ስጋት የተደቀነበት የ2ቱ ሱዳኖች የሰላም ውል | አፍሪቃ | DW | 30.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ስጋት የተደቀነበት የ2ቱ ሱዳኖች የሰላም ውል

በደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮች እና በመንግሥቱ አንፃር በሚዋጉ ራሱን የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ጦር፡ በምሕፃሩ ኤስ ፒ ኤል ኤ ብሎ በሚጠራው ቡድን ዓማፅያን መካከል ሰሞኑን በተካሄደ ውጊያ 163 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣን አስታወቁ።

ከተገደሉት መካከል 143 ቱ ዓማፅያን፡ 20 ቹ ደግሞ ወታደሮች ናቸው፤ወደ 20 የሚጠጉ ደግሞ ቆስለዋል። የደቡብ ሱዳን ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፊሊፕ አግወር እንዳስረዱት፡ የመንግሥት ወታደሮች ደቡብ ሱዳን ፣ በሱዳን መንግሥት ይረዳሉ የምትላቸው የኤስ ፒ ኤል ኤም ዓማፅያን ብዙውን የጦር መሣሪያቸውን እና ሌሎች የጦር ቁሳቁስ ያስገቡበት የነበረውን በኦኬሎ ከተማ የሚገኝ አንድ የአየር ማረፊያንም ተቆጣጥረዋል። ኦኬሎ የሚገኘው የዓማፅያኑ መሪ ዴቪድ ያው ያው ትውልድ ቦታ በሆነው በደቡብ ሱዳን ደቡብ ምሥራቃዊ አካባቢ በሚገኘው የጆንግሌይ ግዛት ሲሆን፡ የሱዳን የስለላ ድርጅት በአንቶኖቭ አይሮፕላኖች ላማፅያኑ ያቀበለው ኤኬ-47 ን የመሳሰሉ የጦር መሳሪያዎች በዚሁ ያየር ማረፊያ መያዙን ኮሎኔል አግወር ገልጸዋል።

ዴቪድ ያው ያው በ 2010  ዓም በሱዳን በተካሄደ ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የምክር ቤት እንደራሴነት መንበር ማሸነፍ ሳይችሉ በቀሩበት ጊዜ የሱዳን ገዢ ፓርቲ ምርጫውን አጭበርብሮዋል በሚል ነበር ትግል የጀመሩት። ከዚያ ደቡብ ሱዳን በ 2011 ዓም ነፃነቷን ካገኘች በኋላ የተሰጠውን የምሕረት ዕድል ከተቀበሉ እና የጦር ኃይሉን በመቀላቀል የጀነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ካገለገሉ በኋላ አምና ወደ ሱዳን በመሸሽ በደቡብ ሱዳን መንግሥት አንፃር ትግል ጀምረዋል። ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን  በጋራ ድንበራቸው ላይ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ የሆነ ክልል ለማቋቋም እና ተቋርጦ የነበረዉ የነዳጅ ዘይት ምርትና ሽያጭ ለመቀጠል ቀደም ባለ ጊዜ የተፈራረሙትን ውል በተግባር ለመተርጎም ከጥቂት ጊዜ በፊት የደረሱት ስምምነት፡ እንዲሁም፡ በካርቱም የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ሀገራቸው የሱዳኑን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኧል በሺርን በማንኛውም ጊዜ በጁባ ከተማ ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆንዋን ከጥቂት ቀናት በፊት የገለጹበት አነጋገራቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ሁኔታዎች መሻሻላቸውን ያሳየ እና በድንበራቸው አካባቢም ያሁኑን ዓይነት ግጭት ያስወግዳል ተብሎ ነበር የተገመተው። በጀርመን የሚገኘው  የሪፍት ቫሊ የፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ሱዳናዊው ማግዲ ኧእል ጊዙሊ ሁለቱ ሀገራት በዚሁ ረገድ ገና ብዙ ይቀራቸዋል ባይ ናቸው።
« እንደማስበው፡ ግልጽ የሆነ መቀራረብ አለ። በተጨባጭ የሆነው ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ እንዲሆን ከተወሰነው ድንበር አካባቢ ጦራቸውን ማስወጣታቸው ነው። ይህ አካባቢ  በጋራ ድንበራቸው የሚገኝ ሀያ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ነው። ይህ የድንበር አካባቢ ረጅም እና አዳጋች መሆኑ የማይካድ ነው። ባካባቢው የሚንቀሳቀሱት የሁለቱ ሀገራት ጦር ኃይላት ብቻ ሳይሆኑ ፣ የሁለቱ ሀገራት ዓማፅያን ቡድናት እና በተወሰነ ጊዜ አንዱን ወይም ሌላውን ወገን በመደገፍ የውክልና ጦርነት ያካሄዱ ኃይላትም ጭምር ናቸው። »


በዚሁ መሠረት ልማቱ ባልተሟላ ራቅ ብሎ በሚገኘው የሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር አካባቢ በተካሄዱ ውጊያዎች የሞተውን ሰው ቁጥር በትክክል ማወቁ እጅግ አዳጋች ነው። ሆኖም፡ የመገናኛ ብዙኃን የሚያወጡዋቸው ዘገባዎች እንዳሳዩት፡ ታህሳስ ፡ 2011 እና ጥር 2012 ዓም በደቡብ ሱዳን የጆንግሌይ ግዛት በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 600 ሰዎች ተገድለዋል። ከዚሁ ውጊያ በኋላ፡ የደቡብ ሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፊሊፕ አግወር እንዳስታወቁት፡ የሀገራቸው መንግሥት ባነቃቃው የጦር መሣሪያ ትጥቅ የመፍታት ዘመቻ ከ 10,000 የሚበልጥ የጦር መሣሪያ መሰብሰብ መቻሉን እና የጆንግሌይን ግዛት ከያው ያው ሚሊሺያ ቡድን ነፃ ለማድረግ በመስራት ላይ ይገኛል።
ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን፡ ምንም እንኳን የሰላም ውል ቢፈራረሙም፣ በጋራ ድንበራቸው ላይ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ የሆነ ክልል ማቋቋም እና ተቋርጦ የነበረዉ የነዳጅ ዘይት ምርትና ሽያጭ መቀጠል የሚያችላቸውን ስምምነት ቢደርሱም፡ አንዱ ሀገር በሌላኛው ሀገር መንግሥት አንፃር የሚዋጉ ያማፅያን እና የሚሊሺያ ቡድናትን፡ ሱዳን በደቡብ ሱዳን የጆንግሌይ ግዛት፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ በሱዳን የብሉ ናይል እና የደቡብ ኮርዶፋን የሚንቀሳቀሱትን ዓማፅያን ትረዳለች በሚል መወቃቀሳቸውን እና ይህንኑ ወቀሳ ማስተባበላቸውን መቀጠላቸው ገና በሚገባ ላልተጠናከረው በድንበሩ ፀጥታ ላይ አሉታዊ መዘዝ እንደሚያስከትል ነው በጀርመን የሚገኘው  የሪፍት ቫሊ የፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ሱዳናዊው ማግዲ ኧል ጊዙሊ የገለጹት።
« ትልቁ ስጋት የድንበሩን አካባቢ ፀጥታ ማስከበር ነው። ምክንያቱም በዚሁ አካባቢ የሚጀመር ማንኛውም ዓይነት ውጊያ ሁለቱን ሀገራት እንደገና ወደ ፍጥጫው እንዳያስገባቸው ይችላልና። »

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን


 

Audios and videos on the topic