውም ያለብዙ ድካም ፍራንክፉርትን 2-0 በመርታት ነበር። ሻልከ በዕድልም ቢሆን ብሬመንን 2-1 በማሸነፍ በሁለተኝነቱ ሲጸና ፍራንክፉርትና ዶርትሙንድ ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ፔስካራን 6-1 በመርታት የሊጋ አመራሩን በአራት ነጥቦች ለማስፋት ችሏል። ከስድሥት ሶስቱን ጎሎች ለብቻው ያስቆጠረው ፋቢዮ ኩዋግሊያሬላ ነበር። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ጁቬንቱስ አመራሩን ያሰፋው በአንዲት ነጥብ ብቻ በመበለጥ በቅርብ ይከተል የነበረው ሁለተኛው ኢንተር ሚላን በአታላንታ 3-2 በመሸነፉ ነው። ናፖሊ፣ ፊዮሬንቲናና ላሢዮም በየበኩላቸው ግጥሚያ ሲያሸንፉ ከሶሥት እስከ አምሥት የሚከተሉት ክለቦች ናቸው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ተጫዋቹ ማማዱ ሣኮ ቀድሞ ከሜዳ ሲወጣበት አመራሩን እንዳይነጠቅ ለጥቂት ነው ያመለጠው። ፓሪስ በጎዶሎ በመጫወት ካለፈው ሻምፒዮን ከሞንትፔልየር 1-1 ሲለያይ ለጊዜው በጎል ብልጫ ይመራል። ሆኖም ሁለተኛው ኦላምፒክ ማርሤይ በእኩል 23 ነጥብ የሚከተለው ገና አንድ ጨዋታ ጎሎት ነው። ኦላምፒክ ሊዮንም ከሶሾ እኩል-ለእኩል በመለያየት በ 21 ነጥቦች በሶሥተኝነት ተወስኗል። በፈረንሣይ ሻምፒዮና አንደኛውን ከዘጠነኛው የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ሲሆኑ ፉክክሩ ሳይለይለት ብዙ የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን አይንድሆፈን ሄረንፌንን 5-1 በመቅጣት በ 30 ነጥቦች አመራሩን ከትዌንቴ ነጥቋል። ትዌንቴ ኤንሼዴ ከአርንሃይም ባዶ-ለባዶ ሲለያይ  አሁን በ 29 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ከዚሁ ሌላ ቪቴስ አርንሃይም በ 25 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን አያክስ አምስተርዳምም በ 21 አራተኛ ሆኖ ይከተላል። በፖርቱጋል አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ፖርቶና ቤንፊካ ሊዝበን በየበኩላቸው ግጥሚያ ሲያሸንፉ በ23 ነጥቦች በጋርዮሽ መምራታቸውን እንደቀጠሉ ነው።

ቴኒስ

ለንደን ላይ በሚካሄደው የዓመቱ መደምደሚያ የኤቲፒ ማጠቃለያ ግጥሚያዎች የስዊሱ ሮጀር ፌደረርና የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች ጠንካራ በሆኑ ግጥሚዎች ለፍጻሜ  አልፈዋል። ሮጀር ፌደረር የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን ግሩም በሆነ ጨዋታ 7-6,6-2 ሲያሸንፍ በፍጻሜው ለድል ከበቃ በታላቁ ማጠቃለያ ውድድር ለሰባተኛ ጊዜ ነው የሚሆነው። ፌደረር ከአራት ወራት በፊት መሪይን በዊምብልደን ፍጻሜ ሲያሸንፍ የስኮትላንዱ ተወላጅም ከዚያው በተከተለው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ፌደረርን በመርታት ለወርቅ ሜዳሊያ መብቃቱ የሚታወስ ነው።                                                  

ሁለቱ ተጫዋቾች በዘንድሮው የውድድር ወቅት ትናንት ለአራተኛ ጊዜ መገናኘታቸው ነበር። የሮጀር ፌደረር የፍጻሜ ተጋጣሚ ኖቫክ ጆኮቪች ደግሞ የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ሲያሸንፍ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኝነቱን ባለፈው ወር ከሮጀር ፌደረር መልሶ መውሰዱ አይዘነጋም።  የሁለቱ ኮከቦች ፍጻሜ ግጥሚያ ትግል የተመላበት እንደሚሆን ከወዲሁ ሊጠበቅ የሚችል ነው።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 12.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16hOq
 • ቀን 12.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16hOq