ስፖርት፤ መስከረም ም 21 ቀን፣ 2011 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 01.10.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ መስከረም ም 21 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

​​​​​​​«ማንቸስተር ዩናይትድን ምን ነካው?» በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ «ቀያዮቹ ሴጣኖች» ዘንድሮ ውሉ የጠፋባቸው ይመስላል፤ ከዋነኛ ተፎካካሪዎቻቸው በ9 ነጥብ ርቀት ዝቅ ብለው በአዲስ መጤው ዎልቭስ ተበልጠው 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በታላቁ የስኮትላንድ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማሬ ዲባባ ድል ተቀዳጅታለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:42

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

«ማንቸስተር ዩናይትድን ምን ነካው?» በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ «ቀያዮቹ ሴጣኖች» ዘንድሮ ውሉ የጠፋባቸው ይመስላል፤ ከዋነኛ ተፎካካሪዎቻቸው በ9 ነጥብ ርቀት ዝቅ ብለው በአዲስ መጤው ዉልቭስ ተበልጠው 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ሽንፈት ሲቀምስ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተንን የሚያስቆመው አልተገኘም። በታላቁ የስኮትላንድ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማሬ ዲባባ ግላስኮው ከተማ ውስጥ ድል ተቀዳጅታለች።  

አትሌቲክስ

አትሌት ማሬ ዲባባ ስኮትላንድ ግላስኮው ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ እሽቅድምድም አሸናፊ ኾናለች። በኦሎምፒክ የማራቶን ሩጫ ውድድር የነሐስ ባለቤቷ አትሌት ማሬ የስኮትላንድ ታላቁ ሩጫ ላይ ለድል የበቃችው 1 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በመሮጥ ነው።  ትውልደ-ኬንያዊቷ የባሕሬን  ሯጭ ሮዝ ቼሊሞ እና አሜሪካዊቷ አሊያ ግሬይ ማሬን ተከትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል።  የሩጫ ፉክክሩን ያጠናቀቁበት ጊዜም 1 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ እና 1 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ ኾኖ ተመዝግቧል።

በወንዶች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር የብሪታንያው የረዥም ርቀት ተፎካካሪ ክሪስ ቶምሰን አንደኛ ወጥቷል። ፖላንዳዊው ሯጭ ማርቪን ቻቦውስኪ እና ብሪታንያዊው ሉክ ትራይነር በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ አጠናቀዋል።

30,000 ግድም ታዳሚያን በተሳተፉበት በታላቁ የስኮትላንድ ሩጫ ውድድር በተለያዩ የርቀት አይነቶች በርካታ ውድድሮች የተከናወኑ ሲኾን፤ ታዳሚዎችን ያስደመመ ክስተትም ታይቷል። ሁለት እግሮቹ እና እጆቹ የማይነቀሳቀሱ ኪራን አለን የተሰኘ አንድ የ10 ዓመት ልጅ ከጀርባው በታሰረለት ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪ እና በቤተሰቦቹ ርዳታ የሩጫ ውድድሩ ሜዳ ላይ ሊያገባድድ ያሰበውን ርቀት አጠናቋል።  በስተመጨረሻም ታዳጊው በደስታ ሲፍለቀለቅ ታይቷል።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ከአንድ ቡድን በስተቀር ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ግስጋሴያቸውን እንደቀጠሉ ነው። መሪው ማንቸስተር ሲቲ፤ ሊቨርፑልን፤ ቸልሲን፤ ቶትንሐምን፤ እና አርሰናልን አስከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድን በ9 ነጥብ ርቆ ይገኛል። እስካሁን በተከናወኑ 7 ጨዋታዎች 10 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከታችኛው ዲቪዢዮን ባደገው ዎልቭስ ቡድን ለጊዜውም ቢኾን መበለጡ በርካታ ደጋፊዎቹን አበሳጭቷል። ባለፈው የውድድር ዘመን የተሰናበቱት ስዋንሲ ሲቲ፣ ስቶክ ሲቲ እና ዌስት ብሮሚች አልቢኖን ከተኩት ሦስት ቡድኖች ውስጥ ዎልብስ አንዱ ነው። ካርዲፍ እና ፉልሀም ወራጅ ቃጣና እና ግርጌ ላይ ይገኛሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ መሪ የነበረው ሊቨርፑል ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቸልሲ ጋር ቅዳሜ ዕለት ያደረጉት ግጥሚያ እጅግ የተጠበቀ ነበር። ሊቨርፑል ደረጃውን ላለማስነጠቅ ቸልሲ ደግሞ በአንድ ደረጃ ከፍ ለማለት የተናነቁበት ጨዋታ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ግን የማሸነፍ ዕድላቸው ሳይሰምር አንድ እኩል ተለያይተው ነጥብ ተጋርተዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ኤደን ሐዛርድ ለቸልሲ ያስቆጠራት ግብ ሊቨርፑሎች ወደ ማጥቃቱ እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል። ኤደን ሐዛርድ በ7 ጨዋታ 9 ጊዜ ወደ ግብ ሞክሮ 6ቱን ከመረብ በማሳረፍ የግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል።

በ32ኛው ደቂቃ ላይ ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላህ  የቸልሲ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ ኬፓ አሪዛባላጋን አልፎ በመጠምዘዝ ኳሷን ወደ ግብ መላክ ተሳክቶለት ነበር። የጀርመኑ ተከላካይ አንቶኒዮ ሮዲገር ግን ማን ድንበሬን ጥሶ ሲል አስወግዷታል። የሁለተኛው አጋማሽ 59 ደቂቃ ላይ ሳዲዮ ማኔ በሮቤርቶ ፊርሚኖ ተመቻችቶ የተላከለትን ኳስ በሦስት ተከላካዮች መሀከል ግሩም በኾነ መልኩ ቢሞክርም ከአትሌቲክ ቢልባዎ በ71,6 ሚሊዮን ፓውንድ የተዘዋወረው የቸልሲ ግብ ጠባቂ በድንቅ ኹኔታ አክሽፎበታል። 64ኛው ደቂቃ ላይ ሞ ሳላህ ጥፋት ፈጽሞ ዳኛው ፊሽካ ከመንፋታቸው እንጎሎ ኮንቴ በፍጥነት ኳሷን ወደ ሊቨርፑል ክልል የላካትና ኤደን ሐዛርድ  ያደረገው የግብ ሙከራ ለሊቨርፑል አስደንጋጭ ነበር።

ለሊቨርፑል ተቀይሮ የገባው ሼርዳን ሻቂሪ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ የመኾን ዕድል አምክኗል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤርቶ ፊርሚኖ ዘሎ በጭንቅላት ወደ ግብ የላካት ኳስ በተከላካይ ግብ ከመኾን ተርፋለች። ጫና መፍጠሩ እያየለ የመጣው ሊቨርፑል ተቀይሮ በገባው ዳንኤል ስቱሪጅ የተረጋጋጋ ምት አቻ የምታደርገውን ግብ በ89ኛ ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ ሊቨርፑል ቸልሲን ልቆ ታይቷል። 

ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ ጨዋታዎች፦ ኤቨርተን ፉልሐምን 3 ለ0፤ ማንቸስተር ሲቲ ብሪንግቶንን፤ ላይስተር ሲቲ ኒውካስትልን፤ ዎልቭስ ሳውዝሐምፕተንን፤ ቶትንሀም ሁደርስፊልድን  እንዲሁም አርሰናል ዋትፎርድን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ በዌስትሐም ዩናይትድ 3 ለ1 ድል ተነስቷል።  ትናንት ካርዲፍ ሲቲ በበርንሌይ 2 ለ1 ተሸንፏል። ዛሬ ማታ ክሪስታል ፓላስ ከበርመስ ጋር ይጋጠማል። በደረጃ ሰንጠረዡ መሪው ማንቸስተር ሲቲ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ከሚከተለው ሊቨርፑል ጋር የፊታችን እሁድ የሚያደርጉት ጨዋታ እጅግ ይጠበቃል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠመው ባየር ሙይንሽን መሪነቱን ለቅርብ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አስረክቧል። «ድንቅ፤ እጅግ እጅግ ድንቅ!»  ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል የቦሪስያ ዶርትሙንዱ አሰልጣኝ  ሉቺዬን ፋቭሬ ቡድናቸው ባየር ሌቨርኩሰንን 4 ለ 2 አሰናብቶ የመሪነቱን ስፍራ ሲቆናጠጥ። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዐርብ እለት ባየር ሙይንሽን በሔርታ ቤርሊን 2 ለ0 ሽንፈት መቅመሱ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባየር ሙይንሽንን በአንድ ነጥብ ልዩነት ቀድሞ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  በስድስት ጨዋታዎች 14 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ባየር ሙይንሽንን ከሁለት ቀን ቀደም ብሎ ጉድ የሠራው ሄርታ ቤርሊን በ13 ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦስተኛ ደረጃ  ይዟል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ በነገው ዕለት ስድስት ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን፣ ከሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም፤ እንዲሁም ሌላኛው የጀርመን ቡድን ቦሩስያ ዶርትሙንድ የፈረንሳዩ ሞናኮን፤ ማንቸስተር ሲቲ ከሆፈንሀይም፤ ሻልከ ከሎኮሞቲቭ ሞስኮው ይገጥማሉ።

ሪያል ማድሪድ ከሲኤስ ኬኤ ሞስኮው፤ ቶትንሀም ከባርሴሎና፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቫሌንሺያ፤ ቤኔፊካ ከኤኢኬ፤ ሊቨርፑል ከናፖሊ፤ሮማ ከፕሌሴን፤ ጁቬንቱስ ከያንግቦይስ፤ ሊዮን ከሻካታር ዶኔትስክ ፤ ፒኤስጂ ከሬድ ስታር ቤልግሬድ፤ ፖርቶ ከጋላታሳራይ፤ ኢንተር ሚላን ከፒኤስቪ አይንድሆቨን፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከክለብ ብሩጅ ጋር ይጋጠማሉ።

የመኪና ሽቅድምምድ

በሩስያው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምምድ የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ድል ቀንቶታል። በትናንቱ ፉክክር የብሪታንያው አሽከርካሪ ያስመዘገበው ድል ዘንድሮም በአጠቃላይ ውድድር አሸናፊ ለመኾን በርከፍቶለታል። ሐሚልተን እስካሁን በሰበሰበው ነጥብ ከጀርመናዊ ተፊፎካካሪው ሰባስቲያን ፌትል በ50 ነጥብ ልቆ ይገኛል። የትናንቱ ድል ታክሎበት ሌዊስ ሐሚልተን እስካሁን 306 ነጥብ መሰብሰብ ሲችል የፌራሪው አሽከርካሪ ሰባስትያን በ256 ይከተላል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ 189 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ይከተላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic