ስፖርት፣ ሚያዝያ 24፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 02.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት፣ ሚያዝያ 24፣ 2008 ዓ.ም

ዛሬ በአየርላንድ በተካሄደው የቤልፋስት ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ብርሐን ገብረ ሚካዔል አሸፈች።ለዋንጫ የተቃረቡት የእንግሊዙ ሌስተር ሲቲ እና የጀርመኑ ባየር ሙንሽን በሳምንቱ መገባደጃ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በአቻ አጠናቀው እጣ ፈንታቸውን እየተጠባበቁ ነው። ስፔን ላይ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ አንገት ላንገት ተያይዘዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:17
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:17 ደቂቃ

ስፖርት፣ ሚያዝያ 24፣ 2008 ዓ.ም

ዛሬ በተካሄደው የቤልፋስት ማራቶን በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያዊቷ ብርሐን ገብረ ሚካዔል አሸፈች። ብርሐን ውድድሩን በ2:48.26 ቀዳሚ ሆና ስትጨርስ ሰሜን አየርላንዳዊቷ ላውራ ግርሐም ሁለተኛ እንዲሁም የቼክ ሪፐብሊኳ ራድካ ቹራኖቫ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
የ29 አመቷ ብርሐን ውድድሩን ባለፈው ዓመት ያሸነፈች ሲሆን በዛሬው ውድድርም ከፍተኛ የአሸናፊነት ቅድመ-ግምት ተሰጥቷት ነበር። ከዚህ ቀደም በህንድ (2.39.11.) ቤልፋስት (2.40.57) እና በስፔን (2.36.31.) የማራቶን ውድድሮች ያሸነፈችው ብርሐን በዛሬው ዕለት 42 ኪ.ሜትሩን በጥንካሬ ስትመራ ነበር።
በወንዶቹ ጎራ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ጆዔል ኪፕሳንግ ውድድሩን በ2.17.39. በሆነ ሰዓት ሲጨርስ ያገሩ ልጆች ኤሪክ ኮኤች እና ዳን ታኑይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነዋል።
በፎርሙላ አንድ የሩሲያ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ አሸናፊ ሆኗል። ኒኮ ሮዝበርግ ውድድሩን በተከታታይ ለሰባተኛ ጊዜ በማሸነፍ ከማይክል ሹማኸር ጋር ተስተካክሏል። በሩሲያዋ የሶቹ ከተማ በተካሄደው ውድድር ኒኮ ሮዝበርግ ከሌላው የሜርሴዲስ ቡድን አጋሩ ብሪታንያዊዉ ሊዊስ ሐሚልተን በ12 ሰከንድ ቀድሞ ገብቷል። የፈራሪ ተወዳዳሪው ኪሚ ራይኮነን በሶስተኛነት ሲያጠናቅቅ እድለ ቢሱ ሴባስቲያን ፌትል ሁለት ጊዜ ከበስተኋላው ተገጭቶ ውድድሩን ገና ከጅማሮው ለማቋረጥ ተገዷል።


ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ አራት ተከታታይ ውድድሮችን ያሸነፈው ኒኮ ሮዝበርግ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው የቡድን አጋሩ ሊዊስ ሐሚልተንን በ43 ነጥብ ይመራል።በትናንትናው ውድድር ሊዊስ ሐሚልተን ተደጋጋሚ የቴክኒክ እክሎች ገጥመውታል።የሳምንቱ መገባደጃ ውድድር ለኒኮ ሮዝበርግ አስደናቂ ሆኖለታል።ኒኮ ሮዝበርግ በግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ከጣልያናዊው አልቤርቶ አስካሪ፤ጀርመናውያኑ ማይክል ሹማኸር እና ሴባስቲያን ፌትል ጋር ተስተካክሏል።
አስደናቂው ሌስተር ሲቲ በ132 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከፍ ሊያደርግ ተቃርቧል። በናጠጡ ቱጃሮች የገንዘብ ድጋፍ ጥቂት ክለቦች ብቻ በነገሱበት ውድድር ሌስተር ሲቲ እና አሰልጣኙ ክላውዲዮ ራኔሪ የሰሩት ታሪክ ለእግር ኳስ ተንታኞች፤ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆን ለክለቡ ደጋፊዎችም የሚታመን አይደለም።
ትናንት ከማንችስተር ዩናይትድ የተጫወተው ሌስተር ሲቲ አሸንፎ ቢሆን ኖሮ ከፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሙን ባስጻፈ ነበር። በኦልትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው የ36ኛ ሳምንት ጨዋታ ፈረንሳዊው አንቶኒ ማርሻል በስምንተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ ቢሆንም የሌስተር ሲቲው አምበል ዌስ ሞርገን በ17ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ጎል አስቆጥሯል። በ86ኛው ደቂቃ ዳኒ ድሪንክዋተር በቀይ ካርድ ሲወገድ ምሽቱ ለሌስተር የከፋ መስሎ ነበር። የማንችስተር ተጫዋቾች ዳኒ ድሪንክዋተር ሆላንዳዊውን ሜምፌስ ዴፔይን ጎትቶ ሲጥል የፍጹም ቅጣት ምት ሊሰጠን ይገባል ብለው ቢወተውቱም አሰልጣኙ አልተቀበሏቸውም። አስደናቂ የቡድን ጥንካሬን የተላበሱት ሌስተሮች ዛሬ ምሽት የዋንጫ ተፎካካሪያቸው ቶተንሐም ከሌላው የለንደን ቡድን ቼልሲ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በጉጉት የሚጠብቁት ነው። በምሽቱ ጨዋታ ቶተንሐም ከተሸነፈ ሌስተሮች በውድድሩ ሁለት ጨዋታ እየቀራቸው ዋንጫውን ከፍ የሚያደርጉ ይሆናል።ለእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንግዳ ባይሆኑም ለዋንጫ ክብር በቅተው የማያውቁት ጣልያናዊው ክላውዲዮ ራኔሪ በሚቀጥለው ዓመት በቻምፒየንስ መሳተፋቸው ታላቅ ስኬት ሆኖላቸዋል።


ከዚህ ቀደም ቼልሲን ያሰለጠኑት ክላውዲዮ ራኔሪ ሌስተር ሲቲ ዋንኛ ዓላማ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ መታደግ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ያ ቀርቷል። ደጋፊዎቻቸውም «ዋንጫውን እናሸንፋለን» እያሉ ሲዘምሩ ይደመጣል።
«አስደናቂ የውድድር ዘመን ነው። ክለቡን ለመታደግ ነበር ዋንኛ ዓላማችን። ነገር ግን እዚህ ደርሰናል። እስከ መጨረሻው ድረስን መፋለም እንፈልጋለን።»
በዕለተ ቅዳሜ በደጋፊቻቸው ተቃውሞ የገጠማቸው አርሰን ቬንገር በተጋጣሚያቸው ኖርዊች ሲቲ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አንድ ለባዶ አሸንፈዋል። የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ፉክክሩን ለሌስተር ሲቲ እና ቶተንሐም የተውት አርሰናሎች ተዳክመው በታዩበት ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር የተነሳው ዳኒ ዌልቤክ በ59ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎብ አንድ ለምንም አሸንፈዋል።
ትናንት ምሽት ከሳውዛምፕተን የተጫወተው ማንችስተር ሲቲ 4ለ2 ተሸንፏል። ሴኔጋላዊው ሳይዶ ማኖ አስደናቂ ሆኖ በታየበት ጨዋታ ሶስት ግቦችን ሲያሳርፍ ቀሪዋን ሼን ሎንግ አስቆጥሯል። በቻምፒንስ ሊግ የግምሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከሪያል ማድሪድ ጋር የተደለደለው ማንችስተር ሲቲ በ19 ዓመቱ ናይጄሪያዊ ኬሌቺ ኢህናቾ ሁለት ግቦች ቢያገኝም ጨዋታውን የሚያሸንፍበት ስልት ጠፍቶት ተስተውሏል።
ሊቨርፑል እና ጀርመናዊ የርገን ክሎፕ ወደ ዌልስ ተጉዘው ሶስት ገብቶባቸው ተመልሰዋል። ጋናዊው አንድሪው አየው ሁለት እንዲሁም ጃክ ኮርክ ለስዋንሲ ሶስቱን ግቦች ከመረብ ሲያሳርፉ ሊቨርፑሎች በክርቲያን ቤንቴኬ አንድ ማስተዛዘኛ አግኝተዋል።
በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቶተንሐም ዛሬ ምሽት ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለቼልሲ የሚፈይደው ነገር ባይኖርም በጉጉት ይጠበቃል። የጨዋታው ውጤት ምን አልባትም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እጣፈንታ ይወስን ይሆናል። በፕሪምየር ሊጉ ሌስተር ሲቲ በ77 ነጥቦች ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቶተንሐም በ69፤አርሰናል በ67 እንዲሁም ማንችስተር ሲቲ በ64 ከሁለት እስከ አራት ተቀምጠዋል።


በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርሙንሽን እና አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። በሜዳው አሊያንዝ አሬና ቦሩሺያ ሞንቼግላድባሽን ያስተናገደው ሙንሽን በስድስተኛው ደቂቃ ቶማስ ሙለር ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ ሆኖ ለአራተኛ ተከታታይ ጌዜ ዋንጫውን ያነሳ መስሎ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ቦሩሺያ ዶርትሙንድ በሰባት ነጥብ ልዩነት ላይ የሚገኘው ሙንሽን ምሽቱ እንደ እቅዱ አልሰመረለትም። በሁለተኛው አጋማሽ 72ኛው ደቂቃ የ25 ዓመቱ አንድሬ ሐን ያስቀጠራት ግብ ጨዋታው በአቻ እንዲጠናቀቅ ባየር ሙንሽን እና ደጋፊዎቹም ፈንጠዝያቸውን እንዲያቆዩት አስገድዳለች።
ሺንጂ ካጋዋ፤አድሪያን ራሞስ፤ማርኮ ሬውስ እና ፒሬ ኤምሪክ ኦውባሜያንግ ግብ ባስቆጠሩበት የዕለተ-ቅዳሜ ጨዋታ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ ዎልፍስበርግን አምስት ለአንድ አሸንፏል። አንድሪያ ሹርለ ለዎልፍስበርግ ማስተዛዘኛ ባስቆጠረበት ምሽት ኦውባሜያንግ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በሚቀጥለው አመት በአውሮጳ ሊጎች መሳተፍ የማይችለው ዎልፍስበርግ የድንቅ ክህሎት ባለቤት የሆኑ ወጣት ተጨዋቾቹን ለማቆየት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።


በዓመቱ መገባደጃ የቀድሞ ክለቡን ባየር ሙኒክን መቀላቀል እንደሚፈልግ ያስታወቀው ተከላካዩ ማትስ ሑምልስ በጨዋታው በዶርትሙንድ ደጋፊዎች ተቃውሞ ገጥሞታል። ዶርትሙንድን በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም የተቀላቀለው ሑሜልስ ግን እንዲህ በቀላሉ ሐሳቡ የሚሳካ አይመስልም። ተጫዋቹ በሚቀጥለው ዓመት ለባየር ሙኒክ መጫወት እንደሚፈልግ ይግለጥ እንጂ የዶርትሙንድ ኃላፊ ሐንስ-ዮዓኪም ቫትዘ በርካሽ ዋጋ እንደማይሸጥ አስታውቀዋል።
በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ የሚገኘው ሐኖቨር 96 በዕለተ-እሁድ ማለዳ የ19 አመት ወጣት አጥቂውን በመኪና አደጋ አጥቷል። ወጣቱ አጥቂ ኒክላስ ፋየርቤንድ የሚጓዝበት መኪና መንገድ ስቶ በመገልበጡ በተከሰተው አደጋ ህይወቱ አልፏል።
በቡንደስሊጋው ባየር ሙንሽን በ82 ነጥቦች ቀዳሚውን ደረጃ ተቆናጥጧል። ቦሩሺያ ዶርትሙንድ በ77፤ባየር ሊቨርኩዘን በ57 እንዲሁም ቦሩሲያ መንሼንግላድባህ በ49 ነጥቦች ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በስፔን ፕሪሜር የዋንጫው መድረሻ አሁንም አልለየለትም። ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ በእኩል 85 ነጥቦች አንገት ላንገት ተናንቀዋል። ሪያል ማድሪድም ቢሆን በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በ84 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በግብ ክፍያ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው ባርሴሎና እጅግ ተዳክሞ በታየበት ዕለተ ቅዳሜ ከሪያል ቤቲስ ተጫውቶ ሁለት ለምንም አሸንፏል። ሉዊስ ሱዋሬዝ እና ራኪች ግቦቹን አስቆጥረው ጨዋታውን ያሸንፉ እንጂ ባርሴሎና ዘገምተኛ ሆኖ ታይቷል።


አትሌቲኮ ማድሪድ እና አጥቂው አንቶኒዮ ግሪዝማን አስደናቂ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። ከባርሴሎና በፊት የተጫወተው አትሌቲኮ ማድሪድ በ55ኛው ደቂቃ ፈረንሳዊው አንቶኒዮ ግሪዝማን ባስቆጠራት ግብ ራዮ ቫልካኖን አንድ ለምንም አሸንፏል። በላሊጋው የበላይ ሆኖ የመጨረስ ተስፋው በባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ሽንፈቶች ላይ የተመሰረተው ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ሪያል ሶሲዳድን አንድ ለባዶ አሸንፏል። ግቧን ያቆጠረው ዌልሳዊው ጋሬዝ ቤል ነበር።

በሚቀጥሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት (ማክሰኞና ረቡዕ) አጓጊው የአውሮጳ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍጥጫ ምላሽ ያገኛል። ባለፈው ሳምንት ወደ ስፔን ተጉዞ አንድ ለምንም የተሸነፈው ባየር ሙንሽን በሜዳው ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይጫወታል። በዕለቱ ይዘውት በገቡት ታክቲክ በጀርመን መገናኛ ብዙኃን ክፍኛ የተብጠለጠሉት ፔፕ ጋርዲዮላ አንቶኒዮ ግሪዝማንን እና በሙሉ መንፈስ እና አስደናቂ የቡድን ስሜት የሚጫወቱ አትሌቲኮ ማድሪዶችን ለማሸነፍ ጫና በርትቶባቸዋል። የእግር ኳስ ተንታኞች የሚጠቅሷቸው ቁጥሮች ግን ለጋርዲዮላም ይሁን የሙንሽን ደጋፊዎች መርዶ ነጋሪ ይመስላሉ። በቻምፒዮንስ ሊግ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ተጋጣሚያቸውን በሜዳቸው 1-0 ካሸነፉ መካከል 69% ወደ ሚቀጥለው ዙር አልፈዋል።
ረቡዕ ሪያል ማድሪድ በሜዳው ከማችስተር ሲቲ ይጫወታል። ባለፈው ሳምንት ማችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሐድ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ታይቷል። ከመሸነፍ የዳነውም በግብ ጠባቂው ጆ ኸርት ድንቅ ብቃት ነበር። በሳንቲያጎ በርናባውረቡዕ ምሽት በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ጉዳት ላይ የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሜዳው ይመለሳል። በፕሪምየር ሊጉ ያልተሳካላቸው እና በመጪው ዓመት በስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚተኩት ፔሌግሪኒ ስንብታቸውን ለማሳመር በበርናባው አንዳች ተዓምር ከተጫዋቾቻቸው መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

እሸቴ በቀለ


አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic