ስደተኞች በዩጋንዳ | አፍሪቃ | DW | 31.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ስደተኞች በዩጋንዳ

ዩጋንዳ ያለው የናኪቫል የስደተኞች መጠለያ እንደ አንድ አነስተኛ ከተማ የሚቆጠር ነው ። በመጠለያው ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ ። የኮንጎ የሶማሊያ የሩዋንዳ የደቡብ ሱዳን የኤርትርና የቡሩንዲ ስደተኞች ተጠልለዋል ። ሁሉም ሃገራቸው ከሚካሄድ ጦርነትና የዘር ማጥፋት ሸሽተው ከለላ ፍለጋ እና አዲስ ህይወት ለመጀመር ነው ዩጋንዳ የመጡት ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:53 ደቂቃ

ስደተኞች በዩጋንዳ

የዶቼቬለዋ ዚሞነ ሽሊንድቫይን ከስፍራው እንደዘገበችው በዩጋንዳ ታሪክ ይህል ያህል ቁጥር ያለው ስደተኛ ሃገሪቱ ገብቶ አያወቅም ።ስደተኞቹ በተመዘገቡበት የስም ቅደም ተከተል እየተጠሩ ነው ። በትልቁ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ በሚገኝ ሜዳ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ልብስ ለመቀበል ተሰልፈው በመጠባበቅ ላይ ናቸው ። አብዛኛዎቹ ከዓመታት አንስቶ ፍርሃትና ሽብር ከነገሰባት ከብሩንዲ ነው የመጡት ።በናኪቫል ስደተኞች መጠለያ የዩጋንዳ መንግሥት ተጠሪ ብራያና አካንኩንዳ እደሚሉት ብዙዎቹ መያዝ ከሚችሉት ጥቂት ንብረት በስተቀር ባዶ እጃቸውን ነው የተሰደዱት ።
«እንደምታዩት ለወንዶች ለሴቶችና ለልጆች ልብስ እያደልን ነው ። ይህ ከመላው ዓለም ለስደተኖች የተሰበሰበ እርዳታ ነው ። ስጦታዎቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው ። ዛሬ ልብስ የምናድለው ለአምስት ሺህ ቤተሰቦች ነው ። ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልገናል ። መጋዘናችን ውስጥ በቂ ልብስ የለንም ። ብዙዎቹ ከሃገራቸው ሲሸሹ ጥቂት ልብሶች ብቻ ነው ይዘው የሚወጡት ።»
ባለፈው ዓመት ዩጋንዳ የገባው ስደተኛ ቁጥር በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ስደተኞች በሃገሪቱ ከለላ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል ። በየቀኑ 100 ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ዩጋንዳ ይገባሉ ። ከነዚህም ግማሽ ያህሉ ወደ ናኪቫሊው ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ነው የሚመጡት ።


የናኪቫል የስደተኞች መጠለያ ደቡብ ምዕራብ ዩጋንዳ ታንዛንያ ድንበር አቅራቢያ ነው የሚገኘው ። በመጠለያ አካባቢ መንደሮች የሉም ። መሬቱ የመንግሥት ነው ።መንግሥት ለስደተኛ ቤተሰቦች ጎጆ የሚቀልሱበትና ለእርሻ የሚሆናቸውም መሬት ያከፋፍላል ። ይህ የስደተኞች መጠለያ ባለፉት 20 ዓመታት ወደ አነስተኛ ከተማነት ተቀይሯል ። መጠለያው አሁን ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች አስጠልሏል ። በየቀኑ 50 ስደተኞች ወደ መጠለያው ይገባሉ ።
ፕየር ካሪሙሙጃንጎ ከቡሩንዲ የተሰደደው ባለፈው ዓመት ነው ። ከባለቤቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር መጀመሪያ ወደ ርዋንዳ ነበር የሄደው ። ሆኖም የርዋንዳው የስደተኞች መጠለያ በሰዎች የተጨናነቀ ስለሆነ በቋጠረው ገንዘብ የአውቶብስ ቲኬት ገዝቶ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዩጋንዳ መጥቷል ።
« እዚህ ስንመጣ ምንም አልነበረንም ። ሆኖም ሌላው ቢቀር ኡጋንዳዎች እዚህ መቆየት ትችላላችሁ ብለውናል ።ከምግብ በተጨማሪ ይህን አነስተኛ ቤት ለመሥራት የሚያስፈልገንን ለጣሪያ የሚሆን የፕላስቲክ ሽፋንና የመሳሰሉትን አግኝተናል ። አሁን ግን አርጅቶ ተበሳስቷል ።ሆኖም ረድተውናል ።ቤት መሥራት ቀላል አይደለም ። ከጭቃ ነው የሰራነው ። የተሰጠን መሬት ሰፊ አይደለም ። በዚህ የተነሳም አነስተኛ ቤት ሰርቼ ፣ በተቀረው መሬት ላይ ለምግብ የሚሆነንን ካሳቫ ተከልኩበት ። እያንዳንዳችን በወር ሁለት ኪሎ አተር እና 12 ኪሎ በቆሎ ብቻ ይሰጠናል ። በቆሎው ልጆቼን ስላሳመማቸው ነው ካሳቫ

የተከልኩት ።»
ጋራ ላይ የተሰሩት የካሪሙሙጃንጎና የሌሎችም መሰል ስደተኞች የጭቃ ጎጆዎች ጣሪያ ላስቲክ ነው ። ወደ 20 ሺህ የሚሆኑ የቡሩንዲ ስደተኞች በዚህ ሰፈራ ውስጥ ተካተዋል ።ናኪቫል የሚገኙ ስደተኞች እንደ የመጡበት ሃገር ተለያይተው ነው የሰፈሩት ። በመጠለያው ማዕከል ቢሮዎች ምግብ ማደያ መድኃኒት ቤቶችና ስደተኞቹ ያቋቋሟቸው የተለያዩ የንግድ ቤቶች ይገኛሉ ። ዩጋንዳ እጅግ የላላ የሚባል የስደተኞች ፖሊስ ነው ያላት። ወደ ሃገርዋ ከሚመጡ ስደተኞች ሁሉም ማለት ይቻላል ከለላ ያገኛሉ ። የዩጋንዳን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን ጨምሮ በርካታ ዩጋንዳውያን በ1970 ዎቹና በ1980 ዎቹ በተካሄደ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ስደተኞች ነበሩ ። በዩጋንዳ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት UNHCR ተጠሪ ቻርሊ ያክሌ የዩጋንዳን የስደተኖች አያያዝ ሌላው ዓለምም በምሳሌነት ሊወስደው የሚገባ ልምድ ነው ይላሉ።
« የዩጋንዳ መንግሥት ለስደተኞች ጥበቃ በማድረግ በኩል ቸርነቱ እና እንግዳ ተቀባይነቱ ፍፁም የተለየ ነው ። ስደተኞችን በመጠለያዎች ከማስተናገድ ይልቅ ለነርሱ በተከለ መንደር ቤት የሚሰሩበት እና ምግብ የሚያመርቱበት መሬት ይሰጣቸዋል ።ይህ የአፍሪቃ ሃገራት ብቻ ሳይሆኑ ሌላው የዓለም ክፍል ሊከተለው የሚገባ ትልቅ ምሳሌ ነው ።»

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic