ስፖርት፤ ሚያዝያ 3 ቀን፤ 2008 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 11.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት፤ ሚያዝያ 3 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ጠንከር ያለ ፈተና ገጥሞታል። ፌዴሬሽኑ በጥቂት ወራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን መርምሮ ውጤቱን ካላሳወቀ የሚጠብቀው ቅጣት የከፋ ነው። ሊቨርፑል ስቶክ ሲቲን ትናንት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል። አርሰናል ነጥብ ሲጥል፤ ቸልሲ ተሸንፏል፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ግን የገጠመው አስደንጋጭ ሽንፈት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:50

የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ላይ ምርመራ አድርጋ እንድታሳውቅ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ቀነ ገደብ ተጥቷታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የምርመራ ውጤቱን በቀነ ገደቡ መሠረት ማቅረብ ካልቻለ ለዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ ማለትም ዋዳ ደንብ ባለመገዛት በሚል ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ስቶክ ሲቲን ትናንት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል። ሌስተር ሲቲም ትናንት አሸንፏል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከታችኛው ዲቪዚዮን /ምድብ/ ያደጉት ዳርምሽታድት እና ኢንግሎሽታድት ድል ቀንቷቸዋል። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ በሰፋ ልዩነት ሲያሸነፍ፤ መሪው ባርሴሎና እጅ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ቁጥራቸው እስከ 200 የሚደርሱ አትሌቶቿ ላይ ፈጣን ምርመራ እንድታከናውን ግዳጅ ተጥሎባታል። የምርመራ ቀነ-ገደቡ ካለፈ የሀገሪቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚጠብቀው ቅጣት ከበድ ያለ ነው።

ይህ ክስተት የአትሌቲክሱ ዘርፍ ላይ ጥላ ቢያጠላም ትናንትና በሁለት የአውሮጳ ከተሞች በተከናወኑ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በሁለቱም ድል ቀንቷቸዋል።

በሮተርዳሙ የማራቶን ሩጫ ለተብርሃን ገብረሥላሴ በ2:26.15. አንደኛ ስትወጣ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሱቱሜ ከበደ በሁለተኛነት አጠናቃለች።

በቪየናው ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሹኮ ገኔሞ አንደኛ ሆናለች። የገባችበት ሰአት 2:24:31 ነው። ሩት አጋ ተከትላት በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች። በሁለቱም ውድድር በወንዶቹ ፉክክር ኬንያውያን አሸናፊ ሆነዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ስቶክ ሲቲን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ነጥቡን 48 አድርሷል። ደረጃውንም ወደ ስምንተኛነት አሻሽሏል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቸልሲ ቅዳሜ እለት በስዋንሲ ሲቲ አንድ ለባዶ ተሸንፏል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል በበኩሉ 59 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከዌስትሐም ዩናይትድ ጋር 3 ለ3 በመለያየት ነጥብ በመጋራቱ ከመሪው ሌስተር ሲቲ ጋር የነበረውን የነጥብ ልዩነት በ13 ርቋል። ሌስተር ሲቲ ትናንት ሰንደርላንድን 2 ለ0 አሸንፎ በ72 ነጥብ የመሪነት ግስጋሴውን ቀጥሏል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በቶትንሀም 3 ለ0 ተረትቶ በ53 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተወስኗል። ከፊቱ እንደሚገኘው እንደ ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ዌስት ብሮሚችን 2 ለ1 ድል ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ በ57 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቶትንሀም በ65 ነጥቡ ደረጃው ሁለተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዳርምሽታድት ሐምቡርግን 2 ለ1 በማሸነፍ ኢንግሎሽታድት ደግሞ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 1 ለ0 በመርታት በቡንደስ ሊጋው በሚቀጥለው የውድድር ዘመንም የመዝለቅ ጥንካሬያቸውን አሳይተዋል። ከትናንት በስትያ ሽቱትጋርትን 3 ለ1 የረታው ባየር ሙይንሽን ቡንደስሊጋውን በ75 ነጥብ እየመራ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ68 ይከተላል። ትናንት ከሻልከ ጋር 2 ለ2 ነጥብ ተጋርቷል።በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ አይበርን ቅዳሜ እለት 4 ለ0 በማንኮታኮት ከመሪው ባርሴሎና ጋር የነጥብ ልዩነቱን ወደ 4 አድርሶታል ከአትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ በ1 ነጥብ ነው የሚበለጠው። 76 ነጥብ ያለው ባርሴሎና ለሪያል ሶሴዳድ 1 ለምንም በመሸነፍ እጅ ሰጥቷል። አትሌቲኮ ማድሪድ ኢስፓኞላን 3 ለ1 አሸንፏል።

የሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ውድድር በነገው እለት ይከናወናል። የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ ቮልፍስቡርግ ጋር ይጋጠማል። ባለፈው ሣምንት በተከናወነው የመጀመሪያው ጨዋታ ቮልፍስቡርግ በሜዳው ሪያል ማድሪድን 2 ለ0 ጉድ አድርጎታል። ሁለት እኩል የተለያዩት የፈረንሣዩ ፓሪስ ሳንጀርሜን እና የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲም ሁለተኛ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት በነገው ዕለት ምሽት ላይ ነው። ከነገ በስትያ ረቡዕ ደግሞ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ ሊስቦንን ይገጥማል። ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ባየርን ቤኔፊካን በጠበበ ልዩነት አንድ ለባዶ ነበር ያሸነፈው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ


Audios and videos on the topic