ስፓኝና አፍሪካዉያን ስደተኞች | የጋዜጦች አምድ | DW | 29.09.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ስፓኝና አፍሪካዉያን ስደተኞች

ወደአንድ መቶ የሚጠጉ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገራት የመጡ ስደተኞች ከሜዲትራኒያን ባህር ደቡብ ዳርቻ በምትገኘዉ የስፓኝ ግዛት ሆና በቀረችዉ የሜሊላ ልሳነምድር ሲገቡ 400 የሚሆኑት ግን በጠባቂዎች ተያዙ። ከአፍሪካ እየተባባሰ የመጣዉ የስደት ሁኔታ ያሳሰበዉ የስፓኝ መንግስት ወደየመጡበት አገር መመለሱን ስራዬ ብሎ በመያያዙ ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትችት እየተሰነዘረበት ነዉ።


በተለያየ መንገድ ወደአገሪቱ የሚሰደዱ ቁጥራቸዉ በመበራከቱም ወደአገራቸዉ የመመለሱ ተግባር እንዳለ ሆኖ ስደተኞችን ለማስተናገድ የተመደበዉን የገንዘብ መጠን የስፓኝ መንግስት ሁለት በመቶ ለመጨመር አስቧል።
100ዎቹ ስደተኞች ከቅኝ ግዛት ዘመን በኋላም በስፓኝ ቁጥጥር ስር ወደምትገኘዉ ሜሊላ ለመግባት የቻሉት ግዛቲቱን ከሌላዉ የሞሮኮ አካል የሚለዩትን ሁለት ግዙፍ ቅጥሮች በመዝለል ነዉ።
እንዲህ ያለዉ የስደተኛ ማዕበል ይላል ዘገባዉ ከመከሰቱ ጥቂት ሰዓታት በፊት የስፓኝ ቴሌቪዥን ድንበር ጠባቂዎች ተመሳሳይ የድንበር መሻገር ባለፈዉ መስከረም 10ዕለት ተከስቶ ያንን ለመግታት ሲታኮሱ የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም አሳይቷል።
በተጨማሪም በስንት ጭንቅ ጥበቃዉንና አጥሩን አልፈዉ ወደሞሮኳዊ ስፓኝ ግዛቷ የገቡትን ያልተመዘገቡ ስደተኞች ወዲያዉ በህገወጥ መንገድ ወደሞሮኮ ሲመልሷቸዉም ያሳያል።
ስደተኞቹ በሰሜን አፍሪካ ወደሚገኙት ሜሊላና ኪዩታ ወደተባለችዉ ሌላኟዋ የስፓኝ ልሳነ ምድር ለመግባት የሚያደርጉት ሙከራ አጥር በመዝለል ብቻ አያበቃም።
ከሞሮኮ የባህር ዳርቻ እስከ ስፓኝ ግዛቶች ጠረፍ በዋና ለመሻገር የሚሞክሩ የመኖራቸዉን ያህል በገደል አፋፍ ጥግ መጓዝ ሲሞክሩም ተንሸራተዉ ባህር ዉስጥ በመግባት ያለቁትን ቤቱ ይቁጠራቸዉ።
ለመዝለል የሚሞክሯዋቸዉ ሜሊላን የከበቡ ሁለት ግዙፍ የሽቦ አጥሮችም 5ሜትር ርዝመት ያላቸዉ፤ በስለላ ካሜራና ሲነኳቸዉ ለጠባቂዎች ምልክት በሚሰጡ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ዘዴዎች የተወሳሰቡ ናቸዉ።
ስደተኞቹ ያንን ለማለፍ የሚሞክሩት መሰላል በመጠቀም ሲሆን የመጀሪያዉን ካለፉ በኋላ የሚጠብቃቸዉን ጠባብ የጠባቂዎች መተላለፊያ አልፈዉ ሌላ ተመሳሳይ አጥር ነዉ።
ጠባቂዎቹን የሚያነቃዉ የአደጋ ጥሪ ከጮኸ ሁሉም አከተመ።
ማክሰኞ ዕለት ጠባቂዎቹ እንደገለፁት አጥሩን ሊያልፉ ሲሉ ካጋጠሟቸዉ ስደተኞች ጋር ግጭቱ የተፈጠረዉ በመጡበት እንዲመለሱ ባስገደዷቸዉ ወቅት ነዉ።
በዚህ ሰዓት ጠባቂዎች የፕላስቲክ ጥይቶችን፤ አስለቃሽ ጭስና ዉሃ የመሳሰሉትን በመጠቀማቸዉ ብዙዎች መጎዳታቸዉ ተጠቅሷል።
በስፓኝ የትብብር ህግ መሰረት አንድ ስደተኛ ምድሪቱን እንደረገጠ ወዲያዉ ወደፖሊስ ተወስዶ ምርመራና ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ ከተዋዋለችዉ አገር ከመጣ ወደአገሩ እንደሚመለስ ተነግሮት ይመለሳል። ከሌላት አገራት የመጣ ስደተኛ ከሆነ ግን ከምርመራዉ በኋላ ማቆያ ጣቢያ ይወሰዳል።
ፕሮዲየን በተባለዉ የህፃናት መብት ድርጅት በቪዲዮ ተቀርፆ በስፓኝ ቴሌቪዥን የቀረበዉ ታሪክ ይህን ህግ የሚጥስ ነዉ በሚል ተቃዉሞ ቀስቅሷል።
የሰላም ልዑክ የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ የካቶሊኩ ቄስ ኣንኼል ጋርዚያ ባስቸኳይ አጥሩ መወገድ አለበት ባይ ናቸዉ።
ምንም እንኳን መፍትሄ መስጠት ባንችልም ለራሳቸዉና ለቤተሰቦቻቸዉ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደስፔን የሚገቡትን ስደተኞች ህይወት ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መወገድ ይኖርበታል ሲሉም ይሞግታሉ።
የበርሊን ግንብ በ1981ዓ.ም. ፈርሶ ባየንበት ዘመን በየቦታዉ የሚያሳፍሩ የመለያየት ግድግዳዎች ተገንብተዉ መታየታቸዉ ያስገርማል ሲሉም ተቃዉሟቸዉን ገልፀዋል።
ፓድሬ ኣንኼል በመባል በስፋት የሚታወቁት እኝሁ ቄስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደሜሊላ በመሄድ ያዩትን የመለያ አጥር የበደል አጥር በማለት ነዉ የገለፁት።
በእሳቸዉ እምነትም በአካባቢዉ ሊሰሩ የሚገቡ ስንትና ስንት አሳሳቢ ጉዳዮች ያሉ በከፍተኛ ወጪ መለያ አጥር ገንብቶ ያንን ለመጠበቅ እንቅልፍ ማጣቱ አሳፋሪ ነዉ።
ከዚህ በመነሳትም መጨረሻዉ በአካል ጉዳትና ሞት የሚጠናቀቀዉን የስደተኞችን ሁኔታ ለመቀነስ መደረግ ያለበት ያሉትን ሁለት ሃሳብ ይሰነዝራሉ።
የመጀመሪያዉ የስፓኝና የሞሮኮ መንግስታት ተነጋግረዉ ከሞሮኮም ሆነ ከሌሎች አፍሪካ አገራት የሚፈልሱ ስደተኞችን ቁጥር ለመቆጣጠር መሞከር።
በሌላ ወገን ደግሞ በደቡብ በሚገኙ አገራት የሚታየዉን የድህነት መጠን ለማስወገድ እዉነተኛ የልማት ጥረት ለማድረግ ቆርጦ መነሳት ነዉ።
ይህን ባግባቡ ማድረግ ከተቻለ ስፓኝ ሄዶ ጥቂት ዶላር አገር ቤት ለሚገኙ ወገኖቹ ለመላክ ሲል ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተስፋ የቆረጠ ስደተኛ አይኖርም ይላሉ ቄሱ።