ስፖርት፤ መጋቢት 3 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.  | ስፖርት | DW | 12.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ መጋቢት 3 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ከሮም አደባባይ እስከ ሩቅ ምሥራቅዋ ጃፓን፤ ከባርሴሎና እስከ ዴን ሐግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ ማሳረጊያ ተፎካካሪዎቻቸውን ልቀው ተገኝተዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሐምቡርግ የግብ ጎተራ ኾኗል። ባርሴሎና ረቡዕ የእንግሊዙ ቸልሲን ይገጥማል። ነገና ከነገ በስትያ የሚከናወኑ ተጨማሪ የሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በጉጉት ይጠበቃሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:13

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከሮም አደባባይ እስከ ሩቅ ምሥራቅዋ ጃፓን፤ ከባርሴሎና እስከ ዴን ሐግ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ ማሳረጊያ ተፎካካሪዎቻቸውን ልቀው ተገኝተዋል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሐምቡርግ የግብ ጎተራ ኾኗል። የግብ አዳኙ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሔትትሪክ በሠራበት ግጥሚያ ሐምቡርግን ጉድ ያደረገው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ነው። ባየርን ሙሉ ትኩረቱን ረቡዕ ቀጠሮ ለተያዘለት የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ አድርጓል። በላሊጋው በድል ጎዳና እየገሰገሰ የሚገኘው ባርሴሎና ከነገ በስትያ የእንግሊዙ ቸልሲን ይገጥማል። ነገ እና ከነገ በስትያ የሚከናወኑ ተጨማሪ የሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በጉጉት ይጠበቃሉ። በፒዮንግ ቻንግ ፓራሊምፒክ የስፖርት ውድድር ዩናይትድ ስቴትስ በሜዳሊያ ብዛት እየመራች ነው።  

አትሌቲክስ 
በሣምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሃገራት በተከናወኑ የማራቶን የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ መኾን ችለዋል። ጣሊያን ሮም ከተማ  ውስጥ ትናንት በተኪያሄደው የሮማ ኦስቲያ ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። ሃፍታምነሽ ተስፋዬ 1:09:02 በመሮጥ አንደኛ ስትወጣ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ደራ ዲዳ ከ19 ሰከንድ በኋላ ሁለተኛ በመውጣት ጨርሳለች። ኬንያዊቷ ሬቤካ ቼሺር 1:11:04 በመሮጥ የሦስተኛ ደረጃን አግኝታለች። ኢትዮጵያውያቱ አትሌት ዓማኔ እና ጀሌላ የ4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።  

ጋለን ሩፕ በአንደኛነት በአጠናቀቀበት የሮማው የወንዶች ፉክክር ኬንያውያን ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃን ተቆጣጥረዋል ።  አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ የብር ሜዳሊያ ባሸነፈበት የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን የሩጫ ፉክክር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ጋለን ሩፕ 44ኛው የሮማ ኦስቲያ ግማሽ ማራቶንን ድል ያደረገው 59:47 ሮጦ በመግባት ነው። ጋለን በአንደኛነት ያሸነፈው ሁለተኛ የወጣው ኬንያዊ አትሌት ሞሰስ ኬማይን በ57 ሰከንድ በመቅደም ነው።

ናጎያ ጃፓን ውስጥ በተደረገው ሌላ የማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መስከረም አሰፋ ኬንያዊቷ ቫላሪ ጀሚልን በመጣስ አንደኛ ወጥታለች። መስከረም የገባችበት የ2:21:45 ሰአት በናጎያ ማራቶን ሦስተኛው ፈጣን ጊዜ ተብሎ ተመዝግቧል።  

ፈታኝ ብርቱ ነፋስ በነበረበት የትናንቱ የባርሴሎና ማራቶን  በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ጸጋዬ በላይነሽ እና ወርቅነሽ ዓለሙ የ2ኛ እና የ3ኛ ደረጃን አግኝተዋል።  በዚህ ውድድር በአንደኛነት የጨረሰችው ኬንያዊቷ ሩት ቼቢቶክ አሸናፊ ኾና የገባችበት ሰአት 2:25:49 ነው። በወንዶቹ ፉክክር ከአንደኛ  እስከ ሦስተኛ ደረጃ የያዙት ኬንያውያን ናቸው። ኢትዮጵያዊው ታሪኩ ክንፉ፤ እንዲሁም መጀመሪያ አካባቢ ከፊት ሲመሩ ከነበሩት ውስጥ የነበረው ፀጋዬ ከበደ እና አበግ ጸዳት ከ4ኛ እስከ 6ና ደረጃ ይዘዋል። ኅሉፍ ጸጋዬ እና ዓለሙ ገመቹም በዚሁ ውድድር8ኛ እና 10ኛ ወጥተዋል።  

ፖርቹጋል ውስጥ በተከናወነው የሊዛቦን ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክርኬንያውያን ሁለተኛ የወጣውን ኤርትራዊ ሯጭ በመሀል አስገብተው ከ1 እስከ 4 ያላ,ውን ደረጃ ተቆጣጥረዋል። በዚህ ውድድር ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው የኤርትራው ሯጭ ዘረሰናይ ታደሰ ዘንድሮ ሳይሳካለት በ6ኛነት አጠናቋል። ዘረሰናይ በዚህ የሩጫ ዘርፍ ለሦስት ጊዜያት በማሸነፍ የ58:23 የዓለም ክብር ወሰን ማስመዝገብ የቻለ አትሌት ነው። በሊዛቦኑ ፉክክር አንደኛ የወጣው ኬንያዊ ኢሪክ ኪፕታኑይ ሲኾን፤ ያጠናቀቀውም 1 ሰአት ከ5 ሰከንድ በመሮጥ ነው። የኤርትራው ዮሐንስ ገብረ ገርግሽ በኤሪክ በ11 ሰከንድ ብቻ ተበልጦ ኹለተኛ መኾን ችሏል። ከዓመታት በፊት በፕራግ ማራቶን ምርጥ ሰአት አስመዝግቦ የነበረው  አጸዱ ፀጋዬ  ዘረሰናይን አስከትሎ በአምስተኛነት አጠናቋል። 

