ስደተኞች እና የአውሮጳ ህብረት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ስደተኞች እና የአውሮጳ ህብረት

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ቫሌታ ማልታ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄዱት ጉባኤ በሜሪቴራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚካሄድ ፍልሰትን ለመግታት ይረዳሉ ባሏቸው እርምጃዎች ተስማምተዋል ። የመሪዎቹ ውሳኔ በርካታ ትችቶች እና ተቃውሞዎች ገጥመውታል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

ስደተኞች እና የአውሮጳ ህብረት

የ28 ቱ የአውሮጳ አውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በወቅቱ  የህብረቱ ሊቀመንበር በሆነችው በማልታ ዋና ከተማ ቫሌታ ባካሄዱት የጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም የመጀመሪያ ጉባኤያቸው ትኩረት ሰጥተው ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል የህብረቱ የስደተኞች መርህ  የአዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እርምጃዎች እና አስተያየቶች እንዲሁም የፊታችን መጋቢት 60 ዓመት የሚሞላው የህብረቱ መሠረት የሆነው የሮሙ ውል ይገኙበታል። መሪዎች ከሁሉ አስቀድመው የተነጋገሩት እና ውሳኔዎችንም ያሳለፉት ግን በአወዛጋቢው  የስደተኞች ጉዳይ ላይ ነበር  ። አባል ሀገራት በአሁኑ ጉባኤያቸው ስምምነት ላይ የደረሱት በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም ያስችላሉ ባሏቸው ተጨማሪ እርምጃዎች ላይ ነው ። በኢጣሊያ መሪነት እንዲወሰድ ከተስማሙባቸው ከነዚህ እርምጃዎች መካከል በሊብያ በኩል ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደትን እና ህገ-ወጥ ሰው አሻጋሪዎችን ለመከላከል እንዲሁም እዚያ የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ ለማሻሻል በተመድ ለሚደገፈው የሊቢያ መንግሥት እንዲሁም ሊቢያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ይገኙበታል ። በዚሁ ውሳኔ ህብረቱ ችግሩን ለመፍታት ከተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ፣ እና ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳይ ድርጅት  በምህፃሩ IOM ጋር በቅርበት የመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል ። ህብረቱ ከሊቢያ ጋር ብቻ ሳይሆን ሊቢያን ከሚያዋስኑ የሰሜን አፍሪቃ ሀገራት እና ከሰሀራ በስተደቡብ ከሚገኙ አጎራባቾችዋ ጋርም ስደተኞችን ለመግታት በጀመረው የጋራ ጥረት እንደሚቀጥልም ነው የገለፀው ። ሊቢያን በተመለከተም በተመድ ለሚደገፈው መንግሥት ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ በየአካባቢው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም የመቀራረብ ፍላጎት እንዳለውም ጠቁሟል ። እነዚህን ጥረቶቹን ለማገዝም በያዝነው በጎርጎሮሳዊው 2017 በተለይ በሊቢያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ህብረቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ። ኢጣልያም በበኩልዋ ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውል 200 ሚሊዮን ዩሮ መድባለች ። በስምምነቱ መሠረት የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች እንደ እስካሁኑ ከሞት የሚታደጓቸውን የባህር ስደተኞች ወደ ኢጣልያ አይወስዱም ። ይልቁንም ወደ ተነሱበት ወደ ሊቢያ ይመልሱዋቸዋል እንጂ ። የአውሮፓ ህብረት ለዚህ ማስፈፀሚያ ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ሥልጠና እና

አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችን ለመስጠት ተስማምቷል  ። ይህ የህብረቱ ውሳኔ ግን ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ቀርቦበታል ። ለሊቢያ የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት እንደገናም ስደተኞችን ወደ ሊብያ ለመመለስ መስማማታቸው በተባበሩት መግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች እና በዚሁ ሥራ በተሰማሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ክፉኛ ተወግዟል ። በግብፅ እና ኢራቅ የቀድሞ የጀርመን አምባሳደር ከዛሬ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ወዲህ ደግሞ  በሊቢያ የተመድ ልዩ ልዑክ ማርቲን ኮብለር መሪዎቹ የደረሱበትን ስምምነት ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አጣጥለውታል ።  ኮብለር ስደተኞች ልዩ ልዩ ስቃይ እና መከራ ወደ ሚደርስባቸው ሊቢያ እንዲላኩ መወሰኑ ትክክል አይደለም ነው ያሉት  ። 
«ስደተኞች በሊቢያ መጠለያ ካምፖች ተገደው ይደፈራሉ፣ ይደበደባሉ አንዳንዴም ተተኩሶባቸው ይገደላሉ ። እነዚህ በዘፈቀደ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና የሀገሪቱ ፍትህ አልባ መሆን ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለመመለስ አያስችሉም ። ይህ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ።»
ጋንዲ የተባለው መቀመጫውን ሚላን ኢጣልያ ያደረገ ስደተኞችን የሚረዳ ድርጅት ሃላፊ ዶክተር አልጋነሽ ውሳኔውን ስደተኞችን በእጅጉ የሚጎዳ ብለውታል ። ውሳኔውን ያወገዙት ዶክተር አልጋነሽ ውሳኔው ግን አላስገረማቸውም ። 
«የአውሮጳ ህብረት ከዚህ ቀደም የስደተኞች መነሻ ለሆኑ ሀገራት መንግሥታት ማለት ለሱዳን ለኤርትራ እና ሌሎች አገራት ስደትን እንዲያስቆሙገንዘብ ለመስጠት ከወሰነ በኋላ ይህኛው ስምምነትም የሚጠበቅ ነበር ። ይህ ለህብረቱ ጥሩ ያልሆነ አቋም ነው ።በማልታው ጉባኤያቸው ስደተኞችን በእጅጉ የሚጎዳ ውሳኔ አሳልፈዋል ።ሊቢያን እንመራለን ለሚሉ ለሀገራቸው ግን ምንም ለማይሰሩ ገንዘብ የሚሰጥ ከሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰው አሻጋሪዎችንም እየረዱ ነው ማለት ነው ። ስደተኞችን ከመታደግ ይልቅ ለሊቢያ ገንዘብ ሊሰጡ ነው። »
ሊቢያ የሚገኙ ስደተኞችንም የሚረዱት እና ችግራቸውን በቅርብ የሚያውቁት ዶክተር አልጋነሽ ኢጣልያ ከዓመታት በፊት በቤርሉስኮኒ ዘመን ከሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ላይ መድረሷን ያኔም በርካታ ስደተኞች ለስቃይ መዳረጋቸውን ያስታውሳሉ ።  የአውሮጳ ህብረት ይህን እያወቀ ለስደተኞቹ ሳይጨነቅ ተመሳሳይ ስህተት ለመድገም እየተዘጋጀ ነው ይላሉ ። በርሳቸው አስተያየት ህብረቱ ለሊብያ የሚሰጠው ገንዘብ ችግሩን ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም ።ዶክተር አልጋነሽ ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት እንደ ኮብለር ሁሉ ሀገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ ነው ። 

«ሊቢያ ውስጥ ብዙ ጎሳዎች አሉ ። የተለያዩ አንጃዎችም ይገኛሉ ። ገንዘቡ ለአንደኛው ወገን ከተሰጠ ሌላው ገንዘብ ያልተሰጠው ገንዘብ ያገኘው ላይ ውጊያ ይከፍታል ። ይህ አይደለም መፍትሄው ።  ችግሩ አይቆምም  ይብሳል ።ብዙ ሰዎች ሲሞቱ ማየታችን አይቀርም ። ስደተኞች ሊቢያ እንዲቆዩ ፣ወይም ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ከተደረገ በዚያ በረሀ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል የሊቢያ ችግር መንስኤ አውሮጳ እና አሜሪካን ናቸው ። በሀገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት የመነሳቱ ምክንያት እነርሱ ናቸው ።በነርሱ እርምጃ ሰበብ ነው ይህ ሁሉ የመጣው ። አሁን ይህን ችግር በተገቢው መንገድ ሊያቃልሉት ይገባል ።  አሁን ፍፁም ላልተረጋጋችው ሀገር ገንዘብ መስጠት የለባቸውም ።»
ሊቢያ አሁንም ያልተረጋጋች ሀገር መሆንዋን የሚናገሩት ዶክተር አልጋነሽ ብቻ አይደሉም ። አምባሳደር ማርቲን ኮብለርም የሊቢያ የፀጥታ ችግር በአንድ ለሊት የሚፈታ ጉዳይ እንዳይደለ ነው ያስረዱት  ።  
«ሊቢያን እንደ ሀገር ለማቆም ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ከወዲሁ ለማወቅ አይቻልም ። ሊቢያ በታሪክዋ ጠንካራ የሚባል መንግሥታዊ ተቋም ነበራት ለማለት ያስቸግራል ። የሀገሪቱ ሁለት ትውልድ ከጋዳፊ አምባገነን መንግሥት በስተቀር የሚያውቀው ነገር የለም ። እና በአንድ ለሊት የሚፈልጉትን መንግሥት ማግኘት ከባድ ነው ይህንም ሊቢያዎችም ሆኑ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ያውቀዋል ። »
 ሊቢያ ያልተረጋጋች እና ስደተኞችም ሊላኩባት የማይገባ ሀገር መሆንዋን  አዲሱ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚግማር ገብርየልም አስታውቀዋል ።ጋብርየል ትናንት እንደተናገሩት ሊብያ በጣም የተረጋጋች ሀገር ናት የሚል እምነት የላቸውም ። የርሳቸው አስተያየት ግን የፓርቲያቸው የSPD የምክር ቤት ተወካዮች ቡድን መሪ ከሰጡት አስተያየት ጋር የሚቃረን መሆኑ አስገርሟል ። የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ባሳለፉት ውሳኔ ላይ የሚሰማው ተቃውሞ አልበረደም ። 
«በርካታ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የአውሮፓ ህብረትን ውሳኔ ተቃውመው አቤቱታቸውን አቅርበዋል ። ይህን መስማት የማይፈልግ ወገን ካለ አይሰማም ። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በሊቢያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያውቃሉ ። በቱርክ ፣በግሪክ እና በየቦታው ያለውን  ስለሚያውቁ ይህን ለማስቀረት ይታገላሉ ። በሺህዎች የሚቆጠሩ አቤቱታዎች ይቀርባሉ ።»    
ዶክተር አልጋነሽን ጨምሮ እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መፍትሄ የሚሉት ስደተኞች በሰፈራ መርሃ ግብር በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ እንዲመጡ ማድረግን ነው ። ይህ በነርሱ አመለካከት ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት ማስቀረት የሚያስችል አማራጭ መፍትሄ ነው ። በባህር ጉዞ የስደተኞችን ሞት ያስቀራል በየአካባቢው ከሚገኙ የሰው አሻጋሪዎችና የታጣቂዎች ሰለባ ከመሆንም ይታደጋቸዋል ።  
«የኔ ድርጅት እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለስደተኞች ሰብዓዊ ኮሪደር ወይም መተላለፊያ ይፈጠር ነው የምንለው ። ጀርመን ባለፈው ዓመት ስደተኞችን እንዳስገባችው ሌሎቹ ሀገራትስ ለምን ይህን አያደርጉም ። ማድረግ ይችላሉ ። ምክንያቱም ወደ አውሮጳ የሚመጡት ቁጥር በአጠቃላይ እጅግ አነስተኛ ነው ። እናም ለስደተኛው ሰብዓዊ መተላለፊያ እንዲከፈት ካደረጉ ፣ሰዎች በየአካባቢው በተገቢው መንገድ እና በክብር እንዲሰፍሩ ማድረግ ይቻላል ።ከህብረተሰቡም ጋር በቀላሉ ሊዋሀዱ ይችላሉ ። »
የአውሮጳ ህብረት እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2016 ወደ 180 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች በሜዲቴራንያን ባህር በኩል አውሮጳ ገብተዋል ። በዚህ መንገድ የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም ህብረቱ ያሳለፈው እነዚህን መሰል አቤቱታዎችን ተቃውሞዎች የሚቀርቡበት ውሳኔ አሁንም ማወዛገቡ ቀጥሏል ።
ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች