1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረትና የአውሮጳ ኅብረት ጉባኤ

ማክሰኞ፣ የካቲት 8 2014

የአፍሪቃ ሀገራት በአውሮጳ ሀገራት ላይ ያሏቸው ቅሬታዎች ብዙ ናቸው። ከመካከላቸው አንዱ ውስን የሆነውና ለውጥም ያልታየበት የንግድ ግንኙነት ነው። የኬፕታውን ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የኤኮኖሚ ባለሞያው ካርሎስ ሎፔዝ እንደሚሉት ይህ ሀገራቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል ።

https://p.dw.com/p/474LE
Elfenbeinküste EU-Afrika-Gipfel in Abidjan
ምስል Reuters/P. Wojazer

የአፍሪቃ ኅብረትና የአውሮጳ ኅብረት ጉባኤ

የአውሮጳ ኅብረትና የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች በጋራ ጉባኤ ሲያካሂዱ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓመተ ምኅረት ካይሮ ግብጽ ውስጥ የመጀመሪያውን ጉባኤያቸውን በማካሄድ ነበር ሁለቱ ወገኖች ይፋዊ ትብብራቸውን የጀመሩት። ሁለተኛውን በ2007  በሊዝበን ፖርቱጋል ሶስተኛውን በ2010 በትሪፖሊ ሊቢያ ፣አራተኛውን በ2014 በብራሰልስ ቤልጅየም አምስተኛውን ደግሞ በአቢዣን ኮትዲቯር በ2017 አካሂደዋል። ጉባኤው ከከ2007 ዓም በኋላ በየሦስት ዓመቱ በአፍሪቃና በአውሮጳ ከተሞች እየተፈራረቀ ሲካሄድ ቆይቷል። ስድሰተኛው ጉባኤ በ2020 ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ምክንያት ዘግይቶ፣ መሪዎቹ በአካል በተገኙበት ከነገ በስተያ ይጀመራል። ለሁለት ቀናት የሚቆየው በዝግ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን የአውሮጳ ኅብረት ምኞት ነው። ለዚህም የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ከጉባኤው አስቀድሞ ባለፈው ሐሙስ ወደ ዳካር ሴኔጋል ተጉዘው ከወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳሊ ጋር ተነጋግረዋል።ፎን ዴር ላየን ከዳካር ጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሁለቱ ኅብረቶች የጋራ ርዕይ አላቸው።

«ብራሰልስ የሚካሄደውን የአፍሪቃና የአውሮጳ ኅብረቶች ጉባኤ በጋራ አዘጋጅተናል።የአፍሪቃ ኅብረትም ሆነ የአውሮጳ ኅብረት የጋራ ርዕይ አላቸው።ይኽውም የጋራ መረጋጋትና ብልጽግና ነው። ጉባኤው ይህን እውን ማድረግ የሚቻልበትን ተጨባጭ መንገዶችንና ብልሀቶችን ማሳየት አለበት ።»

ከዚሁ ጋርም የአውሮጳ ኅብረት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት  በአፍሪቃ ለመሰረተ ልማቶች ግንባታ እገዛ የሚውል 150 ሚሊዮን ዩሮ እንደመደበ አስታውቀዋል። እነዚህን የመሳሰሉ እቅዶቹን ከጉባኤው አስቀድሞ ይፋ ያደረገው የአውሮጳ ኅብረት ለረዥም ጊዜያት ሻክሮ የቆየው ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል የአሁኑ ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ይፈልጋል።ምንም እንኳን የአሁኑ ጉባኤ የዘገየው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ነው ቢባልም ታዛቢዎች ግን ጉባኤው በታቀደለት ጊዜ ያልተካሄደበት ሌላ ምክንያትም አለ ባይ ናቸው። ይህ በራሱ ለግንኙነቱ መሻከር ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል ኒልስ ኬይጀር የተባሉት የጀርመን የልማት ተቋም ባልደረባ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ። የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ የዛሬ ሁለት ዓመት ከኮሚሽነር ፎን ዴር ላየን ከተነጋገሩ በኋላ ፖሊቲኮ ለተባለው ድረገጽ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ኅብረቶች መካከል ልዩነት መኖሩን ተናግረው ነበር። ሁለቱ ወገኖች ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት አንስቶ  በጾታዊ ግንኙነት ላይ እስካላቸው እምነት፣ በሞት ቅጣት፣በአፍሪቃ ሀገራት ቀውስ የአፍሪቃ ኅብረት ሚና ድረስ  ብዙ የሚያለያዩዋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሙሳ ፋኪ አንስተው ነበር። ኮቪድ 19 ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል። የበርካታ በኮቪድ መከላከያ ክትባት እጥረት የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች በአውሮጳውያኑን ክፉኛ አውግዘዋል። አፍሪቃውያን አንዴም ሳይከተቡ አውሮጳውያኑ ለዜጎቻቸው ሥስተኛ ዙር ክትባት እየሰጡ መሆናቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ድርጊቱን የክትባት አፓርታይድ ብለውታል። የአሮውሮጳ ኅብረት ግን እነዚህን ቅሬታዎች ለመሸፋፈን ሙከራ ያደርጋል እየተባለ ነው። ተንታኝ ኬይጀር እንደሚሉት ግን ይህ አፍሪቃውያኑ ከሚፈልጉት ጋር የሚሄድ አይደለም።

Senegal Ursula von der Leyen und Präsident Macky Sall
ምስል Seyllou/Getty Images/AFP

«የአፍሪቃ ሀገራትና የአፍሪቃ ኅብረት ወቅታዊዎቹ አጀንዳዎች እንዲተገበሩና እንዲጠናቀቁ ነው የሚፈልጉት።የአውሮጳ ኅብረት ትኩረት ግን አዳዲስ ሃሳቦችንና ስልቶችን ማፍለቅ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በግንኙነቱ ላይ ውጥረት የፈጠረ ይመስለኛል።»

የአፍሪቃ ሀገራት በአውሮጳ ሀገራት ላይ ያሏቸው ቅሬታዎች ብዙ ናቸው። ከመካከላቸው አንዱ ውስን የሆነውና ለውጥም ያልታየበት የንግድ ግንኙነት ነው። የኬፕታውን ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የኤኮኖሚ ባለሞያው ካርሎስ ሎፔዝ እንደሚሉት ይህ ሀገራቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል ።

«አሁንም በቅኝ ግዛት መሰል ግንኙነት አፍሪቃውያን ሸቀጥ አቅራቢዎች ብቻ ሆነው የቀጠሉበትና ምንም ያልተቀየረበት  ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።አፍሪቃውያኑን የሚገፉ በርካታ ችግሮች አሉ። አፍሪቃውያን በክፍለ ዓለሙ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ወደ ሌሎች አጋሮች እንዲያማትሩ እየተገደዱ ነው። ያለውን በማሳደግ ረገድ የሚታየው ለውጥ አናሳ ነው።አሁን ደግሞ በተለይ «የአውሮጳ የአረንጓዴ ውል» የሚባለው ሁኔታውን ይበልጥ ያባብሰዋል።»

እነዚህን የመሳሰሉት ገፊ ሁኔታዎች ቻይና ሩስያ እና ቱርክ በአፍሪቃ ተጽእኖአቸውን እንዲያጠናክሩ ረድቷል። በተለይ በአፍሪቃ የቻይና መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ትልቁን ቦታ ይይዛል ይህም ኅብረቱን ያሰጋ ጉዳይ ነው። በዚህ የተነሳም ከአሁኑ ጉባኤ ትኩረት ዋነኛው በአፍሪቃ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የሚጠናከርበትን መንገድ መፈለግ  ነው። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ከዚሁ ጋር የአፍሪቃ መሪዎችን ያስቆጣው ፣የአውሮጳውያን የኮቪድ መከላከያ ክትባት ስስት ተነገ ወዲያ በሚጀምረው ጉባኤ መፍትሄ የሚበጅለት ጉዳይ ነው ተብሎም ይጠበቃል።

ሌላው የጉባኤው ትኩረት የአፍሪቃ ሰላምና ፀጥታ  ነው። 6ተኛው የአፍሪቃ ኅብረትና የአውሮጳ ኅብረት ጉባኤ አፍሪቃን የሚያረጋጉና ጸጥታዋን ሊያስጠብቁ የሚችሉ መፍትሄዎች ላይም ይመክራል ተብሏል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