40,000 ሯጮች ተካፋይ በነበሩበት 44ኛው የዴን ሐጉ የማራቶን ሩጫ ስዊዘርላንዳዊቷ ማያ ኖየንሽቫንደር የግል ሰአቷን በማሻሻል አንደኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያውያቱ አትሌት ገነት በየነ እና ዘውድነሽ አየለ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።  

እግር ኳስ
ነገ እና ከነገ በስትያ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ነገ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ የስፔኑ ሴቪላን ሲፋለም፤ የጣሊያኑ ሮማ ከዩክሬኑ ሻካታር ዶኒዬትስክ ጋር ይጋጠማል።  

ከነገ በስትያ ደግሞ፦በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዡን አኹንም የተቆጣጠረው ባርሴሎና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲን ይገጥማል። ቅዳሜ እለት ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 ማሸነፍ የተሳካለት ቸልሲ ረቡዕ በሚኖረው ግጥሚያ ከባርሴሎና ብርቱ ፈተና ይገጥመዋል። ቀደም ሲል የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት የደረሰበት የባርሴሎና አምበል አንድሬስ ኢኔስታ ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ አድርጓል። ወንድ ልጁ ሲወለድ ሐኪም ቤት የተገኘውና በላሊጋው የቅዳሜ ግጥሚያ ያልተሰለፈው ሊዮኔል ሜሲም በቸልሲው ግጥሚያ እንደሚካተት ተገልጧል።  

ረቡዕ በሌላ ጨዋታ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን የቱርኩ ቤሺክታስ ኢስታንቡልን ይገጥማል። ቅዳሜ ዕለት በቡንደስ ሊጋው ወራጅ ቃጣና ውስጥ የሚገኘው ሐምቡርግን  6 ለ0 ላንኮታኮተው ባየር ሙይንሽን ከነገ በስትያ የሚያከናውነው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የሚከብደው አይመስልም። ባየርን ሙይንሽን ቀደም ሲል ቤሺክታስ ኢስታንቡልን ገጥሞ ድል ያደረገው በሰፋ ልዩነት 5 ለ0 ነበር።  

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል። የሚጋጠመውም ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ከሚገኘው ስቶክ ሲቲ ጋር ነው።  ትናንት ቶትንሀም በርመስን 4 ለ1 በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ መኾን ችሏል። 61 ነጥብ ያለው ቶትንሀም በማንቸስተር ዩናይትድ የሚበለጠው በ4 ነጥብ ብቻ ነው። በ1 ነጥብ ብቻ የሚበለጠው ሊቨርፑል በበኩሉ 60 ነጥብ ይዞ በ4ኛነት ይከተለዋል። ሊቨርፑልን 2 ለ1 አሸንፎ ቅዳሜ እለት ነጥብ ያስጣለው ማንቸስተር ዩናይትድ 65 ነጥብ ሲኖረው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ  በ13 ነጥብ ይበለጣል።  

በስፔን ላሊጋ 
ዛሬ ማታ ዲፖርቲቮ አላቬስ ከቤቲስ ሴቪላ ጋር ይጋጠማል። ከትናንት በስትያ ማላጋን 2 ለ0 ያሸነፈው ባርሴሎና 72 ነጥብ ይዞ ይገሰግሳል። ትናንት ሴልታቪጎን 3 ለ0 ድል ያደረገው አትሌቲኮ ማድሪድ በ64 ነጥብ ይከተላል። ከትናንት በስትያ አይበርን 2 ለ1 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ 57 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።   

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ሐምቡርግን 6 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል ባደረገበት ግጥሚያ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል። ፍራንክ ሪቤሪ የመጀመሪያዋን ለራሱ ሁለተኛዋን ግብ ለቡድኑ ተጨዋቾችን በማታለል አስቆጥሯል። የሪቤሪ ድንቅ ግቦች በዕለቱ ብቃቱን ያስመሰከረበት ነበር። አንደኛው ግብ የተቆጠረውው በአርየን ሮበን ነው።

ፓራሊምፒክ

ደቡብ ኮሪያ ፒዮንግ ቻንግ ውስጥ ዓርብ እለት በተጀመረው የፓራሊምፒክ ግጥሚያ ዩናይትድ ስቴትስ በሜዳሊያ ሠንጠረዥ እየመራች ትገኛለች። ፓራሊምፒክ የኦሎምፒክ ውድድር ሲጠናቀቅ የሚኪያሄድ ሲኾን፤ ተወዳዳሪዎችም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው አትሌቶች ናቸው። ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ውድር እስካሁን ቀዳሚ የኾነችው 15 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ 6 የወርቅ፣ 5 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያ አላት። ፈረንሣይ በወርቅም፤ በብርም በነሐስም ተመሳሳይ 3 በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ በሁለተኛነት ትከተላለች። ዩክሬን 9 ሜዳሊያ ይዛ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የፓራሊምፒክ ውድድሩ የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች