ስደትና ስግብግብነት | ዓለም | DW | 07.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ስደትና ስግብግብነት

በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደጠቆመዉ አንዲት ሊቢያ መንግሥት ቢኖራት እና አንዲት ኤርትራ የተሻለ ፖለቲካዊ ሥርዓት ቢመሠረትባት ወደ አዉሮጳ ከሚሻገረዉ ወይም ለመሻገር ከሚሞክረዉ አፍሪቃዊ ስደተኛ ሰማንያ በመቶዉን በየሐገሩ ማቆየት አይገድም ነበር።ሊቢያን ማን አፈረሳት?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:23
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:23 ደቂቃ

ስደትና ስግብግብነት

ሰዉ የመሆን ተፈጥሮዉ እንደ ሰዉ እንዲያዝን፤እንዲራራ፤እንዲያሰላስል የሚያስግድደዉ ሠዉ የዚያን ሶሪያዊ ሕፃን አስከሬን ፎቶ-ቪዲዮሲመለከት አለመደንገጥ፤አለመሰቀቅ ሰበብ-ምክንያቱን አለማሰላሰል በርግጥ አይችልም።አልቻለምም።ሐቻምና ጥቅምት አሳዛኝ፤አሰቃቂዉ ላፔዱዛ አጠገብ ባሕር ዉስጥ የረገፉት ኤርትራዉያን እልቂትነበር።ዘንድሮ ሚያዚያ ሊቢያ ጠረፍ የሰመጡት አረብ-አፍሪቃዉያን አሟሟት። ባለፈዉ ሳምንት የሶሪያዊዉ- ሕፃን ስደተኛ።«ሰዉ የመሆን ክብር ባሕር ዳር ሲጠረግ» ዓይነት አለዉ የቱርኩ ዜና አገልግሎት።የስደተኞች እልቂት፤ ስደተኞችን የመርዳቱ ዳተኝነትን፤ከመሰደዳቸዉ ሰበብ ምክንያት ጋር አሰባጥረን ባጭሩ እንቃኛለን።

የሐጋሪዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን ቱርክ ባሕር ዳርቻ ድፍት-ኩርምት ያለዉ ስደተኛ ሕፃን አስከሬን ፎቶ ሲያዩ-(ካዩ) እንደ ሰዉ የሚሉ፤ የሚያስቡትን አናዉቅም።እንደ ፖለቲከኛ ግን «የስደተኞች ችግር የዓለምም፤የአዉሮጳም አይደለም» አሉ-የሕፃኑ ፎቶ በዓለም በናኘ-ማግሥት ባለፈዉ-ሳምንት ሮብ።«የጀርመን እንጂ።» አከሉ ጠቅላይ ሚንስርሩ።

«ታቃላችሁ ችግሩ የአዉሮጳ አይደለም።የጀርመን ችግር ነዉ።ማናቸዉም ሐጋሪ ዉስጥ መቆየት አይፈልጉም።ሐጋሪ መቆየት ለሚፈልጉ ችግር የለብንም።ሐንጋሪ ይሁን ፖላንድ፤ ስሎቬኪያ ወይም ኢስቶኒያ መቆየት የሚፈልግ የለም።ሁሉም የሚፈልጉት ጀርመን መሔድ ነዉ።»

ወግአጥባቂዉፖለቲከኛስደተኞችሐጋሪዉስጥመቆየት«አይፈልጉም»ያሉትስደተኞችሰርብያንአቋርጠዉወደሐንጋሪእንዳይገቡድንበራቸዉንካሳጠሩበኋላነዉ።3.5 ሜትርከፍታ፤መቶ-ሰባአምስትኪሎሜትርአግድመትያለዉአጥርስደተኛዉን አላቆመም።ኦርባን ጦር አዘመቱ።ስደተኛዉም እየጎረፈ ነዉ።

ኦርባን ያዘመቱት ጦር እስከ መስከረም ሃያ ድረስ አጥሩን ዘለዉ፤ ወይም ሾልከዉ ወደ ሐጋሪ የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም ጥይት እንደማይተኩስ አስታዉቀዋል።ከመስከረም ሃያ በኋላ መንግሥታቸዉ ሥለሚወስደዉ እርምጃ የታወቀ ነገር የለም።የታወቀዉ የሐንጋሪም ሆኑ የሌሎቹ ከኮሚንስታዊዉ ሥርዓት የተላቀቁት የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት ፖለቲከኞች ከምዕራባዉያኑ በላይ የአዉሮጳ ተቆርቋሪ፤ ስደተኛን ነቃፊ፤ አባራሪ መሆናቸዉ ነዉ።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ ያክልበታል።

የሐጋሪዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን ከአስራ-አራት ዓመታቸዉ ጀምሮ ኮሚንስት ነበሩ።በትምሕርት ቤታቸዉ የሐንጋሪ ኮሚንስት ፓርቲ የወጣቶች ድርጅት ዋና ፀሐፊ እስከመሆን ደርሰዉም ነበር።ዛሬ የክርስቲያናዊ እሴት ተቆርቋሪ ናቸዉ።«ስደተኛ» አይባሉ ይሆናል።ግን ከሲኪሽቫሒርቫር ከተማ አልክሱትዶቦዝ፤ ከፌልሱት፤ ቡዳፔስት እያሉ ከከተማ ከተማ ሲዞሩ ነዉ ያደጉት።ዛሬ የስደተኞችን የሚጠሉ፤ የቀኝ አክራሪዎች ተምሳሌት ናቸዉ።እንደገና ገበያዉ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት አዉሮጳ የገባዉ ስደተኛ ቁጥር 438 ሺሕ ነዉ።ይሕ ቁጥር፤ ቱርክ፤ ሊባኖስ፤ዮርዳኖስ፤ ኬንያ ወይም ኢትዮጵያ እያንዳዳቸዉ ከሚያስተናግዱት ስደተኛ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ሲበዛ ትንሽ ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ፤ ኩዌትና ቀጠር ደግሞ ጎረቤታቸዉን የሚያነደዉ፤ እነሱም የሚያሳተፉበት ጦርነት ያሰደደዉን ሕዝብ ለማስተናገድ ፈቃደኛ አይደሉም።

ሃያ ስምንቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት እርስ በርስ የሚወዛገቡት፤ እንደ ሐንጋሪ እና ብሪታንያ የመሳሰሉት ድንበራቸዉን እስከማጠር የደረሱት ድሆቹ፤ ትናንሾቹ፤ የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ከሚያስተናግዱት ስደተኛ ቁጥር በጅጉ ያነሰዉን መቀበሉ አሳስቧቸዉ ወይም ጠልተዉት ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት UNHCR እንደሚለዉ እስካለፈዉ ሐምሌ ድረስ አዉሮጳ ከገባዉ ስደተኛ አብዛኛዉን የተቀበለችዉ ጀርመን ናት።ከትላልቆቹ የአዉሮጳ ሐገራት በጣም ትንሽ ስደተኛ የተቀበለችዉ ደግሞ ታላቅዋ ብሪታንያ ናት።ሲዊድን ከየአንድ ሺሕ ሕዝቧ ስምንት ስደተኛ ስታስተናግድ ታላቅዋ ብሪታንያ የምታስናግደዉ ስደተኛ ለየ2000ዉ ሕዝቧ ቢካፈል አንድ ሰዉ ነዉ።ይሕም በዝቶባት ብሪታንያ በተለይ ካሌ-ፈረንሳይን አቋርጦ ወደ ግዛትዋ ለመግባት የሚሞክሩትን ስደተኞችን ለማገድ ድንበሯን ልታሳጥር ጀምራለች።

በግዛታቸዉ አይደለም በድፍን ዓለም ሰበዊ መብትን፤ የሕዝብ የመንቀሳቀስ ነፃነትን፤ ፍትሕ እኩልነትን ለማስፈን እንታገላለን እያሉ ጦር እያዘመቱ የሚዋጉት የአዉሮጳና የሰሜን አሜሪካ መንግሥታት እራሳቸዉ የሚሳተፉበት ጦርነትን ሳይቀር የሸሹ ስደተኞችን ለማስተናገድ መጠየፍቸዉ፤ እርስበርስ መናቆር፤ መዘላለፋቸዉ በርግጥ አስተዛዛቢ ነዉ።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ በተለይ የአዉሮጳ ሕብረት የተመሠረተበት መሠረታዊ መርሕና ዓላማም እየፈረሰ ነዉ።

አብዱላሕ ኩርዲና ባለቤቱ ሥለ ዉጥቅንቱ የዓለም ፖለቲካ የሚያዉቁት ካለ፤ ድፍን ሐገራቸዉ ሶሪያ፤ በጣሙን ተወልደዉ፤ አድገዉ፤ ተጋብተዉ ወልደዉ የከበዱባት ከተማቸዉ ኮባኒ ቦጦርነት መዉደሟን ነዉ።እንደ ብዙዉ ጎረቤት፤ መንደርተኞቻቸዉ ሁሉ ወደ ቱርክ የተሻገሩትም በጥይት፤ ቦምብ፤ በረሐብ ላለመሞት ነበር።

ቱርክ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እያሉ ካናዳ በምትኖረዉ በአብደላሕ እሕት በኩል ጥገኝነት እንዲሰጣቸዉ አመለከቱ።የካናዳ መንግሥት መስከረም 2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) የሚለዉን አማፂ ቡድን የሚወጋ ጦር ሲያዘምት ከዘመቻዉ ዓላማዎች ቀዳሚዉ «የሁለቱን ሐገራት ሠላማዊ ሕዝብ ከአደጋ መጠበቅ»የሚል እንደነበር የአብደላሕ እሕት አልዘነጋችዉም።

አመለከተች።

ካናዳ ያዘመተቻቸዉ ተዋጊ፤ ሰላይና ማመላለሻ አዉሮፕላኖች ሶሪያና ኢራቅን ይደበድባሉ።ይሰልላሉ፤ ተዋጊ አዋጊዎችን ያመላልሳሉ።ሰባት መቶ ወታደሮችዋ አንድም በቀጥታ ይዋጋሉ አለያም ተዋጊዎችን በተለይ የኩርድ አማፂያንን ያሰለጥናሉ። ወደ ሁለት መቶ ሰላሳ ሺሕ ቶን የሚመዝን ጦር መሳሪያ ለኩርድና ለሌች አማፂያን አስታጥቃለች።የኢራቅና የሶሪያ ሠላማዊ ሰዎች ሕይወት «አሳስቧት» ወታደር፤ ገንዘብ፤ ቦምቧን የምታፈሰዉ ካናዳ ለሶሪያዊዉ ስደተኛና ለቤተሰቦቹ ግን ቦታ አልነበራትም።

አብደላሕና ቤተሰቦቹ የካናዳ መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄያቸዉን ዉድቅ ማድረጉን እንደሰሙ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ወሰኑ።ሰወስቴ ሞከሩ። አልተሳካም።ባራተኛዉ ወደ ኮስ-ግሪክ በምትቀዝፍ ጀልባ ተሳፈሩ።«ጉዞ ጀምረናል፤ ዱዓ አድርጊልኝ» የሚል መልዕክት አስተላለፈልኝ ትላለች-ካናዳ የምትኖረዉ የአብደላሕ እሕት።የሷ ፀሎት የሚበቃ ሥላልመሰላት አባታቸዉም እንዲፀልዩ መልዕክት አስተላለፈች።

እነ አብደላሕን ግን ፈጣሪም፤ ተፈጥሮም፤ መንግሥትም፤ ሰዉም አልደረሰላቸዉም። ጀልባቸዉ ተገለበጠች።ባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ሞቱ። እሱ ተረፈ።የሰወስት ዓመት ልጁ ዉሐ ገድሎት፤ አስከሬኑን ዉሐ ተፍቶ ባሕር ዳርቻ ተገኘ።ፎቶዉ በዓለም ናኘ።ወላድ ይፍረደኝ አይነት አለ-አባት ኋላ።

«ልጆቼ ለኔ ከዓለም በጣም ቆንጆ ልጆች ነበሩ።ለመሆኑ ልጆቹ እጅግ ዉድ ሐብት የማይሆኑበት ሰዉ በዓለም ላይ ይገኝ ይሆን?» ጠየቀ አባት። የቱርኩ ዜና አገልግሎት «ሰዉ የመሆን ክብር ባሕር ዳር ሲጠረግ» ማለቱ መልስ ይሆን-ይሆን?

የሕፃኑን አስከሬን ፎቶ፤ የወድም ወላጆቹን ታሪክ ያየ የሰማዉ የዓለም ሕዝብ ሐዘን፤ ሰቀቀኑን መግለፅ፤ ስደተኞችን ለመርዳት እጁን መዘርጋት፤ ኪሱን መዳበሱ አልቀረም።ሐቻምና ከሰወስት መቶ ሥልሳ የሚበልጡ ኤርትራዉያን ስደተኞች ላምፔዱዛ አጠገብ ማለቃቸዉ እንደተሰማም ተመሳሳይ አፀፋ ነበር።ባለፈዉ ሚያዚያም እንዲሁ።የተራዉ ሰዉ ሐዘን፤ርሕራሔ፤ ርዳታ፤ደግነት ግን ከሰሞናዊ ጫጫታ ባለፍ የሚተክረዉ የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ አይታዉ በማታዉቀዉ ስደተኛ ብዛት መጥለቅለቋን ካስታወቀ እነሆ መስከረም ዓመት ደፈነ።መፍትሔ ግን የለም።መፍትሔ መስጠት የሚገባቸዉ የዓለምን ሐብት የሚቆጣጠሩት፤ የአስተዳደር ፖለቲካዊ ሥርዓቷን፤ የሐገራትን ድንበር፤ የሕዝብን አኗኗር የሚበይኑት መንግሥታት መሆን ነበረባቸዉ።እነዚሕ መንግሥታት የስደተኞች ብዛት፤እልቂት፤ ስቃይ ሰቆቃቸዉ መናሩ ሲዘገብ ሕገ-ወጥ አስኮብላይ የሚሏቸዉን ሰዎች ለማሰር፤ ለመቅጣት ከመዛት መፎከር ባለፍ የችግሩ አካል እንጂ ለችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ ለመስጠት አልፈቀዱም።ወይም አልቻሉም።

በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደጠቆመዉ አንዲት ሊቢያ መንግሥት ቢኖራት እና አንዲት ኤርትራ የተሻለ ፖለቲካዊ ሥርዓት ቢመሠረትባት ወደ አዉሮጳ ከሚሻገረዉ ወይም ለመሻገር ከሚሞክረዉ አፍሪቃዊ ስደተኛ ሰማንያ በመቶዉን በየሐገሩ ማቆየት አይገድም ነበር።ሊቢያን ማን አፈረሳት?አዉሮጳ ከሚገቡት ስደተኞች አብዛኞቹ የሶሪያ፤ የአፍቃኒስታንና የኮሶቮ ዜጎች ናቸዉ።አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ ሶሪያን የሚያወድመዉን ጦርነት የጫረዉ፤ የሚያጋግመዉ ማን ይሆን?የመንስ?

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች