ስጋት ያጠላበት የብሩንዲ ፕሪስ ነፃነት | አፍሪቃ | DW | 19.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ስጋት ያጠላበት የብሩንዲ ፕሪስ ነፃነት

የመንግሥት ግልበጣ በከሸፈባት በቡሩንዲ የፕሪስ ነፃነት የመታፈን ሥጋት አንዳጠላበት ተገለፀ። የቡሩንዲና በሃገሪቱ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማኅበራት እንዳስታወቁት፣ ከብሩንዲ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በኋላ በነፃ መዘገብ አልተቻለም። በዚህም የተነሳ በሃገሪቱ የሚገኙ ገለልተኛ ጋዜጠኞች ሃገር እየለቀቁ እየተሰደዱ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:08
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:08 ደቂቃ

ስጋት ያጠላበት የብሩንዲ ፕሪስ ነፃነት

ከተሰዳጆቹ መካከል የዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ ዘጋቢዎች ይገኙበታል። በቡሩንዲ የመንግስት ግልበጣ ተካሂዶ አንድ ሳምንት እንኳ ሳይሞላዉ ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ሃገራቸዉ ተመልሰዉ መዲና ቡጁምቡራ ላይ ለህዝብ በይፋ የታዩት ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

Bob Rugurika Journalist aus Burundi

የብሩንዲ ጋዜጠኛ ቦብ ሩጉሪካ

ታድያ ጥንካሪያቸዉን ያሳዩት ንኩሩንዚዛ በዝያን እለት ሃገራቸዉ ዉስጥ ምንም ነገር እንደተካሄደ የተነፈሱት ቃል አልነበረም። እንድያም ሆኖ የሳቸዉ በይፋ መታየት ለመገናኛ ብዙኃኑ ትልቅ ክስተት ቢሆንም ከፍተኛ ጫና እየገጠመዉ መሆኑ ታዉቋል። የቡሩንዲና የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ማኅበር ተጠሪ እንደገለፁት፣ በሃገሪቱ የነበሩት በርካታ ገለልተኛ የራድዮና የቴሌቭዥን ጋዜጠኞች በደረሰባቸዉ ጫና ምክንያት ሃገሪቱን ለቀዉ ተሰደዋል። ከነዚህ መካከል ከምሥራቅ አፍሪቃ የሚዘግቡት የዶይቼ ቬለ ተወካይ ጋዜጠኞች ይገኙኙበታል።

« ገለልተኛ የተባሉት የመገናኛ ብዙኃን በሙሉ ስራቸውን እንዳያከናውኑ፣ ሆን ተብሎ እንዲንኮታኮቱ ተደርጓል። ፖሊሶች የሥርጭት ቦታዉን በሮኬት እንዲሁም በቦምብ ነዉ የመቱት። ከነዚህ መካከል እንደ RPA, RT Renaissance, Bonesha እና Isanganiro የተባሉት ታዋቂ የሥርጭት ጣቢያዎች ይገኙበታል።»ሲሉ ኢኖሶ ሙሆዚ ገልፀዋል። በዚህ ርምጃ ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚ የሚሏቸዉን የሥርጭት ጣቢያዎች ለመዝጋት እንዲሁም የተቀሩትን የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶችን በቁጥጥራቸዉ ሥር ለማድረግ መሞከራቸዉ ተጠቅሶአል። በአሁኑ ወቅት በቡሩንዲ የሚታየዉ ቀዉስ በተለይ በሚዲያ ላይ ያነጣጠረ ጦርነት እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ። በቡሩንዲ ታዋቂ የሆነዉ የግል ራድዮ ጣቢያ RPA ማለት (Radio Publique Africain) ዋና ተጠሪ ቦብ ሩጉሪካ ባለፈዉ የሳምንት መጨረሻ ነበር ቡሩንዲን ጥለዉ የሸሹት። እንዲያም ሆኖ ሩጉሪካ ላይ የእስራትና ግድያ ዛቻ ደርሶአቸዋል። RPA የግል ራድዮ ጣቢያ እንደሌላዉ ራድዮ ጣቢያ ሁሉ የመንግሥት ግልበጣዉን የሞከሩት ግለሰቦች ያስተላለፉትን መልክት ማሰራጨቱን የገለፁት የራድዮ ጣቢያዉ ተጠሪ ሩጉሪካ ፣ ይህ እንደሆነ ፖሊስ ስራችን አስቁሞናል።

« ከዚያም ፖሊስ ከምንሠራበት ቦታችን አባረረን። በዚህ ምክንያት ነዋሪዉ በሃገሪቱ ምን እየሆነ ምን ነገር እየተካሄደ እንዳለ የሚያዉቀዉ ነገር የለም። ምናልባት በአሁኑ ወቅት ነዋሪው ነፃ መረጃ ማግኘት የሚችለዉ ከዶይቼ ቬለ፣ ከቪኦኤና ከቢቢሲ፣ አልያም ከራድዮ ፍራስን ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ብቻ ነዉ። »

የግል ሚዲያዎችን ማዉደሙ እጅግ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን የገለጹት በብሩንዲ መዲና ቡጁንቡራ የዶይቼ ቬለ ራድዮ አጋር የሆነዉ «ራድዮ ኢሳንጋኒሮ» ዋና ተጠሪ ጋዜጠኛፓትሪክ ሚታምባሮ በበኩላቸዉ ድርጊቱ በሃገሪቱ የፕሪስ ነፃነት ላይ የተቃጣ ጥቃት መሆኑን ገልፀዋል።

« ድርጊቱ የተፈፀመዉ ፕሬዚዳንቱን በሚደግፉ የፀጥታ አስከባሪዎች ነዉ። በዚሁ ርምጃም የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት መሪ ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬ ያደረጉትን ንግግር በማስተላለፍችን ሊቀጡን ፈልገዉ ነዉ። ከዚህ ቀደም ሲልም ብዙ ዛቻ ደርሶብናል። ጥቃትም ደርሶብን ያውቃል።»


ይህ አይነት ወቀሳ በተደጋጋሚ የተሰነዘረባቸው ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ በተደጋጋሚ ሃሰት ሲሉ ማጣጣላቸዉ ይታወቃል። ፕሬዚዳንቱ ባለፈዉ ሳምንት ዳሬሰላም ላይ በነበሩበት በምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ መሪዎች የጋራ ምክክር ላይ መንግሥታቸዉ ለማኅበረሰብ መብት እና ፕሬሱም ካለምንም ገደብ በነፃ የሚሰራበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች መናገራቸዉ ይታወቃል።

በቡሩንዲ ከሶስት ሳምንት በላይ በቀጠለዉ ተቃዉሞ ከ 20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። እንደ ተመድ በሃገሪቱ ይቀሰቀሳል የሚለዉን ግጭት በመፍራት 105 ሺ በላይ ነዋሪዎች ሃገሪቱን ጥለዉ ተሰደዋል። ስለዚህ ጉዳይ የቡሩንዲ ነዋሪዎች ከሃገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መረጃ ያግኙ አያግኙ ግን የታወቀ ነገር የለም።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic