ስፖርት፣ ሐምሌ 25፣ 2008 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 01.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፣ ሐምሌ 25፣ 2008 ዓ.ም

በዋናነት የሩጫ ተፎካካሪዎችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የመጀመሪያ ዙር ጉዞውን ረቡዕ ይጀምራል። ቡድኑ በሦስት የስፖርቶች ዘርፍ እንደሚሳተፍ ተገልጧል። ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በዋናነት ከአውሮጳ ሃገራት የተሰባሰቡ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስፖርት አፍቃሪዎችና ታዳሚያን ዘንድሮ ኔዘርላንድ ዴን ሀግ ከተማ ውስጥ ተገናኝተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:23

ስፖርት

ከህጻናት አንስቶ የአዋቂዎች የእግር ኳስ ውድድሮች እና ሌሎች ባህላዊ ክስተቶች የተከናወኑበት የስፖርት እና የባህል ዝግጅት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ተከናውኗል። በአዋቂዎች የእግር ኳስ ውድድር አምና ለዋንጫ ደርሶ የነበረው የኖርዌይ ቡድን ዘንድሮ ተሳክቶለታል።

የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ሪዮ ከተማ ብራዚል ውስጥ ሊጀመር አራት ቀናት ብቻ ይቀሩታል። ዘንድሮ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክሱ ባሻገር በብስክሌት እና በውሃ ዋና ውድድሮችም ትሳተፋለች። የኦሎምፒክ ቡድኑ 38 አትሌቶች እና 22 የልዑካን ቡድናትን በአጠቃላይ 60 አባላትን እንዳካተተ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ዋና ጸሐፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ተናግረዋል። ለሁለት ሳምንት የሚከናወነው የሪዮ ኦሎምፒክ የፊታችን ዓርብ ይጀመራል።

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል14ኛው ዙር ዘንድሮ በኔዘርላንድ ዴን ሀግ ከተማ ውስጥ ተከናውኗል። ከረቡዕ አንስቶ እስከ ቅዳሜ ድረስ በቆየው የስፖርት ውድድር እና ባህላዊ ክንዋኔዎች 10,000 ያህል ታዳሚያን በስፍራው እንደተገኙ ፌዴሬሽኑ ድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። በአዋቂዎች የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር 20 ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ። ዘንድሮ ኢትዮ ኖርዌይ እና ኢትዮ ስዊስ ለፍጻሜ ደርሰዋል። ኢትዮ ኖርዌይ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ነበር ብልጫ ማሳየት የጀመረው።ኢትዮ ኖርዌይ በተከታታይ ባስቆጠራቸው ግቦች ኢትዮ ስዊስን 5 ለ1 በማሸነፍ ዘንድሮ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል። ኢትዮ ስዊስን በጨዋታ በልጦ ለድል የበቃው ኢትዮ ኖርዌይ ባለፈው ዓመት ውድድርም ለፍጻሜ ደርሶ ነበር የተሸነፈው። በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ሕዝብ ግንኙነት አቶ ግርማ ሣኅሌ።

የዘንድሮው ዝግጅት የተሰናዳው ውድድሩ በተኪያሄደበት ሀገር ማለትም በሆላንድ ቡድን ሳይሆን በፌዴሬሽኑ መሆኑ ከበፊቱ ለየት አድርጎታል። የፌዴሬሽኑ ሊቀ-መንበር አቶ ዮሐንስ መሰለ የመጀመሪያ ዝግጅታቸው ጥንካሬም ድክመት እንዳለው ጠቅሰዋል። በእርግጥም ታዳሚያኑ እጅግ ሲዝናኑ ነበር።

ዝግጅቱ ከተከናወነበት ሰፊ ሜዳ መግቢያ በስተቀኝ ሲል 10 መጠነኛ ዳሶች ተጥለዋል። በዳሶቹ ውስጥ የምግብ ሽያጭ ሲከናወን ነበር። ሽያጩን የሚያከናውኑትም የበጎ አድራጊዎች እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መሆናቸውን አቶ ግርማ ሣኅሌ ተናግረዋል። በስተግራ በኩል ደግሞ የስጦታ እቃዎችን ሽያጭ ለሚያደርጉ እና ለሰአሊዎች በአጠቃላይ 20 ድንኳኖች ተዘጋጅተው ሽያጭ ሲያከናውኑ ነበር ከዚያም ባሻገር የሰርከስ ትርኢት፣ የውዝዋዜ እና ሙዚቃ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ሌሊቱን ደግሞ አምስተርዳም ከተማ ውስጥ የሙዚቃ ድግስ ተከናውኖ የዘንድሮ መሰናዶ ተጠናቋል። ውድድሮቹ ዴን ሀግ ከተማ ውስጥ ተከናውነው የለሊቱ የሙዚቃ ድግስ ግን አምስተርዳም ከተማ መሆኑ በአንዳንድ ታዳሚያን ዘንድ ቅሬታ ተሰምቷል። ፌዴሬሽኑ ልክ እንደ ዘንድሮው ሁሉ በሚቀጥለው ዓመትም ዝግጅቱን ራሱ ለማሰናዳት እያሰበበት መሆኑን ሊቀ-መንበሩ ገልጠዋል። የሚቀጥለው ዓመት ውድድር የት ሀገር እንደሚከናወን መስከረም ወር ውስጥ ይገለጣል ተብሏል። ዝግጅቱን ለምን ለእኛ አሰጠንም ሲሉ ከአዘጋጆቹ የተጨቃጨቁም ነበሩ።ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 12 ዓመት ባሉት የህጻናት ውድድሮች 8 ቡድኖች ተካፍለው ኢትዮ ዙሪክ ኢትዮ በርሊንን በፍጹም ቅጣት ምት 3 ለ 2 አሸንፏል። ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 16 ዓመት ታዳጊዎች መካከልም 8 ቡድኖች ተካፋይ ነበሩ። በፍጻሜው ኢትዮ ስዊስ ኢትዮ በርሊንን 3 ለ 1 ድል አድርጎ ዋንጫ ወስዷል። በአዋቂዎች የሁለተኛ ዲቪዢዮን ጨዋታ ደግሞ ኢትዮ ስዊድን ከኢትዮ በርገን ጋር በመደበኛው ጨዋታ 3 ለ3 የወጣ ሲሆን፤ በፍጹም ቅጣት ምት ኢትዮ በርገን 6 ለ5 አሸንፏል። አንደኛ ዲቪዚዮን የጸባይ ዋንጫ ለጣሊያኑ ኢትዮ ኤሚሊያ ተሰጥቷል። ኮከብ ተጨዋች፣ ግብ ጠባቂ እና አሠልጣኝ አሸናፊ የሆነው የኖርዌይ ቡድን ነው።

የጀርመን ብሔራዊ ቤድን አማካይ ሌሮይ ሳኔ በ37 ሚሊዮን ፓውንድ ስምምነት ለማንቸስተር ሲቲ ሊፈርም መቃረቡ ተዘግቧል። የማንቸስተር ሲቲ አዲሱ አሰልጣን ፔፕ ጓርዲዮላ ሌሮይን ማስፈረም እንደሚፈልጉ ቀደም ሲል ገልጠው ነበር። ሌሮይ ሳኔ በጀርመን ቡንደስሊጋ ቆይታው በአምስተኛ ደረጃ ላጠናቀቀው ቡድኑ ሻልከ ስምምነት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

በኾዜ ሞሪኝሆ አዲስ አሰልጣኝነት ዘንድሮ ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ቀድሞ ዝናው ይመለሳል ሲል የቡድኑ አጥቂ እና አማካይ ዋይኔ ሩኒ ተናግሯል። ሌላኛው የቡድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ማንቸስተር ዩናይትድ ወደፊት ለመገስገስ አንዳች አቅም አለው ሲል ተናግሯል። ማንቸስተር ዩናይትድ የቱርኩ ጋላታሰራይን 5 ለ2 ባሸነፈበት ጨዋታ ኢብራሒሞቪች ጥንካሬውን አሳይቷል።ለሰማያዊዎቹ ዘንድሮ ለመጫወት የየፈረመው ኤደን ሃዛርድ ቸልሲ ከ100 ሺህ በላይ ተመልካቾች ፊት 3 ለ2 በተሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ቸልሲ በሪያል ማድሪድ 3 ለ2 በተሸነፈበት ጨዋታ ኤደን ሃዛርድ በመጀመሪያ ቀን የቸልሲ ተሰላፊነቱ በተከታታይ ግብ በማስቆጠር አጀማመሩን አሳምሯል። ቸልሲ ለወዳጅነት ረቡዕ እለት ሊቨርፑልን ባሸነፈበት ጨዋታ ግን ኤደን ሃዛርድ ከአውሮጳ ዋንጫ ጨዋታ ድካሙ ረፍት እንዲያደርግ በሚል አልተሰለፍም ነበር። ሪያል ማድሪድ ላይ ግን በተከታታይ አስቆጥሯጥሯል።

የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች በአስደናቂ ሁኔታ ከዌምብልደን ውድድር ከወጣ በኋላ የጃፓኑን ካይ ኒሺኮሪን በማሸነፍ ለድል በቅተዋል። ኖቫክ በቶሮንቶው ሮጀር ከፕ የፍጻሜ ውድድር ላይ ካይን የረታው 6-3 7-5 በሆነ ውጤት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድAudios and videos on the topic