ስፖርት ህዳር 27፣ 2008 ዓ,ም | ስፖርት | DW | 07.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ስፖርት ህዳር 27፣ 2008 ዓ,ም

በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪቃ የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ይዞታ፤በአሜሪካን የፌደራል ምርመራ ቢሮ የተያዘው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር አዲስ የሙስና ቅሌትና የአውሮጳ የሊግ ውድድሮች

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:35 ደቂቃ

ስፖርት ህዳር 27፣ 2008 ዓ,ም

ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪቃ የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ርዋንዳን አንድ ለምንም ያሸነፈችው ዩጋንዳ የዋንጫ ባለቤት ሆናለች። ለሴዛር ኦክሁቲ ምስጋና ይግባውና በ15ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ዩጋንዳን ለ14ኛ ጊዜ የቀጣናው የበላይ አድርጓታል።

በነገራችን ላይ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ የእግር ኳስ ማህበራት ካውንስል አባል ከሆኑ አገሮች መካከል በጎርጎሮሳዊው በ2018 ዓ.ም. ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ መድረስ የቻለው አዲስ አበባ ላይ የሴካፋ ዋንጫን ያነሳው የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ብቻ ነው።

በዕለተ ቅዳሜ ከዋንጫ ጨዋታው ቀደም ብሎ የውድድሩ አዘጋጅ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችውን የደረጃ ጨዋታ ሙሉ ጊዜ አንድ አቻ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ጨዋታውን ኤልያስ ማሞ ባስቆጠራት ጎል ቀደም ብላ መምራት ብትጀምርም በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ አልተሳካላትም። የሱዳኑ ዋላልዲን ሙሳ ያጉብ ያስቆጠራት ጎል ጨዋታው በአቻ ተጠናቆ ወደ መለያ ምት እንዲሻገር አድርጋለች። በመለያ ምቱ ኢትዮጵያ ሱዳንን 5-4አሸንፋ በሶስተኛ ደረጃ አጠናቃለች።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ያሳየው ብቃት ምን ይመስል ነበር? ይህን ጥያቄ ለስፖርት ጋዜጠኛና ተንታኙ መንሱር አብዱልቀኒ አንስተን ነበር።

«ቡድኑ ለደጋፊ የሚመች ቡድን አልነበረም። ውጤት የሚጠበቅበትም አልነበረም።» የሚለው የስፖርት ተንታኙ ውህደት የጎደለው እንደነበር ይተቻል። በአገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን ይዞ የተዋቀረው ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከአልጄሪያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ በብቃት ለመወጣቱም መንሱር አብዱልቀኒ ስጋት አለው።

ቅዳሜ ዕለት በተጠናቀቀው የሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ከተሳተፉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ፤ዩጋንዳና ርዋንዳ በመጪው ጥር ለሚካሄደው የፓን አፍሪቃ ዋንጫ አልፈዋል። ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከአልጄሪያ፤ሲሸልስና ሌሴቶ ጋር ተደልድላለች። እሳካሁን ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ሌሴቶን 2 ለ1 ስታሸንፍ ከሲሸልስ አቻ ተለያይታለች።በመጪው መጋቢት ከምድቡ ጠንካራ ቡድን ናይጄሪያ ጋር ተከታታይ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአህጉራዊው ውድድር ባላት ተሳትፎ ላይ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል።

የአውሮጳ ሊጎች

የጆሴ ሞሪንሆ እንደገና አንገታቸውን ደፍተዋል። ከፖርቹጋል ተነስተው በብሪታኒያ፤ጣልያንና ስፔን ስኬትን የተጎናጸፉት ሞሪንሆ ቅዳሜ እለት ምን አልባት በአሰልጣኝነት ዘመናቸው አስከፊ ሊባል የሚችለው ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ በ14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቼልሲ ከቦርንማውዝ ባደረገው ጨዋታ አንድ ለምንም ተሸንፏል። ይህ ለቼልሲ የውድድር አመቱ ስምንተኛ ሽንፈት መሆኑ ነው።

ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከዌስትሐም ያደረገውን ጨዋታ ያለ ግብ አጠናቋል። የእግር ኳስ ተንታኞች የልዊስ ቫንጋል ቡድን አሰልቺ እግር ኳስ እየተጫወተ እንደሆነ ተችተዋል። ኦልትራፎርድ ላይ በተደረገው ጨዋታ የተሻለ አቋም ያሳየው እንግዳው ዌስትሐም ሁለት የግብ ሙከራዎች የጎል ብረቱን ገጭተዋል።

እለተ ቅዳሜ ለማንችስተር ሲቲ እና አሰልጣኙ ማኑዔል ፔሊግሪኒም መልካም ቀን አልነበረም። ወደ ብሪታኒያ ስታዲየም ያቀናው ማንችስተር ሲቲ በማርኮ አርናቶቢች ሁለት ግቦች ተሸንፎ ተመልሷል።

የየርገን ክሎፕ ሊቨርፑል በበኩሉ እሁድ ዕለት በኒውካስል ሁለት ለምንም ተሸንፏል።የሊቨርፑሉ ተከላካይ በራሱ መረብ ላይ ግብ ያስቆጠረበት ጨዋት ለአሰልጣኙ ቁጭት ወልዷል።

ወደ ዌልስ ተጉዞ በሊበርቲ ስታዲየም ስዋንሲን የገጠመው ሌስተር ሲቲ ሶስት ለምንም አሸንፎ ተመልሷል። አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ሶሶቱንም ግቦች አስቆጥሯል።

በእለተ እሁድ አንድ ጨዋታ የተጫወተው የአርሰናሉ አጥቂ ኦሊቨር ግሩድ ለሁለት ቡድኖች ግብ አስቆጥሯል። ለንደን ላይ በኢሚሬትስ ስታዲየም ሰንደርላንድን የገጠመው አርሰናል በ33ኛው ደቂቃ በጆዔል ካምቤል ባስቆጠራት ጎል አንድ ለምንም እየመራ ነበር። አጥቂው ኦሊቨር ግሩድ የሰንደርላንዱ አማካኝ ያን ምቪያ ያሻማትን ኳስ በ45ኛው ደቂቃ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ጨዋታውን ወደ አቻ ቀየረው። ግሩድ በሁለተኛው አጋማሽ በ63ኛው ደቂቃ ለአርሰናል ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ጥፋቱን ክሷል። አማካኙ ራምሴ በጨዋታው መገባደጃ ሶስተኛ ግብ በማከል ጨዋታው 3ለ1 ተጠናቋል። በዚህም ጨዋታ ጀርመናዊው የመሃል ሜዳ አማካኝ ሜሱት ኦዚል ኮከብ ሆኖ አምሽቷል።

የደረጃ ሰንጠረዡን ሊስተር ሲቲ በ32 ነጥብ በቀዳሚነት ይመራል። አርሰናልበሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ማንችስተር ሲቲ እና ማንችስተር ዩናይትድ በእኩል 29 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በስፔን ላሊጋ የሪያል ማድሪድ የአጥቂዎች ጥምረት እንደገና አንሰራርቶ ፍሬ አፍርቷል። ቅዳሜ እለት በሳንቲያጎ በርናባው ጌታፌን ያስተናገደው ሪያል ማድሪድ በካሪም ቤንዜማ፤ጋሬዝ ቤል እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጎሎች አራት ለአንድ አሸንፏል። ካሪም ቤንዜማ ሁለት ባስቆጠረበት ጨዋታ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች በአሰልጣኙ ራፋ ቤኒቴዝ ላይ ሲያጉረመርሙ ተደምጠዋል።

ሌላው የዋና ከተማ ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ ግራናዳን ሁለት ለምንም አሸንፏል። በጨዋታው አንቶኒዮ ግሪዝማን እና ዲየጎ ጎዲን ለአትሌቲኮ ማድሪድ ሁለቱን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል።

በሜዳው ሴልታ ቪጎን ያስተናገደው ሪያል ቤቲስ ጨዋታውን በአንድ አቻ ውጤት አጠናቋል። ጆርጌ ሞሊና ለሪያል ቤቲስ ቲዎ ቦንጎንዳ ለ ሴልታ ቪጎ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ወደ ደ ማስቴላ ስቴዲየም ያቀናው ባርሴሎና የማሸነፍ ጉዞ ለጊዜው ገታ ብሏል። የቀድሞውን የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ጋሪ ኔቭልን በአሰልጣኝነት የቀጠረው ቫሌንሲያ ሳቲ ሚና ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ለባርሴሎና ልዊስ ሱዓሬዝ ነበር በ59ኛው ደቂቃ ጎልና መረብን ያገናኘው።

ላሊጋውን አስራ አራት ጨዋታዎች ተጫውቶ አስራ አንዱን በአሸናፊነት የተወጣው ባርሴሎና በ34 ነጥቦች ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ አስር አሸንፎ በ32 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። የራፋ ቤኒቴዙ ሪያል ማድሪድ ዘጠኝ አሸንፎ በ30 ነጥብ ሶስተኛ ሴልታ ቪጎ በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙኒክ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል። በአስራ አራት ጨዋታዎች አንድም ጊዜ ሳይሸነፉ ሙንሽንግላድባህ ወደሚደገኘው ቦሩስያ ፓርክ ያቀኑት ባየር ሙኒኮች ሶስት ግቦች ተቆጥረውባቸው አንድ ማስተዛዘኛ አግብተው ተሸንፈዋል። የመጀመሪያውን አጋማሽ ባየር ሙኒክ ተጭኖ ቢጫወትም የቦሩስያ ሞንቼግላድባህ ግብ ጠባቂ ያን ሶመር ልፋታቸውን መና አድርጎታል። በሁለተኛው አጋማሽ ኦስካር ቬንዴት፤ላርስ ስቲንድል እና ፋብያን ማርኮ ጆንሰን ለቦሩስያ ሙንሽንግላድባህ ሶስት ግቦች አስቆጥረዋል። ፍራንክ ሪቤሪ በ81ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ለፔፕ ጋርዲዮላው ባየር ሙኒክ በቂ አልሆነችም። ከጨዋታው በኋላ አስተያየት የሰጠው የባየር ሙኒኩ ተከላካይ ፍሊፕ ላህም በአምስት ደቂቃ ውስጥ ተሸንፈናል ሲል ተናግሯል።

«በመጀመሪያው አጋማሽ 2:0 ወይም3:0የመምራት እድሉ ነበረን ብዬ አምናለሁ።እንደዛ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ሌላ ይሆን ነበር። ለነገሩ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ነው በጨዋታው የተሸነፍነው።»

የቦሩሲያ ሙንሽንግላድባህ አሰልጣኝ ፋቢያን ጆንሰን « በድፍረት ወደ ፊት እየተጫወትን ነበር። እንደሚመስለኝ የስኬቱ ሚስጥር ይኼ ነው። ምናልባት ከባየርን ጋር የሚገጥሙ አብዛኞቹ እንደሚያደርጉት ራሳችንን አልሸሸግንም።ከ 1:0በኋላም ወደ ፊት እንጫወት ነበር። እንደሚመስለኝ ሁኔታው ባየርንንም ትንሽ አስደንግጧል። እና ጥሩ ተሳክቷል።»በማለት የጨዋታ ፍልስፍናቸውን አሞካሽተዋል።

በሌላ የቡንደስሊጋ ጨዋታ ኸርታ በርሊን ባየር ሊቨርኩዘንን ሁለት ለአንድ አሸንፏል።ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስበርግን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ከመሪው ባየር ሙኒክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቧል። ዶርትሙንድ በ32ኛው ደቂቃ ማርኮ ሬውስ ባስቆጠራት ግብ አሸናፊነትን የተቀዳጀ ቢመስልም በ90ኛው ደቂቃ ሮድሪጌዝ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት አቻ ሆኗል። በጭማሪ ሰዓት ጃፓናዊው የመሃል ሜዳ ሞተር ሺንጂ ካጋዋ ያስቆጠራት ግብን ምሽቱን ለዶርትሚንድ ጣፋጭ አድርጋዋለች።

የጀርመን ቡንደስሊጋን ባየርሙኒክ በ40 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአምስት ዝቅ ብሎ በ35 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ሞንቼግላድባህ እና ኸርታ በርሊን በእኩል 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በጣሊያን ሴሪ አ ቅዳሜ ዕለት ጄኖዋን የገጠመው ኢንተር ሚላን አደም ሊጃጂች ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል አንድ ለምንም አሸንፏል። ናፖሊ ደግሞ በቦሎኛ ሶስት ለአንድ ተሸንፏል። ማቲያ ዴስትሮ በ14 እና60ኛ ው ደቂቃ እንዲሁም ሉካ ሮሴቲኒ በ21ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች የናፖሊን ግስጋሴ ለመግታት በቂ ሆነዋል። በጨዋታው የናፖሊው ጎንዛሎ ሂግዌን በ87 እና90ኛው ደቂቃ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል።

በሌላ ጨዋታ ፊዮሬንቲና ዩዲንዜን አተላንታ ፓሌርሞን በተመሳሳይ ሶስት ለምንም አሸንፈዋል። ጁቬንቱስ ላዚዮን ሁለት ለምንም አሸንፏል።ኤሲ ሚላን ከካርፒ ምንም ለምንም እንዲሁም ሮማ ከቶሪኖ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በሴሪ አ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢንተር ሚላን በ33 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፊዮሬንቲና በ32 ናፖሊ በ31 እንዲሁም ሮማ በ28 ነጥቦች ከሁለት እስከአራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ሴፕ ብላተር-ሌላ ቅሌት?

የታገዱት የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት ተከፍሏል ስለተባለው 100 ሚሊዮን ዶላር ወይም 92 ሚሊዮን ዩሮ ያውቁ ነበር ተብለው በዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል የምርመራ ቢሮ ወይም ኤፍ.ቢ.አይ. እየተመረመሩ ነው። ክፍያው በጎርጎሳዊው በ1990ዎቹ የስዊዘርላንድ ኩባንያ የተፈጸመ ሲሆን በምላሹ ኩባንያው የቴሌቭዥን እና የማስታወቂያ ስራዎች ተሰጥተውታል። እጅ መንሻ ነው የተባለውና አሁን በምርመራ ላይ የሚገኘው የ100 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የቀድሞውን የፊፋ ፕሬዝዳንት ጆ ሃቫላንጅ እና የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ ሪካርዶ ቴክሴራን ያካትታል። ሴፕ ብላተር ስለ ክፍያው የማውቀው ነገር የለም ብለው ቢክዱም የአሜሪካን የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍ.ቢ.አይ መርማሪዎች አላመኗቸውም ተብሏል። ሴፕ ብላተር አሁን በሙስና ቅሌት የሚታመሰውን ዓለም አቀፍ ተቋም መሪነት ከመረከባቸው በፊት በጆ ሃቫላንጅ የስልጣን ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። አሁን በፊፋ የስነ-ስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ ለ90 ቀናት የታገዱት ሴፕ ብላተር በመጪው የካቲት ከስልጣናቸው ይወርዳሉ።

ብላተር ከዚህ ቀደምም የፊፋን የአሰራር ስርዓት በመጣስ እና ለሚሼል ፕላቲኒ ፈፅመውታል በተባለው የ2 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በስዊዘርላንድ መንግስት ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።

አሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic