ስፖርት፦ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2010 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 30.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፦ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በገቡበት የትናንቱ የሐምቡርግ ማራቶን ለአምስት ዓመታት በኬንያውያን የተያዘው ክብር ወሰን ለጥቂት ሳይሰበር ቀርቷል። በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን እና ሪያል ማድሪድ የመልስ ግጥሚያቸውን ነገ ማታ ያከናውናሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:12

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት በበላይነት አጠናቀዋል። በውድድሩ (02:06:34) በመሮጥ አንደኛ የወጣው ሰለሞን ደቅሲሳ አንድ ደቂቃ ከ4 ሰከንድ በመዘግየቱ ክብር ወሰን መስበር ሳይሳካለት ቀርቷል። የሐምቡርግ ማራቶን ክብር ወሰን በለንደን ማራቶን ባለድሉ ኤሊዩድ ኪፕቾጌ የተያዘው የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ነው። በሐምቡርጉ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ታዱ አባተ እና አየለ አብሽሮ (2:06:54) እና (2:07:19) ሮጠው በመግባት ውድድሩን ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመኾን አጠናቀዋል። 

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 በለንደን ማራቶን አሸናፊ የነበረው ዩጋንዳዊው ስቴፈን ኪፕሮቲች ኬኒያዊው ሯጭ ሶሎሞን ዬጎን ተከትሎ አምስተኛ ወጥቷል። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ለባሕሬን የምትሮጠው ሽታዬ እሸቴ (2 24 51) በመሮጥ አሸናፊ ኾናለች።

በውድድሩ በአንደኛነት አሸናፊ የኾነው ኢትዮጵያዊው ሯጭ ሰለሞን ደቅሲሳ፦ «በማሸነፌ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል» ሲል ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግሯል። ያሸነፈበት ሰአትም በሐምቡርግ ማራቶን ታሪክ ሦስተኛው ፈጣኑ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦለታል።ሰለሞን በውድድሩ አሸናፊ በመኾኑ 44 ሺህ ዶላር ሽልማት ማግኘቱም ተዘግቧል።

ከሰለሞን በ7 ደቂቃ ከ5 ሰከንድ ዘግይቶ ሩጫውን ያጠናቀቀው ብቸኛው ጀርመናዊ ሯጭ ፊሊፕ ፕፍሊገር በበኩሉ ለገንዘብ ሽልማት ባይበቃም የውድድሩ ማብቂያ መስመር ላይ ሲደርስ ከጓደኛው የመሳም ሽልማት አግኝቷል። ፊሊፕ (02:13:39) በማጠናቀቁ በርሊን ውስጥ ለሚከናወነው የአውሮጳ ውድድር ማለፍ ችሏል።

በትናንቱ የማራቶን ሩጫ እኩለ ቀን ላይ በአንድ ሰአት ልዩነት ሁለት ተሳታፊዎች መተንፈስ አቅቷቸው የመጀመሪያ ርዳታ ተደርጎላቸዋል ሐኪም ቤት ተወስደዋል። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ዛሬ ማታ ቶትንሀም ከዋትፎርድ ጋር ይጋጠማል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም በገዛ ጥፋቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን አሰልጣኙ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ተናግረዋል። ቶትንሀም በፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ኾኖ በመጨረስ የሚቀጥለው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ተሳታፊ ለመኾን እጅግ ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ ይገኛል። 36 ጨዋታዎችን አከናውኖ 72 ነጥብ ከሰበሰበው ሊቨርፑል  ቶትንሀም በአራት ነጥብ ይበለጣል፤ 34 ጨዋታዎችን ነው ያደረገው።

ቶትንሀም በፕሬሚየር ሊጉ የቅርብ ሳምንታት ውጤት መሰረትም መዋዠቅ ታይቶበታል። ለስምንት ጊዜያት አሸናፊ ከኾነበት የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ግምሻ ፍጻሜም በማንቸስተር ዩናይትድ የተሸነፈው ባለፈው ሳምንት ነው።

በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 77 ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ይበልጣል። ማንቸስተር ዩናይትድ በኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ትናንት አርሰናልን ድል ባደረገበት ወቅት የተጎዳው ሮሜሉ ሉካኩ ለፍጻሜው እንደማይደርስ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኞ ተናግረዋል።

ከቸልሲ በ9 ነጥብ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በበኩሉ በሚቀጥለው ዙር የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊ ለመኾን አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል። 54 ነጥብ ይዞ የሚከተለው በርንሌይ ከአርሰናል በሦስት ነጥብ ብቻ ነው የሚበለጠው። በእርግጥ አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም ማለት ነው።  

እያንዳንዳቸው በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡት ሳውዝሀምፕተን፣ ስቶክ ሲቲ እና ዌስት ብሮሚች በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ከ18ኛ እስከ 20ኛ ተደርድረዋል። የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ዌስት ብሮሚች በፕሬሚየር ሊጉ በዘንድሮ ውድድር ማግኘት የቻለው 28 ነጥብ ብቻ ነው። በዚህም መሰረት ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ የ65 ነጥብ ልዩነት አለው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቬርደር ብሬመን ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር ትናንት አንድ እኩል ተለያይቷል። 55 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቬርደር ብሬመንን በ17 ነጥብ ይበልጣል።  ዶርትሙንድ በትናንቱ ድል በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አስፍቷል። በተለይ የ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ማሪዮ ጎይትሰ አቋም መስተካከል ቡድኑን ብቻ ሳይኾን የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮአሒም ሎይቭን አስደስቷል።  ማሪዮ ጎይትሰ በትናንቱ ግጥሚያ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ችሏል። አቋሙ እጅግ እየተሻሻለ በመምጣቱም የዛሬ 15 ቀን ይፋ በሚኾነው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተሰላፊዎች ስም ዝርዝር ጊዜያዊ መዝገብ ላይ የመስፈር ዕድሉን አስፍቷል።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ቤቲስ 20 ነጥብ ይዞ የመጨረሻ 20ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማላጋ ጋር ዛሬ ማታ ይጋጠማል። ሊዮኔል ሜሲ ሔትሪክ በሠራበት ግጥሚያ መሪው ባርሴሎና ትናንት ዴፖርቲቮ ላኮሩኛን 4 ለ 2 አሸንፏል። ቀዳሚዋን ግብ ለባርሴሎና በ7ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ኮቲንሆ ነው። ሊዮኔል ሜሲ በትናንቱ ጨዋታ ኳስ ለባላጋራው አቀብሎ ተከላካዮች ባልጠበቁት ኹኔታ እያፈተለከ ከመሀከላቸው በመውጣት  እጅግ ልዩ ብቃቱን አሳይቶ  ነው ግቦቹን ያስቆጠረው። የሊዮኔል ሜሲን ልዩ ብቃት የታዘቡ አድናቂዎች «ሜሲ ለአርጀንቲናም በዓለም ዋንጫ እንዲህ ይጫወት ይኾን?» ሲሉ ጠይቀዋል። «የለም ለባርሴሎና ብቻ ነው» ሲሉ የመለሱ በርካቶች ናቸው። በኮላክ እና ሉቃስ ግቦች በዜሮ ከመሸነፍ የዳነው ዴፖርቲቮ በላሊጋው 18ኛ ወራጅ ቃጣና ላይ ይገኛል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

ቅዳሜ እለት ሌጋኔስን 2 ለ1 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ እያሟሟቀ ነው።  የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ነገ እና ከነገ በስትያ ምሽት ላይ ይከናወናል። በነገው ግጥሚያ የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን የስፔኑ ሪያል ማድሪድን  በሜዳው ይገጥማል። አሪየን ሮበንን ጨምሮ አምስት ወሳኝ ተጨዋቾቹ ግን  አይሰለፉም። አሪየን ሮበን ሪያል ማድሪድ 2 ለ1 ባሸነፈበት ያለፈው ጨዋታ የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ስለደረሰበት እዚያው ባየር ሙይንሽን ከተማ ውስጥ ቆይቶ ነው የመልስ ጨዋታውን የሚከታተለው ተብሏል።

ቀደም ሲል የእግር መርገጫ አማካዩ ላይ ስብራት የደረሰበት ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር ብዙ ልምምድ ላይ ስላልተገኘ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ኾኗል። የመሀል ተከላካዩ ጄሮም ቦዋቴንግ በባለፈው የማድሪድ ግጥሚያ የጡንቻ መሰንጠቅ ስለደረሰበት እሱም እንደማይሰለፍ ተገልጧል።  የጉልበት ቀዶ ጥገና የተደረገለት አርቱሮ ቪዳል እና የቋንጃ መጋጠሚያ ወለምታ የደረሰበት ኪንግስሌ ኮማንም ከማይሰለፉት መካከል ተመድበዋል። በአንጻሩ ዳቪድ አላባ እና ዣቪ ማርቲኔዝ ለግማሽ ፍጻሜው የመልስ ግጥሚያ መድረሳቸው ታውቋል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ሌላ ግጥሚያ ባለፈው ሳምንት አንፊልድ ሜዳው ላይ ሮማን 5 ለ2 ያሸነፈው ሊቨርፑል ረቡዕ ማታ የመልስ ጨዋታውን ያከናውናል። በዚህ ጨዋታ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ያለ ረዳታቸው ነው የሚያቀኑት። ረዳት አሰልጣኝ ዜልጅኮ ቡቫች በሊቨርፑል ቡድን የዘንድሮ የውድድር ዘመን እስኪያበቃ ድረስ አብረው እንደሚቆዩ ግን ተነግሯል። በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያ ላይ የማይገኙትም በግል ምክንያት እንደኾነ ተጠቅሷል። የ56 ዓመቱ ዜልጆክ ቡቫች ላለፉት 17 ዓመታት ዬርገን ክሎፕን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ በረዳት አሰልጣኝነት አገልግለዋል። ዩሮ ስፖርት ቢቢሲን ጠቅሶ ዛሬ እንደዘገበው ከኾነ በአሠልጣኙ እና ረዳት አሠልጣኙ መካከል የአመለካከት ልዩነት በመፈጠሩ ነው የረዥም ዘመን አብሮ ቆይታቸው የሚያበቃው። 

ዬርገን ክሎፕ እና ረዳታቸው ዜልጆክ ቡቫች የዛሬ 28 ዓመት ግድም ማለትም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990ዎቹ ማይንትስ ቡድን ውስጥ አብረው ተሰልፈው ተጫውተዋል። ዬርገን ክሎፕ ከ17 ዓመት በፊት የማይንትስ ቡድንን በአሰልጣኝነት ሲረከቡም ዜልጆክ ቡቫች ምክትላቸው በመኾን ዳግም ተገናኝተዋል። ዬርገን ክሎፕ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡድንን ከ2008 እስከ 2015 ድረስ ባሰለጠኑበት ዘመንም ምክትላቸው አብረዋቸው ነበር።

የመኪና ሽቅድምድም

በትናንቱ የአዘርባጃን ፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አንደኛ የወጣው ሌዊስ ሐሚልተን የፌራሪ አሽከርካሪ ሠባስቲያን ቬትል ትክክል አልሠራም ሲል ቅሬታውን አቀረበ። የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ቅሬታ ያሰማው በውድድሩ ወቅት ግጭት ሲፈጠር ለማረጋጋት ወደ ውድድሩ ገብቶ ከፊት የሚመራው ተሽከርካሪ ሲንቀሳቀስ ሠባስቲያን ጋዝ በመስጠት እና ፍሬን በመያዝ እንዳሳሳተው በመግለጥ ነው።

በፎርሙላ አንድ ሕግ መሠረት፦ «አረጋጊ ተሽከርካሪ ከፊት ሲገባ እየሄዱ ፍሬን መያዝ አይቻልም። ነዳጅ ሰጥተህ መልሰህ ፍሬን መያዝ አይፈቀድም» ብሏል የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን። ለዚህ ሕግ ተገዢ እንደኾነ የተናገረው ሌዎዊስ፦ «በአውስትራሊያ ውድድር ወቅትም ሠባስቲያን ፍጥነት እየጨመረ ፍሬን ሲይዝ ነበር። እንደውም አንዴ ከኋላ ልወጣበት ነበር። ዛሬም የደገመው ያንኑ ነው» ብሏል።

በትናንቱ ውጤት መሠረት ሌዊስ ሐሚልተን አንደኛ፣ የፌራሪ አሽከርካሪው ኪም ራይከነን ሁለተኛ ሲኾን ሠባስቲያን ቬትል ሠርጂዮ ፔሬዝን ተከትሎ በአራተኛነት አጠናቋል። እስካሁን በተከናወኑ አራት የፎርሙላ አንድ ውድድሮች ድምር ውጤት መሠረት ሌዊስ ሐሚልተን በ70 ነጥብ ይመራል። በአውስትራሊያ እና ባሕሬን ውድድሮች አሸናፊ የነበረው ሠባስቲያን ፌትል በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ኪም ራይከነን 48 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የባለፈው ሦስተኛ ዙር የቻይና ውድር አሸናፊ ዳኒኤል ሪካርዶ ከቫልተሪ ቦታስ ዝቅ ብሎ በአምስተኛነት ይገኛል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic