ስፖርት፤ ሚያዝያ 7 ቀን፣ 2011 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 15.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ ሚያዝያ 7 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት በማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል መካከል ትንቅንቁ ቀጥሏል። የኹለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከእንግዲህ መሸነፍ የለም ሲሉ ፎክረዋል። ኹለቱም በአሸናፊነታቸው ከቀጠሉ ሊቨርፑል የዓመታት ሕልሙ መክኖ ይቀራል። ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ጨዋታ ከተዘናጋ ነገር ይበላሽበታል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:01

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት በማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል መካከል ትንቅንቁ ቀጥሏል። የኹለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከእንግዲህ መሸነፍ የለም ሲሉ ፎክረዋል። ኹለቱም በአሸናፊነታቸው ከቀጠሉ ሊቨርፑል የዓመታት ሕልሙ መክኖ ይቀራል። ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ጨዋታ ከተዘናጋ ነገር ይበላሽበታል።  በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ፦ ባሕር ዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድን መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ደጋፊዎች እጅግ ሰላማዊ የኾነ ድጋፍ አሳይተዋል። የደጋፊዎችን ኹኔታ በተመለከተ ቃለ መጠይቅ አድርገናል። የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን እግር ኳስ ቡድን አመራር አዲስ አበባ ገብተዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን አትሌት በፓሪስ ጎዳናዎች ደምቀው አምሽተዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለዋንጫ ሽሚያ የሚደረገው ፉክክር ተጠናክሮ ቀጥሏል።  ትናንት ሊቨርፑል ቸልሲን 2 ለ 0 ድል በማድረግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር  ሲቲን በኹለት  ነጥብ በልጦ መሪነቱን ለጊዜው አስጠብቋል። በትናንቱ ጨዋታ የሊቨርፑል 2ኛ ግብ ግብጻዊው ሞሀመድ ሳላኅ  ድንቅ ብቃቱን ያስቆጠረበት ናት። ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 1 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ በቀጣይ ነጥብ ላለመጣል የሞት ሽረት ፍልሚያ ማድረጉ አይቀርም።

ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያከናውነው የፊታችን ቅዳሜ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ነው። 67 ነጥብ ያለው ቶትንሀም ሆትስፐርን ማንቸስተር ሲቲ 83 ነጥብ ይዞ ቢርቀውም በደረጃ ሰንጠረዡ ለሦስተኛነት ነው የሚፋለመው። እንደ ማንቸስተር ሲቲ ኹሉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቶትንሀም በአንድ ነጥብ የሚከተለው ቸልሲን በአስተማማኝ ነጥብ ለመራቅ ከባድ ፍልሚያ ማድረጉ አይቀርም። ትናንት በሊቨርፑል የተሸነፈው ቸልሲ 66 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ካርዲፍ ሲቲ፤ ፉልሀም እና ሁደርስፌልድ እንደየቅደም ተከተላቸው ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ ውስጥ ይገኛሉ። ሊቨርፑል ቀጣይ አራት ቀሪ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው ከእነዚህ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ከሚገኙት ካርዲፍ ሲቲ እና ሁደርስፌልድ እንዲሁም ኒውካስል እና ዎልቭስ  ጋር ነው። በአንጻሩ ማንቸስተር ሲቲ በደረጃው ሦስተኛ እና አምስተኛ ከኾኑት ቶትንሀም እና ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እንዲሁም ላይስተር ሲቲ ብራይተን እና በርንሌይ ጋር ይጫወታል። ያም በመኾኑ ምናልባት እድሉ ለሊቨርፑል የሰፋ ይመስላል።

የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን ትናንት ፎርቱና ዱይስልዶርፍን 4 ለ1 በኾነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ በቡንደስሊጋው መሪነቱን ዳግም ተረክቧል።  ዶርትሙንድ ማይንንትስን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 ማሸነፍ ቢችልም በባየር ሙይንሽን በአንድ ነጥብ ከመበለጥ አልዳነም። ባለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ባየር ሙይንሽን በአንድ ጨዋታ ነጥብ ሲጋራ ተቀናቃኙ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ጨዋታ ነጥብ መጣሉ እንዲበለጥ አድርጎታል። ባየር ሙይንሽን  የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው 67 ነጥብ ይዞ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ66 እንዲሁም ላይፕሲሽ በ58 ነጥብ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ኾነው ይከተላሉ።  

የባየር ሙይንሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀርመናዊው ካርል ሄይንትስ ሩሜኒገን ጨምሮ የቡድኑ አባላት አዲስ አበባ  ስታዲየም የፊታችን ረቡዕ ይገኛሉ። እዚያም የኢትዮጵያ ታዳጊ እግር ኳስ ተጨዋቾችን የሚመለከቱ መኾኑ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው የባየርን  የእግር ኳስ ትምህርት ቤትንም  በኢትዮጵያ በይፋ እንደሚከፍቱ የጀርመን ኤምባሲ በፌቡክ ገጹ በእንግሊዝኛ አትቷል።

ከባየርን ሙይንሽን  የእግር ኳስ ትምህርት ቤት ከኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  እና ከባየርን ሙይንሽን ከፍተኛ አመራር  በተገኙበት ትምህርት ቤቱ ይመረቃል ተብሏል። ረቡዕ እለት ከጠዋቱ ሦስት ሰአት ተኩል በሚጀምረው ውድድር 8 የኢትዮጵያ ወጣት ቡድኖች ጨዋታ ያከናውናሉ። ቡድኖቹም፦ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ቡና፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፤ መዲና፣ መከላከያ፤ ሰላም እንዲሁም የሰውነት እግር ኳስ ትምህርት ቤት እና የኢትዮ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መኾናቸውን ኤምባሲው አክሏል።

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ደግሞ መሪው መቀሌ 70 እንደርታ ትናንት ባሕር ዳር ከተማ ስታዲየም ውስጥ በባሕር ዳር ከነማ 1 ለ0 ተሸንፏል። ውድድሩ የተከናወነው በርካታ ደጋፊዎች በተገኙበት ሲኾን ስፖርታዊ ጨዋነት ታይቷል። የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ የደጋፊዎቹን ኹኔታ «አስገራሚ የድጋፍ ድባብ» ሲል ገልጦታል።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ዛሬ ከሰአት በዩናይትድ ስቴትስ ቦስተን ከተማ በተከናወነው የቦስተን ማራቶን የሩጫ ውድድር አሸነፈች ።  ወርቅነሽ በውድድሩ አንደኛ ለመውጣት የፈጀባት ጊዜ 2 ሰአት ከ23 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ነው። ወርቅነሽ በዚህ ውድድር ስታሸንፍ ስምንተኛዋ ኢትዮጵያዊት ኾና ተመዝግባለች።

ትናንት በፈረንሳይ መዲና በተካሄደው የፓሪስ ማራቶን ኢትዮጵያውኑ አትሌቶች ገለቴ ቡርቃ እና አብርሃ መላው በወንዶች እና በሴቶች ምድብ ድል ተጎናጽፈዋል። በተለይ ኢትዮጵያውያቱ ተፎካካሪዎች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ቦታ በመቆጣጠር ደምቀው ታይተዋል።  ኹለቱ የሀገሯ ልጆችን አስከትላ ለድልየበቃችው አትሌት ገለቴ ቡርቃ የማራቶን ሩጫው ድሉን መጋቢት 1 ቀን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች መታሰቢያ ማዋሏን ለዶይቸ ቬለ ተናግራለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic